የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በፈቃዳቸው ሥልጣን ለቀቁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ

የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ለተከታታይ ሳምንታት ሲካሄድ በቆየውና እሁድ ዕለት ካርቱም ውስጥ የተደረገውን ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በፈቃዳቸው ሥልጣናቸውን ለቀቁ።

በሺዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ባለፈው ጥቅምት ወር የተካሄደውን ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ተከትሎ ከጦር ሠራዊቱ ጋር የተደረሰውን የሥልጣን ክፍፍል በመቃወም ነበር አደባባይ ሲወጡ የነበሩት።

ተቃዋሚዎች ሥልጣን ወደ ሕዝቡ ተመልሶ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ በሲቪል መሪዎች እንድትደታዳር የሚጠይቁ መፈክሮችን ሲያሰሙ ነበር። ነገር ግን ወታደሮች በወሰዱት እርምጃ ትናንት እሁድ ሁለት ተቃዋሚ ሰልፈኞች ተገድለዋል።

በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣናቸው ከተወገዱ ከስድስት ሳምንታት በኋላ ወደ ኃላፊነታቸው ተመልሰው የነበሩት የጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ የሥልጣን መልቀቅ ውሳኔ የሱዳን መንግሥት ሙሉ ለሙሉ በጦር ሠራዊቱ ቁጥጥር ስር እንዲገባ ያደርገዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዶክ ሥልጣን መልቀቃቸውን በተመለከተ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር፣ "የአገሪቱ አጠቃላይ ህልውና ከባድ አደጋ ላይ" መሆኑን ገልጸዋል።

በሥልጣን ቆይታቸው ሱዳን "ወደ አደገኛ ሁኔታ" ውስጥ እንዳትገባ ለማድረግ የቻሉትን እንዳደረጉ፣ ነገር ግን "አስፈላጊው ሁሉ ጥረት ቢደረግም ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም" ስለዚህም "የተሰጠኝን የጠቅላይ ሚኒስትርነት ኃላፊነት ሱዳንን ወደ ሲቪሊ አስተዳደር ለማሸጋገር ለሚችል ሰው ለመልቀቅ ወስኛለሁ" ብለዋል።

ትናንት እሁድ በተደረገው ወታደራዊውን አስተደደር በሚቃወም ሰልፍ ላይ የፀጥታ ኃይሎች ሁለት ሰዎችን መግደላቸውን የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ የሕክምና ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።

ባለፈው ሳምንት በተካሄደው የተቃውሞ ላይ ፖሊስ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዝና ጥይት ተኩሶ ቢያንስ አምስት ሰዎች መገደላቸውን የዶክተሮች ቡድን የገለጸ ሲሆን ካለፈው ጥቅምት ወር ወዲህ በፀጥታ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 56 መድረሱን ሮይተርስ ዘግቧል።

ሱዳን ውስጥ ለሳምንታት በቀጠለው የተቃውሞ ሰልፍ የፀጥታ ኃይሎች የሚወስዱት አደገኛ እርምጃ በእጅጉ እንዳሳሰባትና እርምጃ እንደምትወስድ አሜሪካ በሳምነቱ ማብቂያ ላይ አስጠንቅቃ ነበር።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን እንዳሉት የሱዳን የፀጥታ ኃይሎች በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ እየወሰዱ ያለውን እርምጃን በተመለከተ የሚወጡ ሪፖርቶች በጣሙን እንዳሳሰባቸው በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ ገልጸዋል።

ባለሥልጣኑ ጨምረው መንግሥታቸው በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ እየተወሰደ ያለውን አደገኛ የኃይል እርምጃ እንደሚያወግዘውና ሱዳን ወደ ዲሞክራሲያዊ ሲቪል አስተዳደር እንዳትሸጋገር እንቅፋት በሆኑት ላይ ደግሞ አሜሪካ እርምጃ እንደምትወስድ አስጠንቅቀዋል።

እሁድ ዕለት ካርቱም ውስጥ በቀጠለው የተቃውሞ ሰልፍ ላይም የፀጥታ ኃይሎች ወታደራዊ አስተዳደርን በመቃወም አደባባይ የወጡ በሺዎች በሚቆጠሩ ሰልፈኞችን ለመበተን አስለቃሽ ጋዥ ተኩሰዋል።

መንግሥት ተቃውሞውን ለመቆጣጠር ከሰልፉ ቀደም ብሎ የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶች እንዲቋረጡ ያደረገ ሲሆን፣ ወደ ካርቱም የሚያመሩ ዋነኛ መንገዶችና ድልድዮች ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የታጠቁ ፖሊሶችን በማሰማራት እንዲዘጉ አድርጎ ነበር።

ባለፈው ጥቅምት ወር ጄኔራል አብዱል ፋታህ አልቡርሐን በሲቪሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ ላይ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ካደረጉ ወዲህ የእሁዱ ሕዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ 12ኛው ሲሆን ለአዲሱ የፈንጆች ዓመት ደግሞ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።

እሁድ ጠዋት ተቃዋሚዎች በሱዳን ጦር ሠራዊት መሪዎች ላይ ለወራት ሲያሰሙት የነበረውን ተቃውሞ ለመቀጠል ወደ አደባባይ መውጣት ሲጀምሩ አንስቶ የኢንርኔት አገልግሎት መቋረጡን በዓለም ዙሪያ የኢንተርኔት አገለግሎትን የሚከታተለው ኔትብሎክስ አስታውቋል።

ለወራት የቀጠለው የተቃውሞ ሰልፍ አስተባባሪዎች እንደሚሉት ዋነኛ ጥያቄያቸው ጦር ሠራዊቱ ሥልጣን በሲቨሎች ለሚመራ መንግሥት አስረክቦ ከመሪነት መንበሩ ገለል እንዲል ነው።

ተቃዋሚዎቹ ባለፈው ሳምንት በካርቱም አቅራቢያ በምትገኘው ኦምዱርማን ከተማ ውስጥ በተካሄዱት ተመሳሳይ ሰልፎች ላይ የፀጥታ ኃይሎች በከፈቱት ተኩስ በተገደሉት አምስት ሰልፈኞች ሞት ቁጣቸው ጨምሯል።

ከሞቱት በተጨማሪ በተለያዩ የሱዳን ከተሞች ውስጥ በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ፖሊስ በተከሰው አስለቃሽ ጋዝና ጥይት ከሁለት መቶ በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ተዘግቧል።

ሱዳንን ሰላሳ ዓመታት ለመጠጋ ጊዜ በፈላጭ ቆራጭነት የመሩት የቀድሞው ፕሬዝዳንት ኦማር ሐሰን አልበሽር በሕዝባዊ ተቃውሞ ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ አገሪቱ ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ በተቃውሞ ስትናጥ ቆይታለች።

ከአልበሽር ከሥልጣን መወገድ በኋላ ሥልጣን በአገሪቱ ጦር ሠራዊትና በሲቪል ፖለቲከኞች መካከል ተከፋፍሎ የሽግግር መንግሥት ቢቋቋምም ሁለቱ ወገኖች ሳይስማሙ ተቃውሞው ቀጥሎ ቆይቷል።

ሕዝባዊውን ለውጥ የመሩት ኃይሎች ጦር ሠራዊቱ ከአገሪቱ የመንግሥት ሥልጣን ውጪ ሆኖ ሲቪል አስተዳደር እንዲቋቋምና ሱዳን በሕዝብ የተመረጠ መንግሥት እንዲኖራት ግፊትና የተቃውሞ ሰልፎች ሲያደርጉ ቆይተዋል።

ነገር ግን በአገሪቱ የሽግግር ሲቪል መሪዎችና በወታደሮች መካከል ያለው አለምግባባት እየተባባሰ ሄዶ ባለፈው ጥቅምት ወር የሽግግር መንግሥቱ ሊቀመንበር የነበሩት ጄነራል አል ቡርሐን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት አስወግደው ነበር።

ከሦስት ዓመት በፊት በተደረሰውና ባልተከበረው የሥልጣን ክፍፍል ስምምነት መሠረት የሱዳን የሽግግር መንግሥት መሪ ጄነራል አል ቡርሐን ሥልጣናቸውን ለሲቪል ፖለቲከኞች ማስረከብ የነበረባቸው መፈንቅለ መንግሥት ባደረጉ በጥቂት ሳምንታት ውስጥ ኅዳር ወር ላይ ነበር።

ጄነራሉ መፈንቅለ መንግሥት ያካሄዱት ፖለቲከኞች ሰላማዊ ሰዎችን በፀጥታ ኃይሎች ላይ እያነሳሱ በመሆናቸው የእርስ በርስ ጦርነት እንዳይከሰት ለመከላከል ነው ሲሉ የእርምጃቸውን ተገቢነት ገልጸው ነበር።

ጄነራሉ ሱዳን አሁንም በሽግግር ሂደት ላይ እንደሆነችና አገሪቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለማሻገር ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ከሁለት ዓመት በኋላ ምርጫ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

ጄነራል አልቡርሐን በአገር ውስጥና ከዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በደረሰባቸው ጫና ምክንያት በመፈንቅለ መንግሥት ያነሷቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክን ወደ መንበራቸው ቢመሉሱም ተቃውሞው አሁንም እንደቀጠለ ነው።

ለወራት ወታደራዊውን መንግሥት በመቃወም በሱዳን ጎዳናዎች ላይ ድምጻቸውን ሲያሰሙ የቆዩ ሱዳናውያን በጦር ኃይሉ ላይ እምነት ስለሌላቸው ጄነራሎቹ ከመንግሥታዊ አስተዳደር ሥልጣን እንዲገለሉ እየጠየቁ ነው።

ጥቅምት ወር ላይ በጄነራል አብዱል ፋታህ አል ቡርሐን የተካሄደው መፈንቅለ መንግሥት በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ቀውስ ያባባሰው ሲሆን፣ አገሪቱ ወደ ዴሞክራሲ እንድትሸጋገር የሚጠይቁ ተቃዋሚዎች ጦር ኃይሉ በሕዝባዊ ትግል የመጣውን ለውጥ ጠልፏ በሚል ይከሳሉ።