ኦስትሪያ፡ በስህተት የታካሚዋን ጤናማ እግር የቆረጠችው የቀዶ ሕክምና ሐኪም ተቀጣች

ቀዶ ሕክምና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አዛውንቱ ታማሚ በተፈጠረው ስህተት በግራ እግሩ ፈንታ የቀኝ እግሩን አጥቷል።

በኦስትሪያ አንድ የቀዶ ሕክምና ሐኪም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ በስህተት የታካሚዋን ጤናማ እግር በመቁረጧ ተቀጣች።

አዛውንቱ ታማሚ በተፈጠረው ስህተት በግራ እግሩ ፈንታ የቀኝ እግሩን አጥቷል።

ይህ ስህተት መሆኑ የተረጋገጠው ቀዶ ሕክምናው ከተካሄደ ከሁለት ቀናት በኋላ ነበር።

ረቡዕ ዕለት በሊንዝ የሚገኘው ፍርድ ቤት የ43 ዓመቷን የቀዶ ሕክምና ሐኪም በከባድ ቸልተኝነት ጥፋተኛ ያላት ሲሆን 2700 ዩሮ ቅጣት አስተላልፎባታል።

ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ከማምራቱ በፊት ሕይወታቸው ያለፈው የታካሚው ባለቤትም 5000 ዩሮ የጉዳት ካሳ ተሰጥቷታል።

ታካሚው ለእግራቸው ቀዶ ሕክምና ለማድረግ በፍሪስታድት በሚገኘው ክሊኒክ የገቡት ባለፈው ግንቦት ወር ነበር።

ይሁን እንጂ የቀዶ ሕክምና ሐኪሟ በስህተት ጤናማው እግር ላይ ምልክት በማድረጓ ሕክምና በሚያስፈልገው እግር ፈንታ ሌላኛው እግራቸው መቆረጡን ኤኤፍፒ ዘግቧል።

የሕክምናው ስህተት እንደተፈፀመ የታወቀውም እግራቸው የተጠቀለለበት ፋሻ በሚቀየርበት ወቅት ነበር። ታካሚው ሌላኛው እግራቸው መቆረጥ እንዳለበትም ተነግሯቸዋል።

በወቅቱ ሆስፒታሉ በሰጠው ምላሽ ስህተቱ የተከሰተው "በተከታታይ ባጋጠሙ አሳዛኝ ሁኔታዎች ምክንያት ነው" ብሏል።

የሆስፒታሉ ዳይሬክተርም በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ሕዝቡን ይቅርታ ጠይቀዋል።

የቀዶ ሕክምና ሐኪሟም ፍርድ ቤት በቀረበችበት ወቅት ቀዶ ሕክምና በሚካሄድበት ክፍል ውስጥ በመረጃ ልውውጥ ሰንሰለቱ ላይ ጉድለት እንደነበር ተናግራለች።

መቆረጥ በሚያስፈልገው የግራ እግር ፈንታ ለምን በቀኙ ላይ ምልክት እንዳደረገች በተጠየቀች ጊዜም " አላውቅም" ስትል ነበር መልስ የሰጠችው።

ሐኪሟ ይህ ክስተት ካጋጠመ በኋላም ወደ ሌላ ክሊኒክ ተዛውራለች። ግማሽ የሚሆነው ቅጣቷም ታግዷል።

እንደዚህ ያሉ ክስተቶች እምብዛም የሚከሰቱ ባይሆንም ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ስህተቶች አጋጥመዋል።

እአአ በ1995 በአሜሪካ የሚኖር አንድ ሐኪም ቀዶ ሕክምና እያደረገለት የሚገኘውን የስኳር ታማሚ የተሳሳተ እግር እየቆረጠ እንዳለ የተረዳው በቀዶ ሕክምናው አጋማሽ ላይ ነበር።

በዚህ ወቅት ሐኪሙ ጡንቻዎችን፣ ጅማቶችንና በመገጣጠሚያ አካባቢ ያሉ 'ቲሹዎች' ከቆረጠ በኋላ መቁረጡን ለመቀጠል ተገዶ ነበር።