የአሜሪካ እና የታሊባን ስምምነት የአፍጋኒስታንን ውድቀት አፋጥኖታል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ታሊባን አፍጋኒስታንን በቁጥጥሩ ሥር ማድረጉ በቡድኑ እና በትራምፕ አስተዳደር መካከል በተደረገው ስምምነት ላይ የተመሠረተ ነው ሲሉ ገለጹ።
የዶሃ ስምምነት ተብሎ የሚጠራው ውል እአአ የካቲት 2020 የተፈረመ ሲሆን አሜሪካ ወታደሮቿን ከአፍጋኒስታን የምታስወጣበትን ቀን አስቀምጧል።
ጄነራል ፍራንክ ማክኬንዚ ስምምነቱ በአፍጋኒስታን መንግስት እና በወታደሮች ላይ "አስከፊ ውጤት" አለው ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስቲንም በሃሳቡ ተስማምተው ስምምነቱ ታሊባን "እንዲጠናክር ረድቷል" ሲሉ ገልጸዋል።
የዶሃው ስምምነት ቀን ገደብ ከማስወቀመጥ በተጨማሪ እንደ አልቃይዳ ያሉ ቡድኖች የአሜሪካን እና የአጋሮቿን ደህንነት አደጋ ላይ እንዳይጥሉ እርምጃዎችን እንዲወስድ ታሊባን ሰፊ ግዴታዎችን ተጥሎበታል።
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን መንበሩን ከተቆጣጠሩ በኋላ የሠራዊቱን የማስውጣት ዕቅዱን ቀጥለውበታል። ቀነ ገደቡ ግን ከግንቦት ይልቅ ነሐሴ መጨረሻ ሆነ።
የአሜሪካ የመከላከያ ባለሥልጣናት ሐሳባቸውን የተናገሩት ረቡዕ በተወካዮች ምክር ቤት የመከላከያ አገልግሎት ኮሚቴ ፊት ቀርበው ነበር።
ባለስልጣናቱ ሐሳባቸውን የሰጡት የውጭ ኃይሎች ዜጎቻቸውን ሲያስወጡ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ተስፋ የቆረጡ አፍጋኒስታኖች እንዲታደጓቸው ሲለምኑ በካቡል አውሮፕላን ማረፊያ ሁከት ከተነሳ ከሳምንታት በኋላ ነው። በወቅቱ በአጥፍቶ ጠፊ ጥቃት 182 ሰዎች ተገድለዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ዕዝ መሪ የሆኑት ጄነራል ማክኬንዚ ከአፍጋኒስታን መውጣቱን በበላይነት ይቆጣጠሩ ነበር። ሥራው አሜሪካ በሃገሪቱ የነበራትን የ 20 ዓመታት ቆይታ እና ረዥሙ ጦርነት ያበቃበት ነበር።
ጄነራል ማክኬንዚ ለኮሚቴው እንደገለጹት የዶሃው ስምምነት በአፍጋኒስታን መንግሥት ላይ "ሁሉም ዕርዳታ ይጠናቀቃል ብለው የሚጠብቁበትን ቀን" ያስቀመጠ ጠንካራ የስነ-ልቦና ተፅእኖ አሳድሯል።
ዩናይትድ ስቴትስ በአፍጋኒስታን የሚገኙትን ወታደራዊ አማካሪዎቿን ከ 2500 በታች ዝቅ ካደረገች የአፍጋኒስታን መንግስት እና ወታደሩ መውደቃቸው የማይቀር መሆኑን ካመኑ "የተወሰነ ጊዜ" ማለፉን ገልጸዋል።
ከዶሃ ስምምነት በኋላ በሚያዝያ ወር በፕሬዚዳንት ባይደን የታዘዘው የወታደራዊ ቅነሳ ችግሩን ያባባሰው ነው ብለዋል።
ኦስቲን በበኩላቸው አሜሪካ በታሊባን ላይ የአየር ድብደባን ለማስቆም በዶሃው ስምምነት በመግባባታቸው "እስላማዊ ቡድኑ ተጠናከረ፣ በአፍጋኒስታን የጸጥታ ኃይሎች ላይ የማጥቃት ሥራቸውን ጨምሯል። አፍጋኒስታኖች በየሳምንቱ ብዙ ሰዎችን እያጡ ነበር።"
የመከላከያ ባለሥልጣናቱ ማክሰኞ ከሴኔቱ የጦር መሣሪያ አገልግሎት ኮሚቴ ጋር ተነጋግረዋል። በወቅቱ ጄነራል ሚሌይ እና ጄኔራል ማክኬንዚ በነሐሴ ወር አሜሪካ ጦሯን ከማሰወውጣቷ በፊት በአፍጋኒስታን የ 2500 ወታደሮች እንዲቆዩ ምክረ ሃሳብ አቅርበው እንደነበር ገልጸዋል።
ጄኔራል ሚሌይ አክለውም ቡድኑ አሁንም ከአልቃይዳ ጋር ያለውን ግንኙነት ያላቋረጠ አሸባሪ ድርጅት በመሆኑ አሜሪካውያንን ከአሸባሪ ጥቃቶች ለመጠበቅ ከባድ ያደርገዋል ብለዋል።
የታሊባኑ ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ ረቡዕ ዕለት ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ታጣቂዎች "ከአፍጋኒስታን በመነሳት አሜሪካንን ጨምሮ ለማንኛውም ሃገር ምንም ዓይነት ስጋት እንደማይኖር ለዓለም ዋስትና ሰጥተዋል" ብለዋል።
"በአፍጋኒስታን እስላማዊ ኢሚሬት እና በዩናይትድ ስቴትስ መካከል በዶሃ ለተፈረመው ስምምነት መተግበር ቁርጠኛ ነን። አሜሪካና እና አጋሮቿም ለስምምነቱ ቁርጠኝነት እንዲሆኑ እንፈልጋለን። አሉታዊ አስተያየቶችን ከመስጠት ይልቅ የዲፕሎማሲን እና የትብብርን መንገድ ቢመርጡ ለእነሱ የተሻለ ይሆናል"ብለዋል።












