ጊኒ፡ ሦስት ታሪካዊ መፈንቅለ መንግሥቶችን ያስተናገደች አገር

ጊኒ በታሪክ አዙሪት ውስጥ ያለች ትመስላለች። ነፃነቷን እ.አ.አ በ1958 ካወጀችበት ጊዜ አንስቶ፣ ጊኒ በአጠቃላይ ሦስት የተሳኩ የመንግሥት ግልበጣዎችና በርካታ ሙከራዎችን አስተናግዳለች።

የቀድሞዎቹ ሁለት መፈንቅለ መንግሥቶች፣ የአገሪቱ መሪዎቹ ከሞቱ በኋላ የተከሰቱ ሲሆን፤ አሁን ከ10 ቀናት በላይ ያስቆጠረው የዚህ ዓመቱ መፈንቅለ መንግሥት ደግሞ በዲሞክራሲያዊ ምርጫ ወደ ስልጣን የመጡትን ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴን በሕይወት እያለ መፈፀሙ ነው።

በጊኒ የመጀመሪያውን የተሳካ መፈንቅለ መንግሥት የመሩት ኮሎኔል ላንሳና ኮንቴ ነበሩ።

የማዕከላዊ መንግሥቱን ከመንበሩ የገለበጡት እ.አ.አ በ1984 ሲሆን፣ ይህ የሆነውም የጊኒ የነፃነት አባት በመባል የሚታወቁት የአገሪቱ መሪ የነበሩት አሕመድ ሴኩ ቱሬ በሞቱ በሳምንቱ ነበር።

ኮሎኔሉ ከጥቂት ጊዜ በኋላ የጄኔራልነት ማዕረግ የተሰጣቸው ሲሆን፤ በወቅቱ የአገሪቱን ብሔራዊ ተሃድሶ ለመምራት የተመሰረተውን ወታደራዊ ኮሚቴ በበላይነት ይመሩ ነበር።

እርሳቸው ግን የአሕመድ ሴኩ ቱሬ ሞትን ተከትሎ ጊዜያዊ ፕሬዚደንት የነበሩትን ሉዊ ቤያቮጊን ገለበጡ።

በፈረንጆቹ ዲሴምበር 1990 አዲስ ሕገ መንግሥት በማጽደቅ የፓርቲ ብዝኀነት የተንፀባረቀበት አዲስ መንግሥት መሠረቱ።

በ1993ም በተካሄደ አገራዊ ምርጫ አሸናፊነታቸውን አወጁ። ከዚያ በኋላም ሁለት ጊዜ በተከታታይ ተመርጠው ጊኒን በበላይነት መርተዋል።

ዋነኛ ተቃዋሚያቸው አልፋ ኮንዴ በ1998 በቁጥጥር ሥር ውለው ታስረዋል። አልፋ ኮንዴ በፈረንጆቹ የ2001 አምስተኛ ወር ላይም የፕሬዚደንቱን ምሕረት አግኝተው ከእስር ተለቀቁ።

የላንሳና ኮንቴ አገር መሪነት ዘመን ግን አልጋ በአልጋ አልነበረም፤ እንደውም እረፍት የሚነሳ እንጂ።

በ1985 የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተደረገባቸው። በ1996 የተቀሰቀሰ አመጽ ባሕሪውን ቀይሮ ወደ መፈንቅለ መንግሥት የተቀየረ ሲሆን በአጠቃላይ ወደ 2000 ወታደሮች ተሳትፈውበት ነበር።

ወታደሮቹ የአገሪቱን ራዲዮ ጣቢያ በመቆጣጠር የ'ብሔራዊ ደኅንነት ኮሚቴ' ማቋቋማቸውን ገለፁ።

በ2007 መጀመሪያ ላይ ተቃዋሚዎችና ሕዝቡ በጋራ በመሆን የአገሪቱ አመራር ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በሰልፍ ገለፁ።

በዚህም ወቅት የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ድርጅቶች ወደ 180 ሰዎች መገደላቸውን መዝግበዋል።

የ2008'ቱ ሙሳ ዳዲ ካማራ እና ኤንሲዲዲ'ው

እ.አ.አ. በ2008 የመጨረሻው ወር ላይ ላንሳና ኮንቴ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ። ይህም ክስተት የተወሰኑ ወታደሮች በማግስቱ መፈንቅለ መንግሥት ለማካሄድ ምቹ ሁኔታን ፈጠረላቸው።

እነርሱም ኤንሲዲዲ በመባል የሚታወቀውን 'ብሔራዊ የዴሞክራሲ እና የልማት ምክር ቤት'ን አቋቋሙ።

የወታደራዊ ቡድኑ መሪ ካፕቴን ሙሳ ዳዲ ካማራ ከዲሴምበር 23/2008 ጀምሮ በ2010 የሲቪል አስተዳደር እስኪመሰረት ድረስ በኃይል ሥልጣን የተቆጣጠረው ወታደራዊ ቡድን መሪ ሆነው ዘለቁ።

ሙሳ ዳዲ ዘወትር የሚታወሱት ሞቅ ባሉና ንዴት በተሞላባቸው ንግግሮቻቸው ሲሆን ከዚያም በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ የነበሩትን የአውሮፓ አገራት ዲፕሎማቶችን በሕዝብ ፊት በማዋረዳቸውም ጭምር ነበር።

ሴፕቴምበር 28/2009 በኮናክሪ ስቴድየም የተካሄደውን የተቃውሞ ስብሰባ የደኅንነት ኃይሎች ጭካኔ በተሞላበት መልኩ በተኑ። በዚያን ዕለት አምነስቲ ኢንተርናሽናል 157 ሰዎች መገደላቸውንና ሴቶች መደፈራቸውን አሳውቋል።

በዲሴምበር 3/2009 ደግሞ ሙሳ ዳዲ ከተሞከረባቸው ጥቃት አመለጡ።

የግድያ ሙከራውን የፈፀሙት የሙሳ ዳዲ ቀኝ እጅ የነበሩት ቱምባ ዲያካቴ ነበሩ።

በዚህ የግድያ ሙከራ ወቅት ሙሳ ዳዲ ጭንቅላታቸው ላይ ጉዳት ደርሶ ስለነበር ጄኔራል ሴኩባ ኮናቴ ተክተው በ2010 የሽግግር ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ አገሪቱን አስተዳደሩ።

የ2010 ታሪካዊ ምርጫም አላፋ ኮንዴ'ን ወደ መንበረ ሥልጣኑ አመጣቸው።

ሦስተኛውን ዙር ምርጫ ያቋረጠው የመፈንቅለ መንግሥት-ማማዲ ዱምባያ

ታሪካዊው ተቃዋሚ ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴ በ2015 ለሁለተኛ ጊዜ ተመረጡ።

በ2019 እና 2020 መካከል የጊኒን ሕዝብ የአልፋ ኮንዴ ለሦስተኛ ዙር መመረጥ ሲያስጨንቀው ቆይቶ ዋነኛው መነጋገሪያ ርዕሰ ጉዳይ ሆኖ ከረመ።

አልፋ ኮንዴም ብሔራዊው ምክር ቤት ሕገ መንግሥቱ እንዲያሻሽል ትዕዛዝ ሰጡ። ይህም ለውጥ ለሦስተኛ ጊዜ ለመመረጥ እንዲያስችላቸው አደረገ።

ነገር ግን ሦስተኛ ዙር የሥልጣን ዘመን የተመረጡት ኮንዴ ባልታሰበና ባልተጠበቀ መልኩ በፈረንጆቹ ሴፕቴምበር 2/2021 በድንገት በተጠነሰሰው የማማዲ ዱምባያ መፈንቅለ መንግሥት ተጨናገፈ።

ፕሬዚደንት አልፋ ኮንዴም በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን 'ብሔራዊ የአንድነትና የልማት ኮሚቴ' ገልፆ የተቀየረውን ሕገ መንግሥት ማገዱን አሳወቀ።

የዚህም ዋና መሪ ሌቴናንት ኮሎኔል ማማዲ ዱምቡያ ሲሆን ማማዲ ማዕረጉንና ሹመቱን ያገኘው በአላፋ ኮንዴ ነበር።