የፀረ-አበረታች ኤጀንሲ በአትሌቲክስ ውስጥ የካናቢስን መታገድ ሊመረምር ነው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የዓለም ፀረ-አበረታች ንጥረ ነገሮች ተቆጣጣሪ ኤጀንሲ የሆነው ዋዳ በአትሌቲክስ ውስጥ የካናቢስን መከልከል ዳግም ሊመረምር ነው።
ኤጀንሲው ይህን የሚያደርገው አሜሪካዊቷ የአጭር ርቀት ተወዳዳሪ የካናቢስ ምርመራ ማለፍ ባለመቻሏ በቶኪዮ ኦሊምፒክ ሳትሳተፍ ከቀረች በኋላ ነው።
የ21 ዓመቷ ሻካሪ ሪቻርደሰን የወላጅ እናቷን ሞት ተከትሎ ሐዘኗን ለመቋቋም ካናቢስ መጠቀሟን ይፋ አድርጋ ነበር።
የዓለም ፀረ-አበረታች ንጥረ ነገሮች ኤጀንሲ በካናቢስ ዙሪያ ሳይንሳዊ ምርመራ በቀጣይ የፈረንጆች ዓመት እንደሚጀመር ገልጾ፤ ካናቢስ በአትሌቲክስ ውስጥ የተከለከለ ሆኖ አስከ 2022 ይቀጥላል ብሏል።
የፀረ-አበረታች ኤንጀንሲው በካናቢስ ላይ ያለው ሕግ ዳግም ማጤን ያስፈለው "ከሚመለከታቸው በርካታ አካላት ጥያቄዎች በመቅረባቸው ነው" ብሏል።
ሪቻርድሰን ሰኔ ወር ላይ ለቶኪዮ ኦሊምፒክ ማጣሪያ በአሜሪካ በተደረገ ውድድር በ100 ሜትር ማሸነፍ ችላ ነበር። በዚህም በማጣሪው ግማሽ ፍጻሜ ውድድር ላይ ያጠናቀቀችበት ሰዓት 6ኛው በሴቶች የተመዘገበ ፈጣን ሰዓት ሆኖ ተመዝግቦ ነበር።
የአትሌቷ የካናቢስ ምርመራ ውጤት 'ፖዘቲቭ' የሆነው በኦሊምፒክ ማጣሪያ ላይ ሲሆን፤ በማጣሪያ ውድድር ላይ ያስመዘገበችው ፈጣኑ ሰዓትም ውድቅ ተደርጎባታል። የአንድ ወር እገዳም ተጥሎባታል።
ሪቻርድሰን የተካፈለችበት ማጣሪያ ውድድር የተካሄደው ከወላጅ እናቷ ሞት ከአንድ ሳምንት በኋላ ነበር።
የአሜሪካ የትራክ እና መስክ እንዲሁም የአሜሪካ ፀረ-አበረታች ኤጀንሲ በአትሌቷ ወላጅ እናት ሞት ሐዘናቸውን በመግለጽ፤ አትሌቷ ዕጹን የተጠቀመችው የውድድር አቅሟን ከፍ ለማድረግ ባይሆንም ሕጉን ከመከተል ውጪ ሌላ አማራጭ የለንም ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት ካናቢስ ተጠቅሞ የተገኘ አትሌት እስካ አራት ዓመት እግድ ሊጣልበት ይችላል።
ይሁን እንጂ እግዱ የተላለፈበት አትሌት ዕጹን ተጠቅመው ከተገኙ የውድድር አቅምን ከፍ ለማድረግ አለመሆኑን ማረጋገጥ የሚችሉ ከሆነ ቅጣቱ ወደ ሦስት ወራት ዝቅ ሊደረግ ይችላል።
ከዚህ ውጪ አንድ አትሌት ለሕክምና ክትትል ፍቃደኛ ሆኖ የሚገኝ ከሆነ የትኛውም አይነት እግድ ወደ አንድ ወር ዝቅ ሊደረግ ይችላል።












