ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካው አየር መንገድ ያልተከተቡ ሰራተኞቹን 200 ዶላር በየወሩ ሊቀጣ ነው
ዴልታ አየር መንገድ የአሜሪካ ሦስተኛው ትልቁ አየር መንገድ ሲሆን የኮቪድ-19 ላይ ክትባት ባልወሰዱ ሠራተኞች ላይ በየወሩ 200 ዶላር እንዲከፍሉ ሊያደርግ ነው።
ሁለቱንም ክትባቶች ወስደው በበሽታው ለተያዙ ለኮቪድ ህመምተኞች ብቻ የሕመም ክፍያ እከፍላለሁ ብሏል።
የቫይረሱ ስርጭት በመላው አሜሪካ እየጨመረ ባለበት ሁኔታ ውሳኔው የኮሮናቫይረስን "በከፍተኛ ሁኔታ መስፋፋት" ለመግታት ይረዳል ብለዋል ኃላፊው ኢድ ባስቲያን።
እርምጃው አንድ ትልቅ ኩባንያ ሠራተኞቹ እንዲከተቡ ለማድረግ የተወሰደ ሙከራ ነው።
ባስቲያን ለሠራተኞች በላኩት በማስታወሻ ላይ የዴልታ ተጨማሪ ክፍያ ከታህሳስ ጀምሮ በጤና እንክብካቤ መድን ዕቅዱ በተመዘገቡ ሠራተኞቹ ላይ እንደሚተገበር ገልጸዋል።
ይህም አብዛኛዎቹን 75 ሺህ ሠራተኞቹን የሚመለከት ይሆናል።
ዴልታ ለኮቪድ-19 የሆስፒታል ቆይታ በአንድ ሰው በአማካይ 50 ሺህ ዶላር ዋጋ ይከፍላል ብለዋል።
"ክትባቱን ያለመውሰድ ውሳኔው ለኩባንያችን እየፈጠረ ያለውን የገንዘብ አደጋን ለመቅረፍ ይህ ተጨማሪ ክፍያ አስፈላጊ ይሆናል" ብለዋል።
"B.1.617.2 የተባለው አዲስ ዝርያ ከተስፋፋ ወዲህ ከኮቪድ ጋር በተያያዘ ሆስፒታል የገቡ የዴልታ ሠራተኞች ሙሉ በሙሉ ያልተከተቡ ናቸው።"
ከመስከረም 30 ጀምሮ ደግሞ ያልተከተቡ የዴልታ ሠራተኞች በየሳምንቱ የኮቪድ ምርመራዎችን ማድረግ እና በዴልታ የቢሮ ውስጥ ጭምብል ማድረግ አለባቸው።
ሁሉም የአሜሪካ አየር መንገድ ሠራተኞች በአውሮፕላን ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል መልበስ ቢኖርባቸውም በቢሮዎች ውስጥ ግን አይተገበርም።
ዴልታ የተሰኘው የኮሮናቫይረስ ዝርያ በአሜሪካ መስፋፋቱን ተከትሎ የሃገሪቱ ኩባንያዎች ሠራተኞቻቸው ክትባት እንዲወስዱ ለማበረታታት የተለያዩ ዘዴዎች እየሞከሩ ነው።
እንደ ዩናይትድ አየር መንገድ፣ ጎልድማን ሳክስ፣ ማይክሮሶፍት እና ጉግል ያሉ ኩባንያዎች ወደ ሥራ ለመግባት ሙሉ በሙሉ መከተብ እንዳለባቸው ለሠራተኞቻቸው ነግረዋል።
የኢንቨስትመንት ኩባንያው ቫንጋርድ ለክትቡ ሠራተኞቹ የ 1 ሺህ ዶላር ጉርሻ ሰጥቷል። አማዞን እና አፕል ግን በዚህ ረገድ ምንም ፖሊሲ አላወጡም።
የኢንቨስትመንት ባንኩ ክሬዲት ሱይስ ሁሉም ክትባት ያልሰጣቸው ሠራተኞች ከመስከረም 7 ጀምሮ ከቤት እንዲሠሩ እንደሚጠይቅ ረቡዕ ዕለት አስታውቋል። እንደ ሌሎቹ ኩባንያዎች ሁሉ ወደ ቢሮ ሙሉ ለሙሉ መመለሻ ጊዜን እስከ ጥቅምት ድረስ አዘግይቷል።
በወረርሽኙ ወቅት ከፍተኛ የፍላጎት መቀዛቀዝ ተከሰቶ የአሜሪካ አየር መንገዶች በራስ መተማመንን ለመመለስ በሚታገሉበት ጊዜ ነው ዴልታ አየር መንገድ በአዲስ እርምጃ የመጣው።
የአየር መንገዱ የመንገደኞች እስከ ሰኔ 30 ድረስ ያለው የሦስት ወራት ገቢ 5.3 ቢሊዮን ዶላር ነበር። ቀውሱ ከመጀመሩ በፊት በ 2019 ከነበረው ተመሳሳይ ጊዜ ከ 50 በመቶ በላይ ቀንሷል።