ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ለሐረሪ ተወላጆች በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች እንዲሁም በሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያዎች ይቋቋማል ተባለ
ከሐረሪ ክልል ውጭ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ለሚኖሩ የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጅ አባላት በሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አባላት ምርጫ ላይ መሳተፍ እንዲችሉ በተለያዩ ከተሞችና ክልሎች የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ።
መስከረም 20 ለሚደረገው ምርጫ በአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች፣ በኦሮሚያ (አዳማ፣ ጭሮ፣ ኮምቦልቻ፣ ጉርሱም፣ ፈዲስ፣ ደደር እና ሃሮማያ)ና በሶማሌ ክልል የምርጫ ጣቢያዎች እንደሚቋቋሙም ተገልጿል።
ከሐረሪ ክልል ውጭ በሌሎች አካባቢዎች የሚኖሩ የብሔረሰብ ተወላጆች አባላት በሐረሪ ብሔራዊ ጉባዔ አባላት ምርጫ ላይ መሳተፍ አይችሉም በሚል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ወስኖ የነበረ መሆኑ ይታወሳል።
ይህንን በመቃወም ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄዶ በሰበር ችሎት መሰረት የብሔረሰቡ ተወላጆች በተለያዩ አካባቢዎች ሆነው መምረጥ እንደሚችሉ ተበይኗል።
ስድስተኛው አጠቃላይ ብሔራዊ ምርጫ በዋናነት ሰኔ 14፣ 2013 ዓ.ም የተካሄደ ቢሆንም በጸጥታ ችግር፣ በመራጮች ምዝገባ ሂደት ላይ በታዩ ግድፈቶች፣ በመራጮች ምዝገባ ላይ በቀረቡ አቤቱታዎችን ለማጣራት ጊዜ በማስፈለጉ የድምፅ መስጫው ቀን በአንዳንድ ክልልሎችና የምርጫ ክልሎች እንዲራዘም መወሰኑ ይታወቃል።
ምርጫ የተራዘመባቸው ሶማሌ፣ ሐረሪ እና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል መስከረም 20 ምርጫ እንዲካሄድ ተወስኗል።
በዚህም መሰረት የመራጮች ምዝገባ ባልተደረገባቸው እና በተቋረጠባቸው የምርጫ ክልሎችን አስመልክቶ ምርጫ ቦርድ ወሳኔዎችን አስተላልፏል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ በሐረሪ ክልል በጀጎል ዙሪያ እና ሁንደኔ የምርጫ ክልል ምዝገባው በተለያየ የክልል እና የተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚመርጡትን የሐረሪ ብሔረሰብ ተወላጆች እና ከብሔረሰቡ ውጪ ያሉ ተወላጆች ተቀላቅለው በመመዝገባቸው ተለያይቶ እንደ አዲስ ምዝገባ እንዲካሄድ መወሰኑ ተገልጿል።
በጀጎል ልዩ ምርጫ ክልል እንዲሁ የመራጮች ምዝገባ ተቋርጦ እንደነበር ያስታወቀው ምርጫ ቦርድ ለአምስት ተጨማሪ ቀናት የሟሟያ ምዝገባ እንዲከናወንም ውሳኔ ተላልፏል።
ሌላው ምርጫ ያልተደረገበት የሶማሌ ክልልንም በተመለከተ የመራጮች ምዝገባ እየተከናወነ በነበረበት ወቅት ከፖለቲካ ፓርቲዎች ለቦርዱ አቤቱታ ቀርቦ ነበር።
ቦርዱ የመራጮች ምዝገባ ሂደቱ መጣራት እንደሚገባው አምኖ የመራጮች ምዝገባ እንዲቆም በመወሰን 10 የምርጫ ክልሎች ላይ ምርመራ ተደርጓል። ከተለያዩ ሲቪል ማህበራት የተውጣጣ አጣሪ ቡድን በመላክ ምዝገባ ሂደቱ ላይ የቀረቡትን አቤቱታዎች አጣርቷል።
የቡድኑንም ግኝት መሰረት በማድረግ ጅጅጋ 1፣ በጅጅጋ 2 የተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ እንዲከናወን ተወስኗል። ከዚህም በተጨማሪ በቀብሪደሃር ከተማ፣ በቀብሪደሃር ወረዳ፣ በመኢሶ፣ በአፍደም የክልል ምክር ቤት ምርጫ ክልሎች እንዲሁም የመራጮች ምዝገባ ሙሉ ለሙሉ በድጋሚ የሚካሄድባቸው ስፍራዎች ናቸው ተብሏል።
በተወሰኑ የምርጫ ጣቢያዎች የመራጮች ምዝገባ እንዲደገምባቸው የተላለፈባቸው ደግሞ በዋርዴር ምርጫ ክልል ውስጥ በ2 ምርጫ ጣቢያዎች፤ በፊቅ ምርጫ ክልል በ1 ምርጫ ጣቢያ ፣ በገላዴን ምርጫ ክልል በ1 ምርጫ ጣቢያ፣ በጎዴ ከተማ ምርጫ ክልል በ4 ምርጫ ጣቢያዎች ፣ በምስራቅ ኢሜ ምርጫ ክልል በ3 ምርጫ ጣቢያዎችና በቤራኖ ምርጫ ክልል በ3 ምርጫ ጣቢያዎች እንደሆነም ምርጫ ቦርድ አስታውቋል።
የመራጮች ምዝገባ በተቋረጠባቸው ቦታዎች ሁሉ ለ5 ቀናት ያህል የመራጮች ምዝገባ ተሟልቶ እንዲጠናቀቅ መወሰኑም ተገልጿል።
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ያለአግባብ ምዝገባ የተከናወነባቸው በተባሉ የምርጫ ክልሎች የድጋሚ ምርጫ ሙሉ ለሙሉ እንዲከናወን የተወሰነ ሲሆን እነዚህም ዘልማም፣ ዲዚ ልዩ፣ ሱርማ፣ ሙርሲ ማጀት መደበኛ ምርጫ ክልሎች ናቸው።
በክልሉ በጉራፈርዳ ወረዳ የሚገኙ በቴፒ እና ሸኮ ልዩ የሚጠቃለሉ ጣቢያዎችን በተመለከተ ቦርዱ ተጨማሪ ውሳኔን የሚያስተላልፍ እንደሆነም አሳውቋል።