ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
አፍጋኒስታን፡ ሃገራት ዜጎቻቸው ወደ ካቡል አየር ማረፊያ እንዳይሄዱ አስጠነቀቁ
በርካታ ሃገራት በአፍጋኒስታኑ ካቡል አየር ማረፊያ የሽብር ጥቃት ሊኖር ስለሚችል ዜጎቻቸው ወደ አየር ማረፊያ እንዳይሄዱ አስጠንቅቀዋል።
አውስትራሊያ፣ ዩናይትድ ስቴትስና ዩናይትድ ኪንግደም ለዜጎቻቸው ማስጠንቀቂያ ከሰጡ መካከል ናቸው።
ከአየር ማረፊያው ውጪ ያሉ ሰዎችም አካባቢውን ለቀው እንዲሄዱ ተነግሯቸዋል።
ከ82 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች ከ10 ቀናት በፊት በታሊባን ታጣቂዎች እጅ ሥር በወደቀው ካቡል አየር ማረፊያ በኩል ከአፍጋኒስታን ወጥተዋል።
የተለያዩ ሃገራት ከተቀመጠላቸው የነሃሴ 25 ቀነ ገደብ በፊት ዜጎቻቸውን ከአፍጋኒስታን ለማስወጣት እየተሯሯጡ ነው።
በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አሁንም አየር ማረፊያ ውስጥና ውጪ ተኮልኩለው አፍጋኒስታንን ጥለው ለመውጣት እየተጠባበቁ ይገኛሉ።
ታሊባን ቀነ ገደቡን ከነሃሴ 25 በላይ ለማራዘም የቀረበውን ሐሳብ ባይቀበሉም የውጪ ዜጎችን አፍጋናዊያን በነፃ ከሃገር እንዲወጡ እንደሚፈቅዱ ቃል ገብተዋል ሲሉ የአሜሪካው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን ተናግረዋል።
የአውስትራሊያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው "በአሁን ወቅት በጣም አስጊ የሆነ የሽብር ጥቃት አለ" ሲሉ ተናግረዋል።
ይህ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያ የተሰጠው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በካቡል አየር ማረፊያ የምስራቅና ሰሜን መግቢያ ያሉ ሰዎች ሥፍራውን እንዲለቁ ካሳሰበች በኋላ ነው።
ዩናይትድ ኪንግደምም በተመሳሳይ 'በሥፍራው ያሉ ሰዎች ደኅንነቱ ወደተጠበቀ ቦታ ሄደው ሁኔታውን ይከታተሉ' ብላለች።
የዩኬ ውጭ ጉዳይ ቢሮ አፍጋኒስታን ውስጥ አሁን ያለው ነገር አሁንም "የተረጋጋ አይደለም" ብሏል።
ሁሉም ማስጠንቀቂያ ያወጡ ሃገራት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥበዋል።
የአሜሪካው ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ባለፈው ማክሰኞ አፍጋኒስታን ውስጥ ባለው የኢስላሚክ ስቴት ቡድን ዛቻ ምክንያት የአሜሪካ አውሮፕላኖች ሥራቸውን በቅርቡ ያቆማሉ ብለው ነበር።
ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ አሜሪካ ባመቻቸችው በረራ 19 ሺህ ገደማ ሰዎች አፍጋኒስታንን ጥለው ወጥተዋል ሲሉ ብሊንከን ተናግረዋል።
ብሊንከን አክለው አሜሪካ ከተቀመጠው ቀነ ገደብ በኋላም ቢሆን አፍጋኒስታንን ጥለው መውጣት ለሚፈልጉ ሰዎች እርዳታ ትሰጣለች።
1500 ገደማ አሜሪካዊያን አሁንም አፍጋኒስታን ውስጥ ሊኖሩ ይችላሉ ያሉት ብሊንከን ሃገራቸው እነዚህ ሰዎች ያሉበትን ለማግኘት የተቻላትን እያደረገች እንዳለች አሳውቀዋል።
የአሜሪካው የስለላ ድርጅት ሲአይኤና የአሜሪካ ጦር አፍጋኒስታን ያሉ ዜጎችን በሄሊኮፕተር እያስወጡ እንዳሉ ዎል ስትሪት ጆርናል ዘግቧል።
ፔንታገን 10 ሺህ ሰዎች አሁንም በአሜሪካ በረራዎች አፍጋኒስታንን ለቀው ለመውጣት እየተጠባበቁ ቢሆንም ወደ ካቡል አየር ማረፊያ ሊደርሱ አልቻሉም ብሏል።
የቢቢሲ ምንጮች ወደ ካቡል አየር ማረፊያ እንዳይገቡ በታሊባን የተከለከሉ ሰዎች ተገቢውን ሰነድ ይዘው ነበር ይላሉ።
ካቡል አየር ማረፊያ በአሁኑ ወቅት በ5800 የአሜሪካ ወታደሮችና በ1 ሺህ የብሪታኒያ ኃይሎች እየተጠበቀ ይገኛል።