ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ታሊባን ሥራ ያላቸው ሴቶች ቤታቸው እንዲቀመጡ አዘዘ
በመላው አፍጋኒስታን በተለያዩ የሥራ መስኮች ተሰማርተው የሚገኙ ሴቶች ደህንነታቸውን የሚያረጋግጡ ትክክለኛ ሥርዓቶች እስከሚዘረጉ ድረስ በቤታቸው መቆየት አለባቸው ሲሉ የታሊባን ቃል አቀባይ ተናገሩ።
የታሊባን ቃል አቀባይ ዛቢሁላህ ሙጃሂድ "ይህ በጣም አስፈላጊ አሰራር ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።
ከ20 ዓመታት በፊት ታሊባን አፍጋኒስታንን በሚያስተዳድርበት ወቅት ጥብቅ የእስልምና ሕግን ተግባራዊ ያደርግ ነበር።
ታሊባን ሴቶች ትምህርት ቤቶች እንዳይሄዱ እንዲሁም ተቀጥረው እንዳይሰሩ ክልከላዎችን ይጥል ነበር።
የተባበሩት መንግሥታት ታሊባን በሴቶች ላይ ያደረሳቸውን በደሎች በተለይ በሴቶች ላይ የተጣሉ ገደቦችን በተመለከተ "ተዓማኒ" መረጃዎች እንደደረሱት ይፋ አድርጓል።
"የሴቶች መብት መሰረታዊ ቀይ መስመር ነው" ሲሉ የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባቼሌት ትናንት ማክሰኞ በጄኔቫ በተመድ የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
የታሊባን ቃል አቀባይ ሙጃሂድ በመግለጫቸው "የፀጥታ ኃይሎቻችን ሴቶችን የሚመለከቱ ጉዳዮችን እንዴት እንደሚይዙ እና ከሴቶች ጋር እንዴት እንደሚነጋገሩ አልሰለጠኑም" ብለዋል።
"የተሟላዋ የጸጥታ ሃይል መዋቅር እስከሚኖረን ድረስ ሴቶች በቤታቸው እንዲቆዩ እንጠይቃለን" ሲሉም አሳስበዋል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው የአፍጋኒስታን ዜጎች አገራቸውን ጥለው ለመውጣት የሚያደርጉትን ጥረት እንዲያቆሙ አሳስበዋል።
ዜጎች ወደ አየር ማረፊያ ያሚያደርጉትን ጉዞም እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
የተመድ የሰብአዊ መብቶች ሃላፊዋ ባችሌት በአፍጋኒስታን የሴቶች መብትን በተመለከተ ስጋታቸውን ከገለጹ በኋላ ህፃናት ለውትድርና እየተመለሙ እንደሆነ ሪፖርት እንደደረሳቸው ተናግረዋል። እንዲሁም ሰዎች ያለምንም የፍርድ ሂደት ስለመረሸናቸው ተናግረዋል።
በዚሁ ጉዳይ ስብሰባውን ያካሄደው የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት "ለሴቶች እና ለሴቶች መብቶች የማይናወጥ ቁርጠኝነት" ያሳያል ያለውን የውሳኔ ሃሳብ በማጽደቅ ተቐጭቷል።
ነገር ግን የውሳኔ ሃሳቡ ብዙ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በጠየቁት መሰረት በተለይ ለአፍጋኒስታን ልዩ የተባበሩት መንግስታት መርማሪ ሳይሾም ቀርቷል።