ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
51 የአፍጋኒስታን ስደተኞች ኡጋንዳ ሲደርሱ በመቶዎች የሚቆጠሩት ደግሞ ወደ ሩዋንዳ እያመሩ ነው
ታሊባን አፍጋኒስታን መቆጣጠሩን ተከትሎ በርካቶች እየተሰደዱ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ 51 የሚሆኑ ተፈናቃዮች ኡጋንዳ በዛሬው ዕለት ደርሰዋል።
የኡጋንዳ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ቡድኑ ረቡዕ ጠዋት በግል ቻርተር በረራ ተሳፍሮ ኢንተቤ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ማረፋቸውን አሳውቋል።
ሚኒስቴሩ ቡድኑ በኡጋንዳ ለተወሰነ ጊዜ እንደሚቆይ ገልፆ የመጨረሻ መዳረሻቸው ወደ አሜሪካ እና ወደ ሌሎች አገራት እንደሚሆን አስታውቋል።
ስደተኞች በኡጋንዳ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆዩ አልተገለፀም።
ተፈናቃዮቹ የኮቪድ -19 ምርመራ ያደረጉ ወንዶች ፣ ሴቶችን እና ሕፃናትን ያካተቱ ሲሆን ወደ ለይቶ ማቆያ እንደሚገቡ መግለጫው አክሎ አስታውቋል።
ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ ቀውሱን የሸሹ ሰዎችን ኡጋንዳ እንድስታተናግድ የአሜሪካ መንግሥት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት ነው ወደ ዩጋንዳ እየገቡ ያሉት፤
ባለፈው ሳምንት አንድ የኡጋንዳ ባለስልጣን 2 ሺህ ያህል የአፍጋኒስታን ስደተኞችን እንደምትወስድ ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።
ነገር ግን በርካታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በኋላ በጉዳዩ ላይ ውይይቶች እንደቀጠሉ ተናግረዋል።
ኡጋንዳ ከምስራቅ አፍሪካ በርካታ ግጭቶችን እና ሌሎች አደጋዎችን የሸሹ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ስደተኞችን ታስተናግዳለች።
በተያያዘ ዜና ሩዋንዳም ከአፍጋኒስታን ወደ ሌላ ቦታ የሚዛወሩ በርካታ ተማሪዎችን ልትቀበል መሆኑም ተገልጿል።
በአፍጋኒስታን የግል ይዞታ የሆነው ሶላ የአመራር ትምህርት ቤት መስራች ሻባና ባሲጅ ረሺክ ማክሰኞ እንዳስታወቁት 250 የሚሆኑ ተማሪዎች ፣ ሠራተኞች እና የቤተሰብ አባላት በኳታር በኩል ወደ ሩዋንዳ በመጓዝ ላይ ናቸው ብለዋል።
"የአሁኑንም መንፈቀ ዓመት በሩዋንዳ በመማር ማስተማሩ ያሳልፋሉ" በማለትም ተናግረዋል።
የሩዋንዳ ትምህርት ሚኒስቴር ለሶላ መምህራንና ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት በትዊተር ገፁ አስፍሯል።
መስራቿ እንደተናገሩት በሩዋንዳ በጊዜያዊነት ለመቆየት ተስፋ እንዳደረጉ እና ሁኔታው በሚፈቅድበት ጊዜ ወደ አፍጋኒስታን ለመመለስ እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።
በማህበራዊ ትስስር ገፃቸውም "በሃገሬ ልቤ ተሰብሯል" በማለት አስፍረዋል።
አክለውም "ካቡል ውስጥ ሆኜ የአፍጋኒስታን ህዝብ ፍርሃትን ፣ ንዴትን እና በጀግንነት የተሞላውን መንፈሳቸውን አይቻለሁ። ተማሪዎቼን ስመለከት እና ልክ እንደነሱ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በአፍጋኒስታን ያሉ ታዳጊ ሴቶችን ፊት አየሁ።" ብለዋል
ከአውሮፓውያኑ 2001 በፊት አፍጋኒስታንን ሲመሩ ጥብቅ የእስልምና ሕግን ተግባራዊ ያደረጉት ታሊባኖች ከሳምንት በፊት አገሪቱን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዋል።