በህወሓት ኃይሎች ቁጥጥር ስር በምትገኘው ትግራይ ሕይወት እንዴት ቀጥሏል?

በትግራይ ክልል የመብራት፣ የስልክ፣ የኢንተርኔት፣ የባንክና የትራንስፖርት አገልግሎቶች ከተቋረጡ ሁለት ወር ሆኗቸዋል።

የትግራይ ታጣቂዎች ባለፈው ሰኔ ወር ላይ የክልሉ ዋና ከተማ የሆነችውን መቀለ ተቆጣጠሩ የሚሉ ወሬዎች በሚሰራጩበት ወቅት ነበር የመብራት አገልግሎት የተቋረጠው ይላሉ ነዋሪዎች።

በተመሳሳይ ቀን የፌደራል መንግሥት የተናጠል ተኩስ አቁም በማወጅ ከከተማዋ ጀምሮ ከተለያዩ የትግራይ አካባቢዎች እንደወጣ ሲገልጽ ሁሉም የመሰረታዊ አገልግሎቶች ተቋርጠዋል።

ከዚያ ጊዜ በኋላ በክልሉ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ለማወቅ የሚያስችል መረጃ ማግኘት በእጅጉ አስቸጋሪ ሆኗል።

አንዳንድ ግለሰቦች ግን የስልክ ኔትዎርክ ማግኘት ወደ ሚችሉበት የአፋር አካባቢ ጠጋ በማለት እንዲሁም በአንዳንድ የረድኤት ተቋማት ጽህፈት ቤቶች ኢንተርኔት በሚያገኙ ሰዎች በኩል ቢቢሲ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ የተወሰነ መረጃ ለማግኘት ሞክሯል።

በፌደራል መንግሥቱና የትግራይን ክልል ያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ቅራኔዎች ተባብሰው ወደ ጦርነት ከማምራታቸው በፊት በክልሉ የሚገኙ በርካታ የገጠርና የከተማ ነዋሪዎች በዋናነት የስልክ፣ የመብራትና የውሃ አገልግሎቶችን ያገኙ ነበር።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም በክልሉ በተጀመረው ጦርነት ምክንያት እነዚህ አገልግሎቶች በበርካታ አካባቢዎች በመቋረጣቸው ነዋሪዎች ለችግር መጋለጣቸውን ይናገራሉ።

በክልሉ የተለያየ አካባቢ የሚኖሩ እንዲሁም ከክልሉ ውጪ ካሉ ዘመድ ወዳጆቻቸው ጋር ለመገናኘትም ሆነ ሥራቸውን ለመከወን መቸገራቸውን ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ያስረዳሉ።

"ሰው ቤቱ ውስጥ ተዘግቶ በምግብ እጦት ሞተ ሲባል እንዳልሰማ እሰጋለሁ"

ሥራና ደሞዝ እንዲሁም በቂ የነዳጅ አቅርቦት ባለመኖሩ ህይወት እየከበደ፣ በአንዳንድ ሸቀጦች ላይም ከሁለት እጥፍ በላይ የዋጋ ጭማሪ እየታየ፣ የዕለት ተዕለት ኑሮ እጅግ አስቸጋሪ እየሆነ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

አሁን ላይ ሰዎች ምግብ ለማብሰል እንጨትና ክሰል እንደ አማራጭ እየተጠቀሙ መሆኑን የገለጹት ነዋሪዎቹ፣በዚህም ሳቢያ እንጨት በእጅጉ ተወዷል።

ዘይት ሌላው ከፍተኛ ጭማሪ የታየበት ሸቀጥ ሲሆን ምግብ ቤቶች በሚያቀርቧቸው ምግቦች ላይ ጭማሪ አድርገዋል።

ስሜ አይጠቀስ ያለች አንዲት ነዋሪ ለቢቢሲ በሰጠችው ቃል፣ አንድ ሊትር ዘይት 200 ብር እንደሚሸጥ፣ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ7ሺ ብር በላይ፣ አንድ ሊትር ነዳጅ ደግሞ በ500 ብር እየተሸጠ ነው ብላለች።

አሁን ላይ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት በመኖሩ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ታክሲዎች እንደማያመሹ፣ መብራት ባለመኖሩ ደግሞ ሱቆች በጊዜ ስለሚዘጉ ከተማዋ ቶሎ ጭር እንደምትል ያስረዳሉ።

ምግቦች ላይ ባለው ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ እና የገንዘብ እጥረት ምክንያት፣ ሰዎች እርስ በእርሳቸው በመተጋገዝ ኑሮ እየገፋ መሆኑን ገልጻ፣ "የሚላስ የሚቀመስ ያጡም አሉ" ትላለች።

"ወጥ አጥተው ደረቅ እንጀራ የሚበሉ ጎረቤቶች አሉኝ። ገንዘብ እየተላከላቸው ሲኖሩ የነበሩ ጧሪ የሌላቸው ሰዎች ገንዘብ ማግኘት ስላልቻሉ ብዙዎች ለችግር ተጋልጠዋል። በግማሽ እንጀራ የምታድር ነፍስ ይዘን ነው እንግዲህ ኑሮ እየገፋን ያለነው። ሰው በቤቱ ተዘግቶ በምግብ እጦት ሞተ ሲባል እንዳልሰማ እሰጋለሁ" በማለት ያለውን ሁኔታ ታስረዳለች።

ምላዛት፣ የመቀለ ነዋሪዎች ስልክ የሚደውሉባት አካባቢ

ነዋሪዎች ከትግራይ ክልል ውጪ ካሉ የቤተሰብ አባሎቻቸው ወይም ጓደኞቻቸው ጋር በቀጥታ መገናኘት ስለማይችሉ ከከተማ በመውጣት፣ ደቡባዊ ዞን ስር ወደ ሚገኙ አንዳንድ አካባቢዎች ወይም ከአፋር ክልል ጋር ወደ ሚዋሰኑ ቦታዎች በመሄድ ስልክ ይደውላሉ።

በሌላም በኩል በውጪ ድርጅቶች ለሚሰሩ ሰዎች መልዕክት እንዲያደርሱላቸው አጭር የጽሁፍ መልዕክት ወይም ድምጻቸውን ቀድተው በመስጠት እንደሚያስልኩ ይናገራሉ።

አንድ ስሙን እንዳይጠቀስ የጠየቀ የመቀለ ዩኒቨርሲቲ ሠራተኛ ይሄንን በማድረግ ጎረቤቱንና ጓደኞቹን እያገዙ ካሉ ሰዎች መካከል እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጿል።

"ለወራት ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ያልቻሉ ሰዎች አሉ፤ አልፎ አልፎ ኢንተርኔት ወደ ማገኝበት ቦታ ስሄድ 'እኛ ደህና ነን፤ ደህና ናችሁ ወይ?' የሚለውን መልዕክት ከብዙ በቅርብ የማውቃቸው ሰዎች ይዤ እሄድና፤ ተመልሼ በየቦታው እየዞርኩ መልስ አደርሳለሁ። ምን እናድርግ ታድያ?" በማለት ያሉበት ሁኔታ ከባድ እንደሆነ ይጠቅሳል።

ምላዛት፣ አሁን ብዙ የመቀለ ከተማ ነዋሪዎች ወጣ ብለው ስልክ የሚደውሉባትና 'ደካማ ነው' ብለው የሚገልጹት የስልክ ኔትዎርክ የሚደርስባት አካባቢ ናት።

ይህች ስፍራ ከመቀለ ከተማ በ30 ኪሎ ሜትር ርቀት በምሥራቅ በኩል የምትገኝ ስትሆን፣ በአፋር ክልል ያለው የስልክ ኔትዎርክ የሚደርሳት ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ዳዊት ግርማይ በዚህ መንገድ ውጪ አገር ለሚኖረው ታናሽ ወንድሙ ስልክ ለመደወል ሁለት ቀን ተመላልሶ እንደቀናው ገልጿል።

"አካባቢው ላይ በሚገኘው ሰፊ ቦታ ብዙ ሰው ተቀምጦምና ቆሞ ስልክ ሲሞክር ይታያል። አብዛኛው ሰው አንድ ስልክ ለመደወል ግማሽ ቀን ይጠብቃል። ሰው ስለሚበዛ መሰለኝ ኔትዎርኩ ደካማ ነው። እኔ ስምንት ሰዓት ጠብቄ ሲሰራልኝ 'ወንድሜ፤ እኛ ደህና ነን' ብዬው ተመለስኩ" ይላል።

በዚህ አካባቢ አለ የሚባለው የስልክ ኔትዎርክ እንዲሰራ ረጅም ሰዓታት እንደሚወስድ፣ ብዙ ሰዎች ከፍ ወዳሉ ቦታዎች እየወጡ ስልክ እንደሚሞክሩ፣ ሄደውም ሳይቀናቸው የሚመለሱ እንዳሉ ዳዊት ለቢቢሲ አስረድቷል።

"ይሄንን ሁሉ መስዋዕትነት የሚከፈለው ለአንድ አላማ ነው፤ በቃ 'ደህና ነን . . . አትጨነቁ' ከማለት ውጪ ሌላ ነገር ማውራት አይቻልም። ስልኩም መቼ እንደሚሰራ ስለማይታወቅ በሄድንበት ጊዜ ላይሳካም ይችላል። የቤተሰቦቻችን ድምጽ መስማት ደስ ስለሚለን እንጂ ቀላል ሆኖ አይደለም" ሲል የጸጥታው ሁኔታም ቀላል እንዳልሆነ ያስረዳል።

አሁን ብዙ አካባቢው ላይ የስልክ ኔትዎርክ አለ መባሉን የሰሙ ሰዎች ወደ ቦታው ይመላለሳሉ፤ አቅም የሌላቸውም ለሚሄድ ሰው 'መልዕክት አድርስልኝ' ብለው ይልካሉ።

ከዚህ ውጪ የባንክ አገልግሎት ዝግ በመሆኑ ገንዘብ መቀበልና መላክ አይቻልም፤ መብራትም ስለሌለ አብዛኛው ሥራ ቆሞ ቡና ቤቶች ተቀምጠው እንደሚያሳልፉ ይገልጻሉ።

በውቅሮ፣ አጉላዕ ከተሞች የሚኖሩ ሰዎችም በተመሳሳይ ከጎረቤት ክልል አፋር ወደ ሚዋሰኑ አካባቢዎች ጠጋ ብለው፣ ከፍታ ቦታ ፈልገው ስልክ ለመደወል ጥረት እንደሚያደርጉ ይነገራል።

ይህ የስልክና ኢንተርኔት እንዲሁም የባንክ አገልግሎት ችግር ክልሉ ላይ ለሚንቀሳቀሱ የሰብአዊ እርዳታ ሰጪ ተቋማትና ሠራተኞችም ትልቅ ችግር እንደሆነ ይነገራል።

በዚህም ሳቢያ ዓለም አቀፍ ተቋማት በክልሉ የተቋረጡትን የስልክ፣ የኢንተርኔት፣ የመብራትና የባንክ አገልግሎቶች ወደ ሥራ እንዲመለሱ እየጠየቁ ነው።

ህወሓት በበኩሉ እነዚህ አገልግሎቶች ጨምሮ የፌደራል መንግሥት "ትግራይ ላይ የጣለውን እቀባ [ብሎኬድ]" እስኪያነሳ የተኩስ አቁም ስምምነት እንደማያደርግ ገልጿል።

ባለፈው ሳምንት ይሄንን ጉዳይ ያነሳንላቸው የኢትዮ-ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ፍሬህይወት ታምሩ በግጭቱ ምክንያት የወደመው የቴሌኮም መሰረተ ልማት በመጠገን ደንበኞቻቸው አገልግሎት የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ እየጠበቁ እንደሆነ ገልፀዋል።

"አሁን አካባቢው ላይ ግጭት አለ፤ ከዚህ በፊት የተሻለ ሁኔታ ሲፈጠር ቀድመን ገብተን አገልግሎት መስጠታችን ይታወቃል። አሁን ግን ግጭቱ ከክልሉ ወጥቶ ሌላ ችግር ተፈጥሯል። በዚህ ሁኔታ ሥራ መስራት አንችልም። ስለዚህ ደንበኞቻችን አገልግሎት እንዲያገኙ ሁኔታዎች እስኪሻሻሉ እየጠበቅን ነው" የሚል መልስ ሰጥተዋል።

የፌደራል መንግሥት በበኩሉ ቀደም ሲል የተናጠል የተኩስ አቁም አዋጅ በማድረግ ሠራዊቱን ከክልሉ ቢያስወጣም ህወሓት የሚያደርሰውን ጥቃት በመቀጠል ቀውሱን አባብሶ ጦርነቱ ወደ አፋርና አማራ ክልሎች እንዲገባ አድርጓል ሲል ይከስሳል።

ሰሞኑን ከቢቢሲ ሃርድቶክ ቆይታ ያደረጉት የኢትዮጵያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ዶክተር ጌድዮን ጢሞቲዎስ መንግሥት በትግራይ የመሰረታዊ መአገልግሎቶች መቋቀረጥን በተመለከተ ሲናገሩ ጥገና በሚሰሩ ሠራተኞች ላይ ጥቃት ተፈጽሞ እንደሚገደሉ ተናግረዋል።

"ህወሓት በሠራተኞች ላይ የሚፈጽመው ጥቃት እየቀጠለ ባለበት ሁኔታ ደግሞ ሥራውን መስራት አይቻልም። ያቀረብነው የተኩስ አቁም አዋጅ ቢቀበል ኖሮ አሁን ሁኔታዎች ይቀየሩ ነበር" ብለዋል።

በፌደራል መንግሥቱ ሽብርተኛ ቡድን ተብሎ የተሰየመው ነገር ግን የትግራይ ሕጋዊ አስተዳዳሪ ነኝ የሚለው ህወሓት በበኩሉ እነዚህ አገልግሎቶች ሆነ ተብሎ በመንግሥት እንደተቋረጡና ይህንንም ለማስከፈት ጦርነቱን እንደሚቀጥል ይናገራል።

'ላለፉት ዘጠኝ ወራት ራ ፈትቻለሁ'

ፊልሞን ብርሃነ ኢንተርኔት ላይ መሰረት ያደረጉ የግል ሥራዎችን በመስራት የሚተዳደር ወጣት ነው።

ይኹሁ እንጂ ላለፉት ዘጠኝ ወራት በክልሉ የኢንተርኔት አገልግሎት በመቋረጡ ሥራ እንዳቆመ ይናገራል።

ስልክም ባለመኖሩ በቀጠሮ እንኳን ለመገናኘት አስቸጋሪ መሆኑን "ከቀጠርኩት ሰው ጋር ግማሽ ቀን ስንፈላለግ ነው የምንውለው" በማለት ሰዎች በፈለጉት ሰዓት መገናኘት እንደማይችሉ ገልጿል።

ለዚህ ደግሞ እሱና ጓደኞቹ ለሥራ ይሁን ለሻይ መገናኘት ሲፈልጉ ቀድመው መልዕክት የሚያስቀምጡባት 'የመረጃችን ማዕከል' የሚሏት አንዲት ካፌ መርጠው መልዕክት እንደሚለዋወጣና ቀጠሮ እንደሚይዙ ያስረዳል።

የአብዛኛው ነገር ከመብራት፣ ከስልክና ከኢንተርኔት አገልግሎቶች ጋር የተያያዘ ነው የምትለው ወይዘሪት ሳሌም አብዛኛው ሥራ እንደቆመ ትናገራለች።

'ፖሊስ ወይም ትራፊክ የለም'

የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት በጥቅምት ወር መቀለን ጨምሮ ትግራይን በተቆጣጠረበት ወቅት ለሰባት ወራት ሰዓት እላፊ ተጥሎ ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስም ተገድቦ ነበር።

የትግራይ ኃይሎች አብዛኛውን የክልሉ አካባቢዎች ከተቆጣጠሩበት በኋላ ግን ይህን የሰዓት እላፊ እንደተነሳ አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ።

ከሁለት ወር በፊት በግጭቱ ምክንያት ከቦታ ቦታ መንቀሳቀስ ከባድ የነበረ እንደሆነ የምትናገረው ሳሌም አሁን ግን አብዛኛው አካባቢ 'ጥሩ እንቅስቃሴ አለ' በማለት ትገልጻለች።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ መቀለ ትልቅ የጸጥታ ችግር የሚታይባትና ከፍተኛ የስርቆት ወንጀል ያስቸግረናል ሲሉ ነዋሪዎቿ ሲገልጹ ቆይተዋል።

አሁን በአንጻሩ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳለ ያነጋገርናቸው ሰዎች ቢገልጹም፤ በተጨባጭ ሁኔታው ምን እንደሚመስል ቢቢሲ ማረጋገጥ አልቻለም።

ሳሌም ግን "አሁን ስለ ስርቆት ከሰማሁ ረዥም ጊዜ ሆኖኛል፤ ፖሊስ የለም - ግን ስለ ስርቆት አልሰማሁም። በመንገድ ላይም ትራፊክ አላየሁም። ሁሉም ሰው ለራሱ ሲል ኃላፊነት የወሰደ ይመስላል" አለች።