ፊፋ የአፍጋኒስታን ሴት እግር ኳስ ተጫዋቾች ከአገሪቷ እንዲወጡ እንዲደረግ ጠየቀ

የአፍጋኒስታን እግር ኳስ ቡድን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ፌዴሬሽን ማኅበር (ፊፋ) የአፍጋኒስታን እግርኳስ ሴት ተጫዋቾች ከአፍጋኒስታን በአስቸኳይ እንዲወጡ በሚል ለተወሰኑ መንግሥታት ደብዳቤ ፅፏል።

ታሊባን የአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ካቡልን መቆጣጠሩን ተከትሎ ተጫዋቾቹ ለሕይወታቸው ሰግተዋል ተብሏል።

የተጫዋቾች ማህበር ፊፍፕሮ ለእርዳታ ጥሪ እያቀረበ ይገኛል።

ማህበሩ ተጫዋቾቹ ከአገሪቱ የሚወጡበትን መንገድ ለመቀየስም ከተለያዩ መንግሥታት ጋር እየሰራ መሆኑን የገለጸ ሲሆን "ዋናው ፍላጎታችን በተቻለ መጠን በርካቶችን ደህንነታቸው በተጠበቀ መልኩ ማስወጣት ነው" ብሏል።

የአፍጋኒስታን ሁኔታ "ያልተረጋጋ እና በጣም አሳሳቢ ነው" ሲል ፊፋ ተናግሯል።

የቀድሞ የአፍጋኒስታን ብሄራዊ የሴቶች ቡድን አምበል ካሊዳ ፖፓል በበኩሏ በታሊባን አገዛዝ ስር ያሉ ሴት ተጫዎቾች ለከፍተኛ አደጋ ይጋለጣሉ በሚልም ለተለያዩ የስፖርት አካላት ደህንነታቸውን በመጠበቅ እንዲያግዙ ተማፅናለች።

ታሊባን አፍጋኒስታንን መቆጣጠሩን ተከትሎ በርካቶቹ የአገሪቱ ሴት እግርኳስ ተጫዎቾች ለህይወታቸው በመፍራት ተደብቀው ይገኛሉ ተብሏል።

በአውሮፓውያኑ 2007 የመጀመሪያውን የአፍጋኒስታን የሴቶች እግር ኳስ ቡድን በማቋቋም ረገድ ወሳኝ ስፍራ የነበራት ካሊዳ እንደተናገረችው " መተኛት አልቻልኩም፤ እስካሁን እያለቀስኩ ነው እናም አቅመ ቢስነት ተሰምቶኛል" ብላለች።

ታሊባን ከ20 አመታት በፊት በነበረው የቀድሞ አገዛዝ ዘመናቸው ሴቶች ማንኛውንም ትምህርት እንዳያገኙ ከልክለዋል።

ሴቶች ያለ ወንድ አጃቢነት ከቤታቸው መውጣት አይችሉም፤ መሥራት አይፈቀድላቸውም እንዲሁም መላ አካላቸውን የሚሸፍን ቡርቃ እንዲለብሱ ይገደዱ ነበር።

እነዚህን ህጎች የጣሱ ሰዎች ቅጣት እንዲሁም ድብደባ ይደርስባቸው ነበር።

የአፍጋኒስታን የሴቶች ቡድን የቀድሞ ረዳት አሰልጣኝ ሃሌይ ካርተር ከተደበቁት በርካታ ተጫዋቾች ጋር ግንኙነት መፍጠር ከቻሉት መካከል ይገኙበታል።

አሰልጣኟ ለቢቢሲ እንደተናገሩት " ከውጭ ሰው ጋር እየተነጋገሩ መሆናቸው ከታወቀ ህይወታቸው የበለጠ አደጋ ላይ ነው።" ብለዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ የባህር ኃይል ሰራተኛ በበኩላቸው አንዲት ተጫዋች"ሊገድሉን ነው። ሴቶች እግር ኳስ እንዲጫወቱ አይፈልጉም እናም እኛ አደጋ ላይ ነን" የሚል መልእክት እንዳደረሰቻቸው ገልጸዋል።

የፊፋ ቃል አቀባይ ባወጡት መግለጫ "ከአፍጋኒስታን እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር እየተነጋገርን ነው በአገሪቱ ያሉ ተጫዋቾች ያሉበትንም ሁኔታ በዚሁ መንገድ መከታተላችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።