ከጂቡቲ ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ ሲከፈት የባቡር መስመሩ እንደተዘጋ ነው ተባለ

የባቡር መስመር

የፎቶው ባለመብት, AFP

ከቀናት በፊት በተቃዋሚዎች ተዘግቶ የነበረው ከጂቡቲ ወደ መሃል አገር የሚወስደው መንገድ መከፈቱ ተገለጸ።

ጂቡቲን ከአዲስ አበባ የሚያገናኘው የባቡር መስመር ግን አሁንም ዝግ ሆኖ እንደሚገኝ የሶማሌ ክልል ኮምዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊ መሐመድ ሮብሌ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ካሳለፍነው እሁድ ጀምሮ መንገዱና የባቡር መስመሩ በሶማሌ ተወላጆች ላይ የደረሰውን ጥቃት በሚቃወሙ የአካባቢው ወጣቶች ተዘግቶ ነበር።

መንገዱ ከጂቡቲ ወደብ ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ የተለያዩ ሸቀጦች ዋነኛ መተላለፊያ መስመር ነው።

ባለፈው ቅዳሜ በአፋር እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ በሆነና የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳበት ቦታ በተፈፀመ ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአፋር ታጣቂዎች መገደላቸውን የሶማሌ ክልል ኮምዩኒኬሽን ምክትል ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

በዚህ ጥቃት የተበሳጩ የሶማሌ ክልል ተወላጆች መንገዱን እና የባቡር መስመሩን መዝጋታቸውን ተከትሎ፤ የተዘጉትን የመንገድ እና የባቡር መስመር ለማስከፈት "ከወጣቶቹና ከሕዝቡ ጋር እየተወያየን ነው። መንገዱና የባቡር መስመሩ እንዲከፈት እየሠራን ነው" ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ መሐመድ ለሮይተርስ በአጭር የጽሑፍ መልዕክት ምላሽ ሰጥተው ነበር።

ትናንት ለቢቢሲ ቃላቸውን የሰጡት የክልሉ ኮሚኒኬሽን ምክትል ኃላፊ፤ ከአገር ሽማግሌዎች እና ከወጣቶች ጋር በተደረገው ንግግር መንገዱ ከሐሙስ ጠዋት ጀምሮ የተከፈተ ሲሆን፤ በባቡር መስመሩ ላይ ግን ጉዳት በመድረሱ እስካሁን አገልግሎት አልጀመረም ብለዋል።

በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ የተለቀቁ ፎቶዎች እና ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተቃዋሚዎች የባቡር መስመሩን እና ዋና አውራ ጎዳናውን በድንጋይ እና በአፈር ዘግተው አሳይተው ነበር። የባቡር ሃዲዱ ብሎኖችም ተፈተው ታይቷል።

መንገዱ እና የባቡሩ መስመሩ ስለመዘጋቱም ይሁን ስለመከፈቱ እስካሁን ድረስ የፌደራሉ መንግሥት ያለው ነገር የለም።

ከዚህ ቀደም በሶማሌ እና በአፋር ክልል መካከል የይገባኛል ጥያቄ በሚነሳባቸው ቦታዎች በተደጋጋሚ ግጭቶች መነሳታቸው አይዘነጋም።

ቅዳሜ ዕለት ደረሰ ስለተባለው ጥቃት ከአፋር ክልል በኩል መረጃ ለማግኘት ቢቢሲ ወደተለያዩ የክልሉ ባለሥልጣናት ስልክ በተደጋጋሚ ቢደውልም ምላሽ ማግኘት አልተቻለም።