የቱኒዚያው ፕሬዚዳንት መፈንቅለ መንግስት ሊያካሂዱ አስበዋል ተባለ

ተቃዋሚ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የቱኒዚያ የፖለቲካ ፓርቲዎች ፕሬዚዳንቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከስልጣን በማባረር እና በኋላም ፓርላማው ላይ እገዳ በመጣል መፈንቅለ መንግስት ለማካሄድ አስበዋል አሉ።

ፕሬዚዳንቱ በበኩላቸው በሕገ-መንግስቱ መሠረት እርምጃ እንደወሰዱ ተናግረዋል።

ባሳፍነው እሁድ መንግስት የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር እየወሰደ ያለውን እርምጃ፣ የኢኮኖሚ እና ማህበራዊ ቀውሶችን በማውገዝ የተካሄደውን ሰፊ የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ ነበር እርምጃው የተወሰደው።

ሰኞ ረፋድ ላይ ከስልጣን የተሰናበቱት ጠቅላይ ሚኒስቴር ሂቼም መቺቺ ስልጣናቸውን በፕሬዚዳንቱ ሰኢድ ለሚሾም ለማንኛውም ሰው አስረክባለሁ ብለዋል ። አክለውም "የሚያውኩ አካላትን" ሚና መጫወት እንደማይፈልጉ ተናግረዋል ።

የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊከን ከቱኒዚያው ፕሬዘዳንት ጋር ትናንት በስልክ ባደረጉት ውይይት "ከሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች እና ከቱኒዚያ ህዝብ ጋር ግልፅ ውይይት እንዲኖር" አሳስበዋል ሲል ጽህፈት ቤታቸው አስታውቋዋል ።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት "ሁሉም አለመግባባቶች በውይይት መፈታት አለባቸው" ሲል የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ወገኖች ሁሉ የሕግ የበላይነትን እንዲያከብሩ እና ሁከትን እንዲያስወግዱ ጥሪውን አቅርቧል ።

የአረብ ሊግ፣ ሩሲያ እና ኳታርም ተመሳሳይ ጥሪዎችን አሰምተዋል።

በፕሬዚዳንቱ ደጋፊዎች እና ተቃዋሚዎች መካከል የተፈጠረው ግጭት በዋና ከተማዋ ቱኒዝ ሰኞ ዕለትም ቀጥሎ ውሏል ።

ሁለቱ ወገኖች በፓርላማው አካባቢ ድንጋይ ሲወራወሩ የታዩ ሲሆን ወታደሮች ፓርላውን ከበው ሲጠብቁ ታይተዋል።

እ.ኤ.አ. በ 2019 የተመረጠጡት ፕሬዚዳንቱ አቶ ሳይድ በፓርላማው ትልቁን ፓርቲ መቀመጫ ያለው ፓርቲ ድጋፍ ካላቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ አቶ መቺቺ ጋር የቆየ ፀብ አላቸው።

ፕሬዚዳንቱ የመከላከያ እና የፍትህ ሚኒስትሮችንም ከስልጣን አሰናብተዋል ።

እ.ኤ.አ. በ 2011 የፈነዳው የቱኒዚያ አብዮት የአረብ ስፕሪንግ ብቸኛ ስኬት ተደርጎ ይወሰዳል - ነገር ግን በኢኮኖሚም ሆነ በፖለቲካዊ ሁኔታዎች እስካሁን መረጋጋት አልመጣም ።

በቅርቡ የታየው ከፍተኛ የኮቪድ ስርጭት ለረዥም ግዜ ሲብላላ የቆየውን የሕዝብ ቁጣ ቀስቅሷል ። የጤና ጥበቃ ሚኒስትሩ በክትባት ዘመቻ ተጠምደው ባሉበት ባለፈው ሳምንት ከሥራ ተባረዋል ።

እሁድ እለት በመላው ቱኒዚያ በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በጠቅላይ ሚኒስትሩ እና በለዘብተኛው እስላማዊ ፓርቲ እናዳ ላይ የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል ። ፓርቲው በምክር ቤት ከፍተኛ መቀመጫ ያለው ነው።

በደቡብ ምዕራብ በምትገኛው የቱዜር ከተማ የሚገኘው የፓርቲው የአከባቢው ዋና መስሪያ ቤትም በእሳት ጋይቷል።

ፕሬዚዳንቱ በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር ‹‹በቱኒዚያ ሰላም እስኪመለስ እና አገሪቱን እስከምናተርፍ ድረስ እነዚህን ውሳኔዎች ወስደናል›› ብለዋል ።

ከዚህ በኋላ ለሚኖሩ አመፆችም ወታደራዊ ምላሽ እንደሚሰጡ አስጠንቅቀዋል።

ሰኞ ማለዳ ፓርላማው አፈ ጉባኤ ራሺድ ጋኖቺ የፓርላማ አባትን ለማነጋር ጥረት ሲያደርጉ በፕሬዘዳንቱ ደጋፊዎች ታግደዋል። አፈ ጉባኤው እና ታማኝ ተከታዮቻቸው ቁጭ በማለት ተቃውሟቸውን አስተጋብተዋል።

ሰኞ ለትም ለእናዳ ፓርቲ ያደላል ተብሎ የሚታሰበው አልጀዚራ ቴሌቪዥንም በቱኒዝ የሚገኙ የፀጥታ ኃይሎች ቢሮውን እንደበረበሩ ብሎም መሳሪያዎቹን እንደለቃቀሉ እና ሰራተኞቹ ለቅቀው እንዲወጡ በመጠየቅ በቱኒስ የሚገኙትን ቢሮአቸውን መውረራቸውን ገልጿል።