ቤርሙዳ የመጀመሪያ ወርቅ ስታገኝ ናኦሚ ኦሳካ ከኦሊምፒኩ በጊዜ ተሰናበተች

ናኦሚ ኦሳካ እና ደፊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

63,000 ህዝብ ብቻ የሚኖርባት ቤርሙዳ በፍሎራ ደፊ አማካይነት በቶኪዮ ኦሊምፒክ የትሪያትሎን አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ ያገኘች ትንሿ ግዛት ሆናለች።

የ33 ዓመቷ ተወዳዳሪ ለአራተኛ ጊዜ በተሳተፈችበት ኦሊምፒክ 56 ሴት ተወዳዳሪዎችን በመቅደም አንድ ሰዓት ከ55 ደቂቃ ከ 36 ሰከንድ በመግባት አሸንፋለች።

የትሪያትሎን ውድድር የውሃ ዋና፣ የሳይክል እና የረዥም ርቀት ሩጫ ውድድርን አጣምሮ የያዘ ፈታኝ ውድድር ነው።

ቤርሙዳ እአአ በ 1976 ቦክሰኛው ክላረንስ ሂል በበጋ የኦሊምፒክ የነሐስ ሜዳሊያ በማግኘት አነስተኛ የሕዝብ ብዛት ያላት አገር በመሆን ሪኮርዱን ቀደም ብላ ይዛ ነበር። አሁን ግን ሜዳሊያው ወደ ወርቅ ከፍ ብሏል።

"ለአምስት ዓመታት ለኦሊምፒክ አሸናፊነት በጭራሽ አልታጨሁም ነበር። በእርግጥ አሁን ሁሉንም ነገር ዋጋ እንዲሰጠው አድርጎታል" ብላለች ደፊ።

"ቤርሙዳ በሙሉ እየተደሰተ ነው ብዬ አስባለሁ። ይህ ለእኔ ልዩ የሚያደርገው ነገር ነው። ይህ የእኔ ህልም ነበር ግን ደግሞ ከእኔ እንደሚበልጥም አውቃለሁ" ስትል ሃሳቧን ገልጻለች።

ጃፓናዊቷ የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ናኦሚ ኦሳካ በአገሯ ከሚካሄደው የኦሊምፒክ ውድድር በቼኳ ማርኬታ ቮንድሩሶቫ ተሸንፋ በመሰናበት አስደንጋጭ ውጤት አስመዝግባለች።

የ23 ዓመቷ ኦሳካ በጃፓን ዋና ከተማ ቶኪዮ የሚደረገው ውድድር መገለጫ የተደረገች ሲሆን ባለፈው ሳምንት ውድድሩ ሲከፈት የመክፈቻ ሥነ ሥርዓቱን የኦሊምፒክ ችቦን በማብራት የማስጀመር ክብር አግኝታ ነበር።

የአራት ጊዜ ግራንድ ስላም ሻምፒዮኗ በሦስተኛው ዙር ውድድር በዓለም ቁጥር 42ተኛዋ የሜዳ ቴኒስ 2 ለ 0 በሆነ ውጤት ተሸንፋ ሜዳሊያ ማግኘት ሳትችል ቀርታለች።

"እንደማስበው ምናልባት ከዚህ በፊት በኦሊምፒክ ስላልተካፈልኩ እና የመጀመሪያው ዓመት ስለሆነ ትንሽ ጫና ስለነበረ ነው" ስትል ናኦሚ ኦሳካ ተናግራለች።