በልደት ዝግጅት ላይ አልተጠራሁም ያለው ፍቅረኛውን ጨምሮ 6 ሰዎችን ገደለ

በጥቃቱ ዘመዶቻቸውን ያጡ የቤተሰብ አባላት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጥቃቱ ዘመዶቻቸውን ያጡ የቤተሰብ አባላት

በአሜሪካዋ ኮሎራዶ ግዛት ፍቅረኛውን ጨምሮ ስድስት ሰዎችን የገደለው ግለሰብ ድርጊቱን የፈጸመው በልደት ዝግጅቱ ላይ አልተጠራሁም በሚል ምክንያት መሆኑን ፖሊስ አስታወቀ።

ባሳለፍነው እሁድ የ28 ዓመት ወጣቱ ቲዎዶር ማኪአስ በልደት ዝግጅቱ ላይ ሲታደሙ የነበሩ ስድስት ሰዎችን ተኩሶ ከገደለ በኋላ እራሱን አጥፍቷል።

ሟቾቹ የ28 ዓመት ፍቅረኛው ሳንድራ ኢብራ-ፔሬዝ እና ዘመዶቿ ናቸው ብሏል ፖሊስ።

ሰኞ ዕለት የኮሮሎራዶ ስፕሪንግ ፖሊስ "ግለሰቡ መጀመሪያ እያሽከረከረ ወደ ቦታው መጣ። ራሱን ከማጥፋቱ በፊት በልደት ዝግጅቱ ላይ እየታደሙ የነበሩ ሰዎች ላይ በዘፈቀደ ተኩስ ከፈተ" ሲል ገልጾ ነበር።

ፖሊስ እንደሚለው ጥቃቱን ያደረሰው ወጣት ከአንድ ሳምንት በፊት ከፍቅረኛው ቤተሰብ አባላት ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ ነበር። "ቅናተኛ ፍቅረኛ ነበር" የተባለው ወጣት፤ በልደት ዝግጅቱ ላይ ባለመጋበዙ ተኩስ በመክፈት ምላሽ ሰጥቷል ሲሉ የአከባቢው የፖሊስ አዛዥ ቪንስ ኒስኪ ተናግረዋል።

ወጣቱ ተኩሶ ከገደላት ፍቅረኛው ጋር ለአንድ ዓመት ያክል በፍቅር መቆየታቸውን እና ከዚህ ቀደም የወንጀል ሪኮርድ እንደሌለበት ፖሊስ ጨምሮ አስታውቋል።

የጥቃቱ ሰለባዎች በሙሉ አዋቂዎች ቢሆኑም በድግሱ ላይ ግን ህፃናትም ታድመው ነበር። "በድግሱ ላይ ህጻናት ታድመው የነበረ ቢሆንም ከመሃላቸው ማንም አልተጎዳም" ብሏል ፖሊስ።

ጥቃቱ ሲደርስ በስፍራው የነበሩ የ2፣ 5 እና የ11 ዓመት እድሜ ያላቸው ልጆች ምንም አይነት አካላዊ ጉዳት አልደረሰባቸውም።

የሟቾች ቤተሰብ የሆነችው ኑቢያ ማርኬዝ ለኮሎራዲ ስፕሪንግስ ጋዜጣ ስትናገር ከሟቾቹ መካከል ሶስቱ በተመሳሳይ ሳምንት ልደታቸውን እንደሆነና ሁሌም አብረው እንደሚያከብሩ ገልጻለች።

ፖሊስ እንደሚለው ጥቃት አድራሹ የተጠቀመው ሽጉጥ በሕጋዊ መንገድ የተመዘገበ አይደለም።

የኮሎራዶ አስተዳዳሪ ዕሁድ ዕለት ባወጡት መግለጫ ላይ ''በጣም የሚያሳዝን ጥቃት ነው። ሁላችንም የእናቶችን ቀን ለማክበር ደፋ ቀና በምንልበት ወቅት ጥቃቱ መፈጸሙ አሳዝኖኛል'' ብለዋል።