ኮሮናቫይረስ፡ ወረርሽኙን ተከትሎ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች የተበራከቱባት ጃፓን

ጃፓን ከየትኛውም ዓለም በፈጠነና ትክክለኛ በሆነ መልኩ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን መረጃ በአግባቡ ትመዘግባለች።
ከሌሎች አገራት በተለየ መልኩ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች መረጃ በየወሩ እየተጠናቀረ ይቀመጣል። በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ወቅት ደግሞ ይህ መረጃ በጣም አስፈሪ ታሪኮችን ይፋ አድርጓል።
2020 ላይ ከ11 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር በጣም ከፍ ብሏል። በሚያስገርም ሁኔታ ደግሞ የወንድ ሟቾች ቁጥር በትንሹም ቢሆን የቀነሰ ሲሆን ራሳቸውን የሚያጠፉ ሴቶች ቁጥር ደግሞ 15 በመቶ ጨምሯል።
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በአንድ ወር ውስጥ ብቻ ከዛ በፊት በነበረው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ራሰቸውን የሚያጠፉ ሴቶች ቁጥር 70 ከመቶ በላይ ጭማሪ አሳይቶ ነበር።
በጃፓን ምን እየሆነ ነው? የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከወንዶች በተለየ ሴቶችን ለምን ራሳቸውን እንዲያጠፉ አደረጋቸው?
ማስጠንቀቂያ፡ አንዳንድ አንባቢያን ይህ ጽሁፍ ሊያስደነግጣቸው ይችላል?
በተደጋጋሚ እራሷን ለማጥፋት የሞከረችን ሴት በአካል አግኝቶ ማውራት ከባድ ነገር ነው ይላል የቢቢሲው የቶክዮ ዘጋቢ ሩፐርት ዊንግፊልድ።
ያየውን እንዲህ ይገልጻል. . .
ሰዎች ራሰችውን እንዳያጠፉ መከላከል ላይ የሚሰሩ ሰዎችን በጣም እንዳደንቃቸው አድርጎኛል።
በዮኮሀማ ሬድ ላይ ዞን ውስጥ በሚገኝ በዚሁ ጉዳይ ላይ የሚሰራ ለትርፍ ያልተቋቋመ ድርጅት ውስጥ ነው የምገኘው። ከፊልት ለፊቴ አንድ የ19 ዓመት ወጣት ተቀምጣለች። ምንም አይነት ስሜት አይታይባትም።
ቀስ ብላ የግል ታሪኳን ታጫውተኝ ጀመር። ነገሩ የጀመረው የ15 ዓመት ታዳጊ ሳለች ነበር። በወቅቱ ታላቅ ወንድሟ ቀላል የማይባል አካላዊ ጥቃት ይፈጽምባት ነበር። በመጨረሻ ከቤት ጠፍታ ለማምለጥ ወሰነች። ነገር ግን ብቸኝነቱንና ህመሙን መቋቋም አልቻለችም።
የታያት የመጨረሻ አማራጭም ራሷን ማጥፋት ነበር።
''ከባለፈው ዓመት ወዲህ በተለያዩ ጊዜያት ሆስፒታል ስገባና ስወጣ ነበር የቆየሁት'' ትላለች። ''ብዙ ጊዜ ራሴን ለማጥፋት ሞክሬያለው ነገር ግን ሊሳካልኝ አልቻለም። ምናልባት አሁን ተስፋ በመቁረጥ ራሴን ለማጥፋት መሞከር ትቻለሁ።''
ራሷን ለማጥፋት ከመሞከር እንድትቆጠብ ያደረጋት ደግሞ በጎ አድራጎት ድርጅት ውስጥ ያለው 'ቦንድ' የተሰኘው ፕሮግራም ነው። ደህንነቱ የተጠበቀ መኖሪያ ቦታ አግኝተውላታል፤ በተጨማሪም ተገቢውን የአእምሮ ጤና ክትትል እንድታገኝ ረድተዋታል።
ጁን ታቺባና የቦንድ ፕሮጀክት መስራች ነች። በ40ዎቹ የእድሜ ክልል ውስጥ የምትገኝ ጠንካራ ሴት ናት።
''ሴቶች በተለይ ታዳጊ ሴቶች ችግር ውስጥ ሲገቡና ስነ ልቦናዊ ህመም ሲሰማቸው በትክክል ምን ማድረግ እንዳለባቸው አያውቁም። እኛ እዚህ ያለነው የእነሱን ችግር ለመስማት ነው። መፍትሄ ለመስጠትና ችግራቸውን ለመጋራት'' ትላለች።
ጁን እንደምትለው የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መጀመሪያውኑ ችግር ያለባቸውንና ተጋላጭ የሆኑ የማህበረሰብ ክፍሎችን በጣም ጎድቷል።
በፕሪጀክቱ ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች በወረርሽኙ ወቅት እጅግ አስፈሪና አሳዛኝ የስልክ ጥሪዎችን እንዳስተናገዱም ታስታውሳለች።
''ብዙ ጊዜ መሞት እፈልጋለሁ አልያም ምንም አይነት የምሄድበት ቦታ የለኝም የሚሉ ጥሪዎች ይደርሱናል። በጣም የሚያም ነገር እንደሆነ ይነግሩናል። አንዳንዶቹም ብቸኝነት እንደሚሰማቸውና መጥፋት እንደሚፈልጉ ነው የሚገልጹት።''
ከዚህ በፊት አካላዊና ጾታዊ ጥቃት ይደርስባቸው የነበሩ ሰዎች ደግሞ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ነገሮችን ይበልጥ አስከፊ አድርጎባቸዋል።
''በአንድ ወቅት አንዲት ታዳጊ ደውላ በአባቷ ጾታዊ ጥቃት እየደረሰባት እንገሆነ ገልጻ ነበር። በኮሮናቫይረስ ምክንያት አባትየው ለስራ ብሎ ከቤት ስለማይወጣ በየቀኑ ይህንን አሳዛኝ ጥቃት መጋፈጥ ነበረባት።''
በጃፓን ከዚህ በፊት የነበሩትን ቀውሶች ስንመለከት ለምሳሌ በአውሮፓውያኑ 2008 አጋጥሞ በነበረው የባንክ ዘርፋ ቀውስ ወይም በ1990ዎቹ አካባቢ በነበረው የአክስዮን ገበያ መውደቅ ምክንያት በርካታ ጃፓናውያን በተለይ አዋቂ ወንዶች በእጅጉ ተጎድተው ነበር።
በነዚህ ጊዜያት ራሳቸውን የሚያጠፉ ወንዶች ቁጥር በጣም ከፍ ብሎ ነበር።
ኮቪድ-19 ግን የተለየ ነገር ነው። የወረርሽኙ መዘዝ በዋነኛነት ወጣቶችን በተለይ ደግሞ ወጣት ሴቶችን እያጠቃ ይገኛል። ምክንያቶቹ ደግሞ የተወሳሰቡ ናቸው።
ጃፓን ከዚህ በፊትም ቢሆን ካደጉት አገራት ጋር ስትወዳደር ከፍተኛውን ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ታስተናግድ ነበር። ባለፉት አስር ዓመታት ደግሞ አገሪቱ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችን ቁጥር በአንድ ሶስተኛ መቀነስ ችላለች።
ፕሮፌሰር ሚቺኮ ኡዌዳ በጃፓን በዙዳዩ ላይ ቀዳሚ የሚባሉ ተመራማሪ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በጃፓን ባለፉት ቅርብ ወራት ውስጥ ብቻ የታየው ራሰቸውን የሚያጠፉ ሰዎች ቁጥር መጨመር በእጅጉ የሚያስደነግጥ ነው።
''በተለይ ደግሞ ሴቶች ራሳቸውን እያጠፉ ያሉበት አካሄድ ያልተለመደና አሳሳቢ ነው። በዚሁ ጉዳይ ላይ ጥናት ማካሄድ ከጀመርኩበት ጊዜ አንስቶ እንዲህ አይነት ቁጥር ተመልክቼ አላውቅም። ምናልባት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በእጅጉ ካዳከማቸው ዘርፎች መካከል እንደ ቱሪዝም፣ ችርቻሮ ንግድና ምግብን የመሳሰሉት ሴቶች በብዛት የሚሰማሩባቸው መሆናቸው እንደ ምክንያት ሊወሰድ ይችላል'' ይላሉ ፕሮፌሰሯ።
በጃፓን ሌላው ቀርቶ ብቻቸውን የሚኖሩ ሴቶች ቁጥር እየጨመረ ሲሆን፤ ዋነኛ ምክንያታቸው ደግሞ ትዳርን ሽሽት ነው። ብቻቸውን ሲኖሩ ደግሞ ከማህበረሰቡ የሚደርስባቸውን ጫና መቋቋም በጣም ከባድ ነገር ነው።
''በርካታ ወጣት ጃፓናውያን ሴቶች አላገቡም። ቤተሰቦቻቸውንም የሚረዱት እነሱ ናቸው። በርካታዎቹ ደግሞ ቋሚ ስራ የሌላቸው ሲሆን በወረርሽኙ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጫና መገመት ቀላል ነው።
ባለፈው ዓመት ጥቅምት ወር ላይ ብቻ በጃፓን 879 ሴቶች ራሳቸውን አጥፍተዋል። ከዛ በፊት ከነበረው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር ደግሞ ቁጥሩ 70 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
ጃፓን በአሁኑ ሰአት ሶስተኛው ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ላይ ትገኛለች። መንግስትም ለሁለተኛ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ እንዲሆን አዟል። እስከሚቀጥለው ወር ድረስ ሊቀጥል እንደሚችልም ይገመታል።
በርካታ ሆቴሎችና ሬስቶራንቶች በራቸውን እየዘጉ ሲሆን በዚሁ ምክንያትም በርካቶች ስራቸውን እንዳጡ ነው።
ራስን ማጥፋት ውስብስብ ከመሆኑ የተነሳ እንዲሁ በቀላሉ መፍትሄ መዘርዘር የሚቻል አይደለም።
ትልቁና ተመራጩ መፍትሄ ግን ተግባቦትን ማጠናከር ነው። ሰዎች ስለ ሕይወታቸው እንዲያወሩ ማድረግ፣ የሚደገፉበትን ትከሻ አለመንፈግ፣ ሙሉ ጆሮ እና ጥሞናን መስጠት።
ሌላው ሊዘነጋ የማይገባው ነገር፤ ሰዎች ራስን የማጥፋት መዘዝ ለሌላውም እንደሚተርፍ ማወቅ አለባቸው። ራስን አለማጥፋት ምርጫ እንደሆነ ማሳየት ባለሙያዎች የሚመክሩት አንዱ የመፍትሄ ሃሳብ ነው።
ሰዎች ራሳቸውን ሲያጠፉ ወዳጅ ዘመዶቻቸው ላይ ትቶ የሚያልፈውን ጠባሳ ማስተዋል፤ ሃሳቡ ያላቸው ሰዎች ቆም ብለው እንዲያጤኑ ያደርጋል።
በበርካታ ሃገራት እራስን ማጥፋት የመኪና አደጋ ከሚያደርሰው በላይ ጥፋት ያደርሳል። ነገር ግን ለመኪና አደጋ የሚሠራውን ያህል ግንዛቤ ስለ ለራስ ማጥፋት አይሠራም።
አንዳንድ ቦታዎች ራስ ማጥፋትን በተመለከተ ምክር የሚሰጡና የሚሠሩ ተቋማት መመሥረታቸው እንደ በጎ ጅምር እየታየ ነው። ለምሳሌ እንግሊዝ የራስ ማጥፋት መከላከል ሚኒስቴር አላት። የችግሩ መጠንም በትንሹ መቀነስ አሳይቷል።












