ምንጭ- 6768 ለአካል ጉዳተኞች የተዘጋጀ የመረጃ ማዕከል

የፎቶው ባለመብት, Education Images
ኢትዮጵያ ሴንተር ፎር ዲሴቢሊቲ ኤንድ ዴቨሎፕመንት (ኢሲዲዲ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ ነው የተባለ እና ለአካል ጉዳተኞች መረጃ የሚሰጥ 6768 የነጻ ጥሪ ማዕከል ማቋቋሙን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ መላኩ ተክሌ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ይህ ምንጭ የተሰኘ አሳታፊ የሆነ የድምጽ መልእክትን የሚያደርስ (IVR) የስልክ የመረጃ ማእከል ሲሆን፤ በኢትዮጲያ ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት መስጠት የጀመረ የመረጃ ማእከል መሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
የዚህ የመረጃ ማእከል ዋና አላማ ከአካል ጉዳት ጋራ የተያያዙ አስፈላጊ በድምጽ የተዘጋጁ መረጃዎችን ለአካል ጉዳተኛው እና ለተቀረው ማህበረሰብ ማቅረብ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ አካል ጉዳተኞች ጥያቄ ቢኖራቸው ወይንም ማካፈል የሚፈልጉት ልምድ ካለ ድምጻቸውን ቀርፀው መላክ እንደሚችሉ አቶ መላኩ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ይህ አገልግሎት ከኢትዮ ቴሌኮም ጋር በመተባበር የሚሰራ መሆኑንም ኃላፊው አክለዋል።
ይህንን የአጭር የስልክ ቁጥር ኢትዮ ቴሌኮም በነጻ እንደሰጠና ሰርቨሩ ኢትዮ ቴሌኮም ዳታ ማዕከል ውስጥ መቀመጡን አክለው ተናግረዋል።
እኤአ በ2011 የዓለም ባንክ እና የዓለም ጤና ድርጅት ባወጡት መረጃ መሰረት ከአለም ሕዝብ 15 በመቶ ያህሉ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ወደ 17.6 በመቶው የሕብረተሰብ ክፍል የአካል ጉዳተኛ ነው።
ይህ የነጻ አገልግሎት በሙከራ ደረጃ ነው ያለው ያሉት ኃላፊው፤ ለጊዜው አገልግሎቱ በአማርኛ ቋንቋ ብቻ መጀመሩን በመግለጽ፤ በቀጣይ በሌሎች የአገሪቱ ቋንቋዎች እንደሚሰጡ አስረድተዋል።
በኢትዮጵያ መረጃ ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ አይደለም የሚሉት አቶ መላኩ በርካታ የመረጃ ተደራሽነት ክፍተት መኖሩንም ይጠቁማሉ።
አገልግሎቱን ለማግኘት በማንኛውም ዓይነት ስልክ መደወል እንደሚቻል እንዲሁም ኢንተርኔት እንደማያስፈልግ ኃላፊው ጨምረው አስረድተዋል።
አቶ መላኩ፤ ወደዚህ የጥሪ ማዕከል እንደ ሌሎች የጥሪ ማዕከሎች ተገልጋዮች ሲደውሉ የስልክ ኦፕሬተሮች ወይንም ባለሙያዎች አንስተው መልስ የሚሰጡበት አለመሆኑንን ይናገራሉ።
ተጠቃሚዎች በሚደውሉበት ወቅት ከመጀመሪያ ጊዜ ደዋዮች አጠቃላይ መረጃ እንደሚወስድም ጨምረው ተናግረዋል።
ይህ መሰረታዊ መረጃ ስለተጠቃሚዎች በማወቅ ወደፊት ሥራውን ለማስፋት በማሰብ መዘጋጀቱን አቶ መላኩ ያስረዳሉ።
ይህ አስፈላጊ በድምጽ የተዘጋጁ መረጃዎችን የያዘው አገልግሎት ስምንት ክፍሎች እንዳሉት አቶ መላኩ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ወቅት ተናግረዋል።
ከአገልግሎቶቹ መካከልም ስለ አካል ጉዳተኞች በኢትዮጵያ ውስጥ ያለን አዲስ መረጃ መግለጽ፣ ስለ አካል ጉዳተኛነት ጠቅላላ መረጃ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ስለ አካል ጉዳተኞች ያሉ ሕጎች፣ አካል ጉዳተኝነት ምን ማለት እንደሆነ፣ ከአካል ጉደተኞች ጋር የሚሰሩ ምን ዓይነት ቋንቋ መጠቀም እንዳለባቸው የሚያስረዱ መረጃዎች መያዙን አብራርተዋል።
ሌላው ይህ የነጻ ጥሪ ማዕከል ስለ አካቶ ጤና ከሥነ ተዋልዶ፣ ተደራሽ ስለሆኑ የጤና ተቋማት እና ስለ ጾታዊ ጥቃት፣ ስለ አካቶ ትምህርት፣ ስለ አካቶ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና፣ ስለ ሥራ እና ሥራ ገበያ፣ የሥራ እድሎች መረጃ ይሰጣል ሲሉ ይናገራሉ።
የኢትዮጵያ ቴሌኮም አጋራቸው በመሆኑም ድርጅቱ ስለሚሰጣቸው አገልግሎቶች የሚያስተዋውቅ ክፍልም እንዳለው ጨምረው ተናግረዋል።
















