ኢንስታግራም 'ክብደት ጨማሪ ክኒን' በማስተዋወቁ ውግዘት ገጠመው

ኢንስትግራም ክብደትን የሚጨምሩ መድሃኒቶችን በሚያስተዋውቁ ተጠቃሚዎቹ ላይ እርምጃ እንዲወስድ ተጠየቀ።
ኢንስታግራም ወጣት ሴቶችን አላማ አድርገው ፍቃድ የሌላቸውና 'አደገኛ' የሆኑ ክብደት ለመጨመር የሚያግዙ መደሃኒቶችን የሚሸጡ ተጠቃሚዎቹን አደብ እንዲያስገዛ የእንግሊዝ ብሄራዊ የጤና አገልግሎት አሳሰበ።
'አፒታሚን' የተሰኘው የሰውነትን ክብደት የሚጨምር እንክብል በእንግሊዝ ምድር የታገደ ቢሆንም በበይነ መረብና ሱቆች ውስጥ እንደሚሸጥ ቢቢሲ 3 አጋልጧል።
እናም የሀገሪቱ የጤና አገልግሎት እንክብሎቹ ማስተዋወቅ አካላዊና አዕምሯዊ ጤንነት ላይ ያለውን ስጋት ይፋዊ በሆነ ደብዳቤ ገልፃል።
ኢንስታግራም ደግሞ ህመሞችን ለመፈወስ ከሚውሉ በስተቀር መድሃኒቶችን መሸጥ 'ከፓሊሲያችን ጋር በእጅጉ የሚቃረን ነው' ብሏል።
የምግብ ፍላጎትን በመጨመር የሰውነት ክብደትን የሚየጨምረው 'አፒታሚን' የጉበት ስራ ማቆምን ጨምሮ ለተለያዩ የጤና እክሎች እንደሚዳርግ የጤና ባለሙያዎች ያስረዳሉ።
ሆኖም ይህ መድሃኒት በርከት ያሉ ተከታዮች ባሏቸው የኢንስታግራም ተጠቃሚዎች በቋሚነት እየተዋወቀ ይገኛል ተብሏል።
ኢንስታግራም በበኩሉ ይህን መድሃኒት ያስተዋወቁና የሸጡ ተጠቃሚዎቹን አካውንት ዘግቻለሁ ሲል ይህንን ጉዳይ ላጋለጠው ቢቢሲ 3 ገልጿል።
ሆኖም የእንግሊዝ የጤና አገልግሎት በርከት ያሉ አካውንቶች አሁንም አሉ ያለ ሲሆን ሪፓርት ቢደረግም ኢንስታግራም እርምጃ አይወስድም ነበር ሲል ከሷል።













