ኮሮናቫይረስ፡ የኮንጎ ፕሬዝደንታዊ ዕጩ በኮቪድ-19 ምክንያት ሞቱ

ጋይ ብራይስ ፓራፊት ኮሌላስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጋይ ብራይስ ፓራፊት ኮሌላስ

በኮንጎ ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ይሳተፉ የነበሩት ዕጩ በኮቪድ-19 ምክንያት ሕይወታቸው አለፈ።

ጋይ ብራይስ ፓራፊት ኮሌላስ በኮንጎ-ብራዛቪል ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ላይ ከሚሳተፉ ዕጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

ሰውዬው ትላንት [እሑድ] በኮቪድ-19 ምክንያት ክፉኛ ከታመሙ በኋላ ሕይወታቸው አልፏል።

የሰውዬውን ሞት ያረጋገጡት የምርጫ ቅሰቅሳ ኃላፊያቸው ናቸው።

የምርጫ ቅስቀሳ ኃላፊው ኤኤፍፒ ለተሰኘው የዜና ወኪል እንደተናገሩት "ከብራዛቪል ወደ ሌላ ቦት ሕክምና እንዲያገኙ ሊወስዳቸው የመጣ የሕክምና አውሮፕላን ውስጥ ነው ሕይወታቸው ያለፈው።"

የ61 ዓመቱ ኮሌላስ ባለፈው አርብ ነበር በኮቪድ-19 መያዛቸው የተረጋገጠው።

ፕሬዝደንታዊ ምርጫዋን ባለፈው እሑድ ያከናወነችው ኮንጎ-ብራዛቪል ባለፈው አርብ የምርጫ ቅስቀሳ ማብቃቱን አውጃለች።

የ77 ዓመቱን ፕሬዝደንት ሳሱ ንጉዌሶን ለመተካት ከሚፎካከሩ ስድስት ዋነኛ ዕጩዎች መካከል አንዱ ነበሩ።

ጋይ ብራይስ ፓራፊት ኮሌላስ በተለምዶ የስኳር በሽታ ተብሎ የሚጠራው [ዳያቢቲስ] በሽታ ተጠቂ ናቸው።

እሁድ ዕለት የተከናወነው ፕሬዝደንታዊ ምርጫ ሰላማዊ ቢሆንም በርካቶች ድምጽ ያልሰጡበት ነበር ሲሉ ታዛቢዎች ተናግረዋል።

ከምርጫው አንድ ቀን ቀደም ብሎ ኮሌላስ ደከምከም ብለው እንዲሁም ኦክሲጅን ተደርጎላቸው ደጋፊዎቻቸው በነቂስ ወጥተው እንዲመርጡ ሲያሳስቡ ነበር።

የቀድሞው የኮንጎ-ብራዛቪል ጠቅላይ ሚኒስትር ልጅ የነበሩት ኮሌላስ የዓሳ ምርት እንዲሁም የሲቪል ሠራተኞች ሚኒስትር ሆነው አገልግለዋል።

የኮንጎ-ብራዛቪል የምርጫ ሕግ አንድ ዑጩ ቢሞት የምርጫ ውጤት አይቀየርም ይላል።

በአፍሪካ ሃገራት ዘንድ እንደ አዲስ እየተሰራጨ ያለው ኮቪድ-19 በርካታ ሰዎች መቅጠፍ ጀምሯል።

ከቀናት በፊት ሕይወታቸው ያለፈው የታንዛኒያው ፕሬዝደንት ጆን ማጉፉሊ በልብ ሕመም እንደሞቱ በይፋ ቢነገርም በኮቪድ-19 ምክንያት ሳይሆን አይቀርም የሚሉ በርካቶች ናቸው።