ፕሬዝዳንት ፑቲን የአሜሪካ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ እንዲደረግ አዝዘዋል ተባለ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የባለፈውን ዓመት የአሜሪካ ምርጫን ዶናልድ ትራምፕን በመደገፍ ተጽዕኖ እንዲደረግ ይሁንታቸውን ሳይሰጡ አልቀሩም ሲሉ የደኅንነት ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ሞስኮ ስለ አሸናፊው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን "አሳሳች እና መሰረተ ቢስ ውንጀላዎችን" ስታሰራጭ ነበር ተብሏል።
ነገር ግን የትኛውም የውጪ ኃይል የመጨረሻው ውጤት ላይ ተጽዕኖውን አላሳረፈም ሲል የአሜሪካ መንግሥት መረጃ ያስረዳል።
ሩሲያ በተደጋጋሚ በአሜሪካ ምርጫ ውስጥ ጣልቃ ለመግባት ትሞክራለች የሚለውን ውንጀላ ስታታጥል ቆይታለች።
በአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት መሥሪያ ቤት በኩል ማክሰኞ ዕለት ይፋ የተደረገው ባለ 15 ገጽ ሪፖርት በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ወቅት በሩሲያ እና በኢራን "ተጽዕኖ የማድረግ ዘመቻ" በሚል የተደረገ እንቅስቃሴ እንደነበር ያትታል።
በሪፖርቱ ላይ ከሩሲያ ጋር ግንኙነት ያላቸው ግለሰቦች ከምርጫው በፊት ስለ ፕሬዝዳንት ባይደን መሰረተ ቢስ ወሬዎችን ሲያናፍሱ እንደነበር ተገልጿል።
አክሎም በሰፊው የምርጫ ሂደት ላይ መተማመንን ለማሳጣት የሐሰተኛ መረጃ ዘመቻ ተከፍቶ ነበር ሲል ገልጿል።
ከሩሲያ የደኅንነት ተቋም ጋር ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ ግለሰቦች ለመገናኛ ብዙሃን፣ ለትራምፕ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና አጋሮቻቸው ፀረ ባይደን የሆኑ ትርክቶችን ሲያቀብሉ ነበር ሲል ሪፖርቱ ያስቀምጣል።
ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ዶናልድ ትራምፕን በማሸነፍ የአሜሪካ 46ኛው ፕሬዝዳንት ለመሆን በቅተዋል።
ሪፖርቱ አክሎም ሩሲያ የትራምፕን የማሸነፍ እድል ለማስፋት ጥረት ስታደርግ ኢራን በሌላ ወገን የትራምፕን ድጋፍ ለማሳነስ ዘመቻ ላይ ነበረች ብሏል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ "ከፍተኛ ግፊት" የሚያደርግ ፖሊሲን ተከትለው የነበረ ሲሆን ማዕቀቦችን በመጣል በሁለቱ አገራት መካከል የቃላት ጦርነት እንዲጦፍ ምክንያት ሆነዋል።
በሪፖርቱ ላይ በተደጋጋሚ የሳይበር ወንጀሎች በመፈፀም ስሟ የሚነሳው ቻይና ከምርጫው በፊት ምንም ዓይነት ዘመቻ ላለማድረግ ራሷን አቅባ እንደነበር ተጠቅሷል።
"ቻይና ከአሜሪካ ጋር ባላት ግንኙነት መረጋጋትን አሳይታ ነበር፤ የምርጫው ውጤት ለቻይና ጥቅም ያደላ እንዲሆን ምንም ዓይነት እርምጃ አላሳየችም" ይላል።
ሪፖርቱ የምርጫ ሂደቱም ሆነ የመጨረሻው ውጤት በውጪ ኃይሎች ጫና እንዳልተደረገበት አመልክቷል።
የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ሪፖርት ይፋ የተደረገው በዚሁ ጉዳይ ላይ የአገር ውስጥ ደኅንነት እና ፍትህ ቢሮዎች በጋራ የሰሩት ጥናትን ይፋ ባደረጉበት ወቅት ነው።
የአነዚህ ሁለት መሥሪያ ቤቶች ሪፖርት እንደሚለው ከሆነ "በሩሲያና ኢራን መንግሥታት በወሳኝ ተቋማት ላይ የተከፈተው ዘመቻዎች ምርጫን በሚመለከት የሚሰሩ ኔትወርኮችን ማጥቃት ሳይችል ቀርቷል።"
እነዚህ የተባሉ ጣልቃ ገብነቶች በሙሉ በተዘዋዋሪ የተፈፀሙ መሆናቸውንም ጥናቱ ጠቅሷል።
ሩሲያና ኢራን በምርጫው ላይ ጣልቃ በመግባት ተጽዕኗቸውን ማሳረፍ የፈለጉት የምርጫ ሂደቱን ቴክኒካዊ ሂደት፣ ድምጽ ቆጣራ፣ ድምጽ አሳጣጥ እና ውጤት ይፋ አደራረግ ላይ መሆኑን ከቢሮዎቹ የወጣው ሰነድ ያሳያል።
የአሜሪካ ደኅንነት ማኅበረሰብ ባለፈው ነሐሴ ወር ላይ ሩሲያ ዶናልድ ትራምፕ እንዲያሸንፉ ቻይናና ኢራን ደግሞ እንዲሸነፉ ዘመቻዎችን እያደረጉ ነው ሲሉ ይፋ አድርገው ነበር።












