የኡጋንዳ ምርጫ 2021፡ ኡጋንዳ በምርጫው ዋዜማ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ አደረገች

የኡጋንዳ ምርጫ ኮሚሽን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በዛሬው ዕለት ምርጫ በምታካሂደው ኡጋንዳ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ ከዋዜማው ጀምሮ እንዲቋረጥ መደረጉ ተገልጿል።

የኢንተርኔትን ሁኔታ በበላይነት የሚቆጣጠር ኔት ብሎክስ የተሰኘው ቡድን በትዊተር ገፁ እንዳስታወቀው ከትናንትና ምሽት አንድ ሰዓት ጀምሮ በመላው አገሪቱ ኢንተርኔት ሙሉ በሙሉ እንደተቋረጠ ነው።

ይህ የባለስልጣናቱ ኢንተርኔት የማቋረጥ ውሳኔም በቅርቡ የትኛውም የትኛውም አይነት ማህበራዊ ሚዲያዎች እንዲዘጉ የተላለፈውንም ይከተላል።

ፕሬዚዳንት ዩዌሪ ሙሴቪኑ እንዳሉት ፌስቡክ የፓርቲያቸውን ደጋፊዎች አካውንት እንዲታገድ በማድረጉ ይህ ውሳኔ እንደተላለፈ አስታውቀዋል።

በአፍሪካ ውስጥ ለረዥም ዘመናት ስልጣን ከተቆጣጠሩት አንዱ በሆኑት ዩዌሪ ሙሴቪኒና በታዋቂው ሙዚቀኛ ቦቢ ዋይን መካከል ከፍተኛ ፉክክር እንደሚጠበቅም እየተነገረ ነው።

ሙዚቀኛውና ለእጬ ፕሬዚዳንትነት የሚወዳደረው ቦቢ ዋይን በበኩሉ የኢንተርኔት መቋረጥ ምርጫውን የማጭበርበር አካልም እንደሆነ በትዊተር ገፁ አስፍሯል።

"የኡጋንዳ ህዝብ በከፍተኛ ፅናትና ውሳኔ ላይ ነው። ይህንን ጨቋኝ መንግሥትም ከስልጣን ለማውረድ የሚያግደው ኃይል አይኖርም" በማለትም አስፍሯል።

የምርጫ ጣቢያዎች በዛሬው ዕለት በአገሪቱ ሰዓት አቆጣጠር መሰረት ከጥዋቱ አንድ ሰዓት ጀምሮ የሚከፈቱ ሲሆን ውጤቱም እስከ ቅዳሜ ድረስ ይፋ እንደማይሆንም ተገልጿል።

አገሪቱ ዘንድሮ ልታካሂደው ያሰበችው ምርጫ ከፍተኛ ሁከቶችን አስተናግዷል። በተለይም በምርጫው ቅስቀሳ ወቅት በተነሱ አመፆችና ሁከቶች የበርካታ ሰዎች ህይወት ተቀጥፏል።

ለ35 አመታት በስልጣን ላይ የቆዩት ፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ለስድስተኛ ጊዜም አገሪቷን ለማስተዳደር ይወዳደራሉ።