የኡጋንዳ ምርጫ 2021፡ 40 ዓመት በሥልጣን ላይ መቆየት የሚፈልጉት መሪና የኡጋንዳ ምርጫ

የቦቢ ዋይን እና ሙሴቪኒ ፖስተሮች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የኡጋንዳው የፖፕ ኮከብ እና የተቃዋሚ ፓርቲ ፕሬዝዳንት የሆኑት እጩ ተወዳዳሪ ቦቢ ዋይን በዘንድሮው ምርጫ ይሳተፋሉ፡፡

ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቬኒ ከ35 ዓመታት የሥልጣን ጊዜ በኋላም ለስድስተኛ ጊዜ ለመመረጥ ይወዳደራሉ።

ስለኡጋንዳ ምርጫ ማወቅ ያለብዎት አምስት ነጥቦች እነሆ፡

1. 40 ዓመት በስልጣን መቆየት የሚፈልጉት ሰው

ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ በአፍሪካ ረዥም ጊዜ በስልጣን ከቆዩ ፕሬዝዳንቶች አንዱ ናቸው፡፡ እርሳቸው እና ናሽናል ሬዚስታንስ ሙቭመንት የተባለው ፓርቲያቸው ለአምስት ዓመት በቆየ ጦርነት ማብቂያ ላይ በጎርጎሮሳዊያኑ 1986 ወደ ስልጣን የመጡ ሲሆን ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኡጋንዳን እየመሩ ናቸው፡፡

ደጋፊያቸው አንጻራዊ ሰላምን እና ብልጽግናን በሀገሪቱ በማምጣት በተለይም በጤና ላይ በተከተሏቸው ፖሊሲዎች ያወድሷቸዋል፡፡ የኤች አይቪ ስርጭትን በመግታት እና በቅርቡም የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቋቋም ሠርተዋል።

እንደጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ዘገባ ከሆነ ኡጋንዳ ከ40,000 ያነሱ ዜጎቿ በቫይረሱ ሲያዙ 300 የሚሆኑት ብቻ ሞተዋል፡፡

በአንድ ወቅት በምዕራቡ ዓለም ከአዳዲሶቹ የአፍሪካ መሪዎች አንዱ ተብለው ቢወደሱም፣ ተቺዎቻቸው ወደ አምባገነን መሪነት ተለውጠዋል ሲሉ ይከሷቸዋል።

ሙሴቬኒ በፓርቲያቸው ውስጥ ተተኪ የሌላቸው ሲሆን በ2017 ደግሞ 75 የነበረውን የፕሬዚዳንቱን የዕድሜ ገደብ በማንሳት እንደገና ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር የሚያስችላቸውን ሕግ ፈርመዋል፡፡

2. ተፎካካሪው የሙዚቃ ኮከብ

ዘንድሮ ለፕሬዝዳንትነት ከሚወዳደሩት 10 ዕጩዎች መካከል ቦቢ ዋይን በመባል በመድረክ ስሙ የሚታወቀው ሮበርት ክያጉላኒይ ሴንታሙ ይገኝበታል፡፡

"የጌቶ ፕሬዝዳንት" ተብሎ በፍቅር የሚጠራው የ38 ዓመቱ ሙዚቀኛ በ 2000 ዎቹ መጀመሪያ የምስራቅ አፍሪካ የሙዚቃ ኮከብ ለመሆን በቅቶ በ2017 ደግሞ በየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ወንበር አሸናፊ ሆኗል፡፡

ቦቢ ዋይን ለሙሴቬኒ አገዛዝ ትልቁ ተግዳሮት ተደርጎ የሚወሰድ ሲሆን ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ውስጥ ያልተሳተፉ ብዙ ወጣቶችንም ማስተባበር ችሏል፡፡ ፕሬዚዳንቱን ከዚህ በፊት በከፍተኛ ደረጃ የተቸ ሲሆን "ህዝብን ይፈራሉ" ሲል ይከስሳል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ይህንን ፉክክር ቀለል አድርገው አልተመለከቱትም፡፡ ቦቢ ዋይንን "የዩጋንዳ መረጋጋትን እና ነፃነትን የማይወዱት" የውጭ ሃይሎች ወኪል እንደሆነ ሲከሱት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ወጣቶች በዘመቻው ወደ ሁከት እንዲገቡ እያሳሳቱ ናቸው ብለዋል፡፡

ቦቢ ዋይን በፖለቲካ ውስጥ ከገባበት ጊዜ አንስቶ ብዙ ጊዜ በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ በሙሴቬኒ ላይ "አብዮት" ያስፈልጋል ሲልም ተናግሯል ፡፡ ትዊተር ላይ "WeAreRemovingADictator" የሚል ሃሽታግም ተጠቅሟል፡፡

3. የትውልድ ክፍተት

የቦቢ ወይን ተወዳጅነት አንደኛው ምክንያት ዕድሜው ነው፡፡ 38 ዓመቱ ሲሆን ከፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ በግማሽ ያነሰ ነው፡፡

እንደ ሲ አይ ኤ ወርልድ ፋክትቡክ ዘገባ ኡጋንዳ በዓለም አቀፍ ደረጃ 15.7 በመያዝ ሁለተኛ ዝቅተኛ የመካከለኛ ዕድሜ ያላት ሃገር ስትሆን የምትበለጠው በኒጀር ብቻ ነው፡፡

"የጌቶው ፕሬዝዳንት" ያደገው በዋና ከተማዋ ካምፓላ ባለ የድሃዎች መንደር ውስጥ ነበር፡፡ አመጣጡ እና በሙዚቃው ማህበራዊ ፍትህ እንዲሰፍን ያደረገው ጥረት እንደ ፖለቲከኛ በከተሜው መካከል ተወዳጅ አድርጎታል፡፡

ቦቢ ዋይን ግን በገጠር አካባቢዎችም ብዙ ደጋፊዎችን በመሳብ ባለሥልጣናትን አስገርሟል። የገጠር አካባቢዎች ለፕሬዚዳንት ሙሴቬኒ የድጋፍ መሠረት ናቸው ተብሎ ይታሰባል፡፡

4. ኮቪድ-19ን መዋጋት

ውጥረቱ ከፍተኛ ሆኖ የምርጫ ዘመቻው ወቅት ከባድ ሁከት ተስተውሏል። በዚህም በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ደግሞ ለእስር ተዳርገዋል፡፡

ባለስልጣናት የፖለቲካ ስብሰባዎችን ለማስቆም ለሚያደርጉት ጥረት የኮቪድ -19 ወረርሽኙን ለመቋቋም የወጡ እርምጃዎችን በምክንያትነት ጠቅሰዋል፡፡ ሂውማን ራይትስ ዎች ግን የፀጥታ ኃይሎች እነዚህን መመሪያዎች "መብቶችን ለመጣስ እና ተቃዋሚዎችን እና ሚዲያዎችን ለማፈን በሰበብነት" እየተጠቀሙ ነው ሲሉ ከስሰዋል፡፡

ቦቢ ዋይን ራሱ ባለፈው ህዳር ወር የኮቪድ እርምጃዎችን ጥሷል በሚል በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ መታሰሩን በመቃወም በተነሳ ሁከት በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወት አልፏል፣ በአብዛኛው በፀጥታ ኃይሎች በጥይት ተመትተው መሞታቸው ተዘግቧል፡፡

የፀጥታ ሚኒስትሩ ኤሊ ቱምዋይን 11 የፀጥታ አካላት ጉዳት የደረሰባቸው መሆኑን ጠቁመው "ሁከቶች የተወሰነ ደረጃ ከደረሱ ፖሊሶች በጥይት የመምታት እና የመግደል መብት አላቸው" ብለዋል፡፡

"ልድገመው? ፖሊስ በጥይት የመምታት መብት አለው። እናም በከንቱ ትሞታለህ .... ኃላፊነቱ የራስህ ነው" ብለዋል።

ቦቢ ዋይን ከዚያን በኋላ በምርጫ ዘመቻ ወቅት የጥይት መከላከያ ጃኬትና የራስ ቆብ መከላከያ መልበስ ጀምሯል፡፡

5. የኡጋንዳ በቀጠናው እና ከዚያ ባሻገር ያላት ሚና

ከ42 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ያላት ሀገር ኡጋንዳ በኬንያ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በታንዛኒያ፣ በሩዋንዳ እና በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ተከብባለች፡፡

ከጎረቤት ሀገሮች ወደ 1.4 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን በማስተናገድ በዓለም ዙሪያ እጅግ ከፍተኛ ስደተኞች ከሚያስተናግዱ ሃገራት አንዷ ናት፡፡

አንዳንዶች በአገሪቱ ውስጥ የተፈጠረውን የፖለቲካ አለመረጋጋት በስጋት እየተመለከቱ ሲሆን፣ ከምርጫ በኋላ ምን ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ይጨነቃሉ፡፡ በኡጋንዳ ውስጥ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር ተደርጎ የማይታወቅ ሲሆን ሙሴቪኒ ቢሸነፉ ምን ሊፈጠር እንደሚችል እና ሠራዊቱ ምን እንደሚያደርግ ግልጽ አይደለም፡፡

ፕሬዚዳንቱ በህዳር ወር በሶማሊያ የቀድሞው የዩጋንዳ ኦፕሬሽን ኃላፊ የነበሩትን ሜጀር ጄኔራል ፖል ሎኬችን በምርጫ ወቅት በዋና ከተማዋ የፀጥታ ኃይሎችን እንዲያስተባብሩ የፖሊስ ምክትል ዋና ኢንስፔክተር አድርገው ሾመዋል፡፡

የአውሮፓ ሕብረት ዘንድሮ ታዛቢዎችን ወደ ምርጫው ላለመላክ መርጧል። ምከንያቱ ደግሞ የኡጋንዳ ባለሥልጣናት ምርጫው ይበልጥ ፍትሃዊ እንዲሆን ካለፉት ታዛቢዎች የተሰጠውን ምክር ችላ በማለታቸው ነው። ይህም ዓለም አቀፋዊ ቁጥጥሩ አነስተኛ ይሆናል ማለት ነው፡፡