ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ ቦቢ ዋይንን የኡጋንዳ ጠላት ሲሉ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዮዌሪ ሙሴቪኒ አስተዳደራቸውን በመተቸት የሚታወቀውን የቀድሞ ድምጻዊ የአሁን ፖለቲከኛ፣ ቦቢ ዋይንን "የሀገሪቱ ብልፅግና ጠላት" ሲሉ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ገለፁ።
የ36 ዓመቱ ድምጻዊና በደጋፊዎቹ ዘንድ "የምንዱባኖች ፕሬዝዳንት" ተብሎ የሚጠራው ቦቢ ዋይን፤ ከሁለት ዓመት በፊት የአገሪቱ ምክር ቤት አባል ሆኖ ከተመረጠ በኋላ ከፕሬዝዳንቱ ጋር አይንና ናጫ ሆኗል።
ቦቢ ዋይን እውነተኛ ስሙ ሮበርት ኪያጉላኒ ሲሆን፣ በ2021 ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒን ተፎካካሪ ሆኖ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደር ተናግሯል።
ቦቢ ዋይን የህዝቦች ኃይል የተሰኘ እንቅስቃሴ መሪ ሲሆን ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ የ33 ዓመት የሥልጣን ዘመን ጨቋኝ መንግሥት ሲመሩ ቆይተዋል ሲል ይከሳቸዋል።
ሙሴቪኒ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ይህንን ክስ ያጣጣሉ ሲሆን ቦቢ ዋይንን ግን በጠላትነት እንደሚመለከቱት ተናግረዋል።
"ቦቢ ዋይን አሜሪካ ሄዶ ባለሃብቶች ኡጋንዳ መጥተው ሀብታቸውን እንዳያፈሱ ተናገረ። ይህ ማለት የኡጋንዳ እድገት ጠላት ነው ማለት ነው። ወደ ባህር ማዶ ሄደህ ባለሀብቶች እንዳይመጡ ከቀሰቀስክ ብልፅግና ላይ ጦርነት ከፍተሃል ማለት ነው። ስለዚህ ስለምን መጥቶ የዚህ ብልፅግና ተቋዳሽ መሆን ይፈልጋል?" ሲሉ ተናግረዋል።
ቦቢ ዋይን የሙዚቃ ሥራውን እንዳያቀርብ ስለመከልከሉም ሲናገሩ "ከፖሊስ ጋር በዝርዝር በጉዳዩ ላይ ባላወራም ለዚያ [አሜሪካ ሄዶ ባለሃብቶች ወደ ኡጋንዳ እንዳይመጡ በመቀስቀሱ] ይመስለኛል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ሙሴቪኒ በኡጋንዳ በፕሬዝዳንትነት ማከናወን የሚፈልጓቸው በርካታ ነገሮች እንዳሉ ተናግረው ከስልጣን ሊወርዱ የሚችሉት በፓርቲያቸው ከተጠየቁ ብቻ መሆኑን ገልፀዋል።
"ቤቴ እየጠበቀኝ ነው፤ ነገር ግን እንደ ኡጋንዳዊ ገና የማከናውነው በርካታ ነገር አለኝ። . . . ፓርቲው የአንጋፋዎችን ድጋፍ አንፈልግም ብሎ ከወሰነ ለቅቀን ሌሎች ጉዳዮችን ለመከወን ደስተኞች ነን" ብለዋል።
ሙሴቪኒ አክለውም በኡጋንዳ ሥራ አጥ ወጣቶችን "እንደ ስጋት ሳይሆን እንደ እድል" እንደሚመለከቷቸውም ተናግረዋል።
ሙሴቪኒ በግብርናውና በኢንፎርሜሽነ ቴክኖሎጂ መስክ ገና ያልተነካ እድል እንዳለ ገልፀው ወጣቶች በዘርፉ ለመሰማራት መጣር እንዳለባቸውም መክረዋል።
"ሱፍ ለብሰው ቢሮ ለመዋል ብቻ ሳይሆን በግብርና፣ በኢንደስትሪ፣ በፋብሪካዎች፣ በአገልግሎት ሰጪው ዘርፍና በኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ላይ ለመሰማራት አእምሯቸውን ማዘጋጀት ይኖርባቸዋል፤ በእነዚህ መስኮች ሥራ ለመፍጠር ጠንክረን እየሰራን ነው" ብለዋል።


















