የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ ከየት ወደ የት?

የጎንደር ካርታ

የፎቶው ባለመብት, Google Earth

የቅማንት የማንነት ጥያቄ በተነሳባቸው አካባቢዎች በተለያዩ ጊዜያት ግጭቶች እየተፈጠሩ የሰው ህይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል። በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎችም ከመኖሪያ ቤታቸው ሲፈናቀሉ ቆይተዋል። ለመሆኑ የዚህ ሁሉ ምክንያት ምንድን ነው?

የቅማንት የማንነት ጥያቄስ በምን መልኩ ተጠይቆ ምን አይነት ምላሽ ተሰጠው? የቅማንት የማንነት ጥያቄ ከውልደት አሁን እስካለበት ደረጃ ድረስ ጉዞው ምን ይመስላል? ቢቢሲ ጉዳዩን በዝርዝር ተመልክቶታል።

ቅድመ -ቅማንት የማንነትና አስተዳደር ጥያቄ

የቅማንት ህዝብ በቀድሞው የጎንደር ክፍለ ሃገር፤ በአሁኑ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን በሚገኙ የተወሰኑ ወረዳዎች የሚኖር ህዝብ ነው። በተለይ በጎንደር ከተማ ዙሪያ በሚገኙ ላይ አርማጭሆ፣ ወገራና ጭልጋ ወረዳዎች ማህበረሰቡ በብዛት የሚኖርባቸው አካባቢዎች ናቸው።

ከ1983 ዓ.ም በፊት በነበረው የመንግሥት አወቃቀርም የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ ስላልነበር ብሔረሰቡ የጎንደር ክፍለ ሃገር አካል ሆኖ ከአማራው ህዝብ ጋር በብዛት ተቀላቅሎ ይኖር ነበር። የራሱ የተካለለ ልዩ አካባቢና አስተዳደርም እንዳልነበረውም መረጃዎች ያሳያሉ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ መነሻ?

ኢህአዴግ ስልጣን ከተቆጣጠረ በኋላ በኢትዮጵያ ቋንቋን መሰረት ያደረገ የብሔር ፌደራሊዝምን መሰረት ያደረገና ስልጣን በፌደራልና በክልሎች የተከፋፈለ ሥርዓት ተመሰረተ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ ይህ ሥርዓት ከሰፈነ በኋላ በ1984 ዓ.ም መነሳቱን በቅማንት ማንነት ዙሪያ ጥናት ያካሄዱት አቶ ቹቹ አለባቸው ያስረዳሉ።

"የቅማንት ብሔረሰብ ጥያቄ ከየት ወደየት-ከማንነት ጥያቄ እስከ የራስ አስተዳደር ጥያቄና የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ" በሚለው ፅሁፋቸው፤ ጥያቄው በቅማንት ህዝብም ተቀባይነት ያልነበረው ሲሆን ለግለሰቦቹ የተሰጣቸውም ምላሽ "የያዛችሁት ሐሳብ ከአማራ ወንድሞቻችን ጋር የሚያጋጭ ነው፣ ስለሆነም አንቀበላችሁም" የሚል እንደነበረ ጥናቱ ያሳያል።

በሕዝቡ ተቀባይነት ካጣ በኋላም ጥያቄው ለአስራ አምስት ዓመታት ያህል ተዳፍኖ ሳይነሳ መቆየቱን ይኸው ጥናት ያመላክታል። የ1999 ዓ.ም የሕዝብና ቤት ቆጠራ ግን አዲስ ክስተት ይዞ መጣ።

የማንነት ጥያቄ ባይነሳም በ1984 ዓ.ም በተካሄደው ሕዝብና ቤት ቆጠራ የቅማንት ሕዝብ በራሱ ተለይቶ 'ቅማንት' በሚል መለያ ኮድ እንደተቆጠረ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዋና የህግ አማካሪ አቶ መርሃ ጽድቅ መኮንን ይናገራሉ።

ነገር ግን ለብቻው ተለይቶ መቆጠሩ አልቀጠለም፤ በቀጣዩ 1999 በተካሄደው ሕዝብና ቤት ቆጠራ ግን ኮዱ ተሰርዞ 'አማራ ወይም ሌላ' በሚል የቅማንት ሕዝብ እንዲቆጠር መደረጉን ያስረዳሉ።

ይህ ሁኔታ ቅሬታን እንደፈጠረና ጥያቄዎችም መቅረብ መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ መርሃ ጽድቅ፣ በተለይም ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ የተለያዩ ግለሰቦች ማመልከቻ ይዘው ወደ ክልሉ መንግሥት መምጣት መጀመራቸውን ያስታውሳሉ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ይርሳው ቸኮልም በአቶ መርሃ ጽድቅ ሃሳብ ይስማማሉ። "ቅማንት ሆነን ሳለ ለምን 'ሌላ' ተባልን በሚል ተሰባስበን ጥያቄውን ጀመርን" ይላሉ።

የቅማንትን ሕዝብ አምስት በመቶ ድምጽ ማለትም 18500 ድምጽ ሰብስበው ማንነታቸው እንዲታወቅ ለክልሉ መንግሥት ጥያቄያቸውን ማቅረባቸውን አቶ ይርሳው ይጠቅሳሉ።

የቅማንት የማንነት ጥያቄ በተደራጀ መልኩ መቅረብ የጀመረው በዚህ ወቅት ነው።

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ማንነት ጥያቄ ምላሽ

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄንም ለመመለስ የክልሉ የርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት ጥናት እንዲጠና አድርጓል። የአቶ ቹቹ ጽሁፍ እንደሚያመለክተው በክልሉ መንግሥት አነሳሽነት በተቋቋሙ ኮሚቴዎች አማካኝነት ሁለት ጥናቶች በ2003 እና 2004 ዓ.ም ተደርገዋል።

ጥናቱም ሞዴል አድርጎ የወሰደው የአርጎባ ልዩ ወረዳ የማንነት ጥያቄ የተመለሰበትን መንገድ እንደነበር አቶ መርሃ ጽድቅ ያወሳሉ። የአርጎባ ጥያቄ በ1998 ዓ.ም ልዩ ወረዳ መሆን ይችላሉ በሚል ምላሽ ተሰጥቶታል።

የተጠናው ጥናትም በ2005 ዓ.ም ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡንም የሚናገሩት አቶ መርሃ ጽድቅ፤ ይህም በሰነድ ደረጃ የአማራ ክልል ምክር ቤት የቅማንት የማንነት ጥያቄን አስመልክቶ ውይይት ሲያደርግ ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑ ነው።

በሕገ መንግሥቱ መሰረት የማንነትና የራስ አስተዳደርን ጥያቄ ለመመለስ አምስት መስፈርቶች አሉ፤ እነዚህም የጋራ ባህል መኖር፣ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ መኖር፣ የአካባቢው ኩታ ገጠም መሆን፣ በሥነ ልቦናና ማንነት ለጠየቀው ብሔረሰብ አባል ነኝ ብሎ ማመንና የተዛመደ ህልውና መኖር ሲሆን፤ የአርጎባ ጥያቄም ምላሽ የተሰጠው እነዚህ መስፈርቶች በማሟላቱ እንደሆነም አቶ መርሃ ጽድቅ ያስረዳሉ።

ጥናቱንም መሰረት በማድረግ የቅማንት ጥያቄ "ማህበረሰቡ እንደ ማህበረስብ መኖሩ ተረጋግጦ እውቅና ቢሰጠውም የራሱን የውስጥ አስተዳደርና ነጻነት ለመመስረት ግን ሕገ መንግሥታዊ መስፈርቶችን አያሟላም" ተብሎ አደረጃጀቱ በክልሉ ምክር ቤት ውድቅ መደረጉን ይናገራሉ።

የማንነት ጥያቄው እንዲመለስ ሞዴል ከተደረገው የአርጎባ ልዩ ወረዳ ጋር ተቀራራቢነት የሌለው፤ የጋራ መግባቢያ ቋንቋ የሌለው በመሆኑና ኩታ ገጠም አሰፋፈር ስላልነበረው ጥያቄውን ለመመለስ የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ አካሄድ እንዳልነበረ አቶ መርሃ ጽድቅ ያስረዳሉ።

በምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ይህ ውሳኔም 174 የምክር ቤት አባላት የብሔረሰብ አስተዳደሩን መቋቋም ሲቃወሙ፣ ሰባት ደግፈውና 21 የምክር ቤቱ አባላት ድምጻቸውን በማቀባቸው ነው ውድቅ የተደረገው ይላሉ።

"'ይህ አካባቢ ያንተ ነው ራስህን አስተዳድር ለማለት የሚያስችል ሁኔታ አልነበረም። የራስ አሰተዳደሩን ለመወሰን የሚያስችል ሕገ መንግሥታዊ መስፈርቶች አልተሟሉም በማለት የራስ አስተዳደር ጥያቄው በክልሉ ምክር ቤት ውድቅ ተደርጓል" ይላሉ አቶ መርሃ ጽድቅ።

ከአማርኛ ጋር እየተቀላቀለና በተወሰኑ አዛውንቶች ብቻ የሚነገረውን የቅማንት ቋንቋ እንዳይጠፋ ለማበልፀግም ጥረት መደረግ እንዳለበት ምክር ቤቱ የራስ አስተዳደር ጥያቄውን ውድ ባደረገበተወ ወቅት ሃሳብ አቅርቦ እንደነበር አቶ መርሃጽድቅ ያስረዳሉ።

አቶ ይርሳው በበኩላቸው ሕገ መንግሥቱ የሚጠይቀውን መስፈርት ማሟላታቸውን ይገልፃሉ።

መግባቢያቸው አማርኛ ቋንቋ ቢሆንም የቅማንትኛ ቋንቋ ያልሞተ መሆኑን፣ ወጥ የሆነ የሕዝብ አሰፋፈር፣ በሥነ ልቦና ቅማንት ነኝ ብሎ የሚያምን ህዝብ መኖሩንና ከአማራው ጋር የተቀላቀለ ቢሆንም የራሳቸው ባህል እንዳላቸውም ይገልጻሉ።

በዚህም መሰረት ውሳኔው የማንነት ጥያቄ ያነሱትን የኮሚቴ አባላት ያስደሰተ አልነበረም። ውሳኔውን ባለመቀበልም ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቤቱታ ማቅረባቸውን አቶ ይርሳው ይናገራሉ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ደግሞ ጉዳዩን የክልሉ መንግሥት ድጋሚ እንዲያየው መልሶ የላከው ሲሆን ከሁለት ዓመታት በኋላ ግን በ2007 ዓ.ም የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር መፈቀዱን አቶ ይርሳው ለቢቢሲ ገልፀዋል።

የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ እንዴት ተመለሰ?

ክልሉ በ2005 ባደረገው ጥናት የቅማንት ማህበረሰብ የማንነትና የራሱን አስተዳደር ለመመስረት ሕገ መንግሥታዊ መስፈርቶችን አላሟላም ከተባለ ከሁለት ዓመት በኋላ ጥያቄው እንዴት ተቀባይነት አገኘ?

በምን መስፈርት የራስ አስተዳደሩ ተመለሰ? ለአቶ መርሃጽድቅ የቀረበ ጥያቄ ነው።

እንደ አቶ መርሃ ጽድቅ ከሆነ በተለይ በአካባቢው ግጭቶች እየተበራከቱና ተቋማት እየተዘጉ በመምጣታቸው፤ በ2007 ዓ.ም የክልሉ የርዕሰ መስተዳድር ምክር ቤት "ጉዳዩ እንደገና ይታይልኝ" በማለቱ ጥናቱ ለሁለተኛ ጊዜ ለክልሉ ምክር ቤት መቅረቡን ያስታውሳሉ።

ምክር ቤቱ የቅማንትን የማንነት ጥያቄ ለሁለተኛ ጊዜ ለማየት እንደተገደደ የሚያስረዱት አቶ መርሃ ጽድቅ "ይህም ፖለቲካዊ ጫና ነበረበት" ይላሉ።

አቶ መርሃ ጽድቅ ፖለቲካዊ ጫና የሚሉትም የ2005ቱ ዓ.ም የምክር ቤት ውሳኔ በቅማንት የማንነት ኮሚቴ ቁጣን ከመቀስቀሱ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ያስረዳሉ።

"ውሳኔው በኮሚቴው ዘንድ ቁጣን ስለቀሰቀሰ እና የሰው ህይወትም እየጠፋ ሲመጣ ፖለቲከኞቹ [በተለይ በፌደራል ደረጃ የነበሩ የብአዴን ካድሬዎች ከፍተኛ ጫና በማሳደራቸው] እጃቸውን አስረዝመው ቅማንት ይኖርባቸዋል የሚባሉትን አካባቢዎች አገናኝታችሁ ወስኑላቸው፤ ሕዝባችን እስከሆኑ ድረስ የትም አይሄዱም" የሚል ትዕዛዝ እንደተሰጠ አቶ መርሃ ጽድቅ ይናገራሉ።

በዚሁ መሰረትም ከላይ አርማጭሆ ወረዳ 25 እና ከጭልጋ ወረዳ 17 በድምሩ 42 ቀበሌዎችን በቅማንት የራስ አስተዳደር፤ በልዩ ወረዳ እንዲዋቀሩ ተወስኗል። ይህም ከሕገ መንግሥቱ መስፈርት ውጪ ብዙ ርቀት ተሂዶ የተወሰነ መሆኑን አቶ መርሃ ጽድቅ ይናገራሉ። ነገር ግን ውሳኔው ግጭቱን አላስቆመውም።

የቅማንት የማንነት ጥያቄና አስተዳደር ቅሬታ

ክልሉ የቅማንትን አስተዳደር አርባ ሁለት ቀበሌዎች በልዩ ወረዳ እንዲዋቀር መወሰኑ በማንነት ኮሚቴው ዘንድ ተቀባይነት እንዳላገኘ የሚናገሩት አቶ ይርሳው ናቸው።

"ሕዝቡን ባላሳተፈ መልኩ፤ 42 ቀበሌዎችን ሰጥቻችኋለሁ ነው የተባልነው" ይላሉ።

አርባ ሁለት ቀበሌዎች ለቅማንት የራስ አስተዳደር መወሰኑንም በመቃወምና በቂ አይደለም በሚልም በጭልጋ በ2007 ዓ.ም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ።

"እነዚህ 42 ቀበሌዎች በውይይትና በፖለቲካዊ ውሳኔ የተካለሉ እንጂ ሕዝበ ውሳኔ የተካሄደባቸው አልነበሩም" ብለውም አቶ ይርሳው ያምናሉ።

የአቶ ቹቹ ፅሁፍም እንደሚያስረዳው በወቅቱ በቅማንት ወረዳዎች የመንግሥት ሥራ ቆሞ ስለነበር፤ ሥራ ለማስጀመር፤ እንዲሁም ውሳኔውን ለማስፈጸም፤ የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሮቢት በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ማውራ ከተባለ አካባቢ ጥቅምት 2008 ዓ.ም ላይ ከሕዝብ ጋር ግጭት ተደርጎ የሰው ህይወት አልፏል። ግጭቱም በህዳር 2008 ዓ.ም በሽንፋ አካባቢ ቀጠለ።

ውሳኔውንም ባለመቀበል የማንነት ጥያቄ አቅራቢዎቹ በድጋሜ ቅሬታቸውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ቢያቀርቡም መልሱ ተመሳሳይ ነበር። 'የክልሉ መንግሥት እንደጀመረው ይጨርሰው' የሚል ምላሽ እንደተሰጠ ይነገራል።

ለሦስት ዓመታት ጉዳዩ በውዝግብ ከቀጠለ በኋላ 2010 ዓ.ም ላይ ጥያቄው እንዴት መፈታት አለበት በሚል ከክልሉ መንግሥት ጋር መስማማታቸውን አቶ ይርሳው ይናገራሉ።

በዚህም መሰረት ከቅማንት የማንነት ጥያቄና ከአማራ ክልል መንግሥት የተውጣጣ ጥምር ኮሚቴ ተዋቅሮ ጥናት ካካሄደ በኋላ ተጨማሪ 21 ቀበሌዎች ወደ ቅማንት ይካለሉ ተብለው ወደ ቅማንት የራስ አስተዳደር መካለላቸውንም አቶ ይርሳው ይጠቅሳሉ።

በተመሳሳይም እነዚህ ቀበሌዎች ሲካለሉ ሕዝበ ውሳኔ አለመካሄዱንና እንዲሁ "በውይይትና በፖለቲካ ውሳኔ" የተካለሉ መሆናቸውንም አቶ መርሃ ጽድቅም ሆኑ አቶ ይርሳው ይስማማሉ።

ቀበሌዎቹን ወደ ቅማንት ራስ አስተዳደር የማካለል ውሳኔ

ጥምር ኮሚቴው በማዕከላዊና በምዕራብ ጎንደር በመዘዋወር የተለያዩ ቀበሌ ነዋሪዎችን አወያይቷል። ከቀደሙት ውሳኔዎችም በተለየ መልኩ በ2010 ዓ.ም 12 ቀበሌዎች በሕዝበ ውሳኔ እንወስናለን የሚል ምላሽ መስጠታቸውንም አቶ ይርሳው ይናገራሉ።

ምንም እንኳን ቀበሌዎቹ የራሳቸውን አስተዳደርን በራሳቸው ድምፅ ለመወሰን ቢያስቡም አራት የጭልጋ ቀበሌዎች ላይ ሁከት በመፈጠሩ ምርጫ ሳይካሄድ መቅረቱን አቶ ይርሳው ይገልጻሉ።

ከአስራ ሁለቱ በስምንቱ ቀበሌዎች ሕዝበ ውሳኔ ተካሂዶ ሰባቱ ወደ ነባሩ አስተዳደር እንዲካለሉ ሲወስኑ፤ አንዷ ቀበሌ ወደ ቅማንት የራስ አስተዳደር ለመካለል መወሰኗን ይናገራሉ።

በቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ ሂደት ይህች አንዲት ቀበሌ የራስ አስተዳደሩን በሕዝበ ውሳኔ የተቀላቀለች ብቸኛዋ ቀበሌ ነች።

በተፈጠረ ሁከት ምክንያት ሕዝበ ውሳኔ ያልተካሄደባቸው አራቱ ቀበሌዎች በጥምር ኮሚቴው አማካኝነት ከቀበሌው ነዋሪዎች ጋር ከተወያዩ በኋላ ሁለት ወደ ቅማንት የራስ አስተዳደር ሁለቱ ደግሞ ወደ ነባሩ አስተዳደር እንዲካለሉ መደረጋቸውን አቶ ይርሳው ይገልጻሉ።

በዚህ ሁኔታ በውይይት፤ በፖለቲካዊ ውሳኔና በሕዝበ ውሳኔ የተካተቱት የቅማንት የራስ አስተዳደር ቀበሌዎች ቁጥር ከ60 በላይ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ይርሳው ቀጣዩ ሥራ የራስ አስተዳደሩን መመስረት ነበር።

የቅማንት የራስ አስተዳደርና የስት ቀበሌዎች ጥያቄ

ቀበሌዎቹ ከተካለሉ በኋላ የራስ አስተዳደሩን ለመመስረት የሚያስችል መነሻ መዋቅር (proposal) ኮሚቴው እንዲያዘጋጅ በክልሉ መንግሥት በተጠየቁት መሰረት ሌሎች ሦስት የመተማ ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ ቅማንት ናቸው በሚል እሳቤ በማካተት 72 ቀበሌዎች፤ በስድስት ወረዳ ለማድረግ ወስነው ለክልሉ መንግሥት ምክረ ሃሳብ እንዳቀረቡ አቶ ይርሳው ያስረዳሉ።

የኮሚቴውን ምክረ ሃሳብ በ2010 ዓ.ም የተመለከተው የክልሉ ምክር ቤት "በከፍተኛ ጫና ውስጥ ሆኖ የማንነት ጥያቄው በ69 ቀበሌዎች እንዲዋቀርና ከልዩ ወረዳነት ወደ ብሔረሰብ አስተዳደርነት እንዲያድግ መወሰኑን" አቶ መርሃ ጽድቅ ይጠቅሳሉ።

ይሁን እንጂ ኮሚቴው ጥያቄያቸው ሙሉ በሙሉ ምላሽ እንዳላገኘና በቅማንት አስተዳደር ስር መካተት የሚገባቸው 3 ቀበሌዎች (መቃ፣ ጉባኤ ጀጀቢትና ሌንጫ) በቅማንት ራስ አስተዳደር ስላልተካተቱ ቀበሌዎቹ በቅማንት ራስ አስተዳደር ካልተካለሉ ውሳኔውን እንደማይቀበለው ይፋ ማድረጉን የአቶ ቹቹ ጽሑፍ ያስረዳል።

አቶ ይርሳውም በበኩላቸው በአቶ ቹቹ ፅሁፍ ይስማማሉ "አራቱን ወረዳ ብንቀበለውም ሦስቱ ቀበሌዎች ወደ እኛ መካተት አለባቸው ብለን ስላሰብን በህግ ሊፈቱ ይገባል ብለን ቅሬታችንን ለፌደሬሽን ምክር ቤት ላክን" ይላሉ።

የፌደሬሽን ምክር ቤት ምላሽ

ቅሬታው የደረሰው የፌደሬሽን ምክር ቤትም ጥናት አድርጎ ምላሽ እንደሰጠ የፌደሬሽን ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ጸሃፊ አቶ ወርቁ አዳሙ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ሦስት ባለሞያዎች ከፌደሬሽን ምክር ቤት ወደ ስፍራው ተልከው፤ የተነሳውን ቅሬታ በአካል ቦታው ድረስ በመጓዝ ጥናት ማካሄዳቸውን ያስረዳሉ።

"ሕገ መንግሥቱ ጋር ስለማይጣጣምና ቅሬታ የቀረበባቸው ቀበሌዎች ኩታ ገጠም ስላልሆኑ፤ የክልሉ መንግሥት የሰጠው ውሳኔ ትክክል ነው" የሚል ምላሽም መስጠታቸውን ያስታውሳሉ።

እንደ ፌደሬሽን ምክር ቤት አሰራር ደግሞ እንደዚህ አይነት ቅሬታዎች ሲፈጠሩ በተለይ ቀበሌን ከቀበሌ፤ ወረዳን ከወረዳና ዞንን ከዞን የማዋቀር ውሳኔ መስጠት ያለበት ቅሬታ የተነሳበት ክልል ራሱ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ወርቁ፤ "ቅሬታው አስተዳደራዊ ጉዳይ በመሆኑ መመለስ ያለበት አስተዳደራዊ በሆነ መልኩ ነው" ይላሉ።

አክለውም "ዋናው ነገር ማንነትን እውቅና መስጠት ነው፤ ይህም ምላሽ አግኝቷል" ያሉት አቶ ወርቁ በክልሉ ውስጥ የሚፈጠርን የአስተዳደር ወሰን በተመለከተ ክልሉ ራሱ እንዲፈታ ነው ህጉ የሚያዘው" ብለዋል።

ኮሚቴው ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን አለመቀበሉን የሚገልፁት አቶ ይርሳው ለዚህ የሚያቀርቡት ምክንያት "ጥናቱን ለማከናውን የተላኩት ሰዎች ከተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጡ ስላልነበሩ፤ ገና ከመመለሳቸው በፊት ምን ይዘው እንደሚመለሱ ስለምናውቅ እነዚህ ሰዎች ይዘውት የሚመለሱት ውጤት ምንም ይሁን ምን አንቀበልም ብለን ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ ጽፈናል" ይላሉ።

ኮሜቴው ጥናቱን ለማከናወን የተላኩት ግለሰቦች ገለልተኛ አይደሉም የሚል ጥያቄ ቢያነሳም አቶ ወርቁ በበኩላቸው "የሚዛናዊነት ጥርጣሬ ካለ ከብሔር ብሔረሰብ የተወጣጡ ቢሆኑ የተሻለ ሊሆን ይችላል፤ ካልሆነ ግን መታየት ያለባቸው ሰዎቹ ሳይሆኑ ይዘውት የሚመጡት መረጃ ነው፤ ከዚህም አንጻር የመጣው መረጃ መሬት ላይ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ በትክክል የሚገልጽ ነው" ይላሉ።

የማንነት ጥያቄና ራስ አስተዳደር ለምን ተፈለገ?

የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄ በዋናነት ልማትን ለማፋጠን እንደሆነ የሚናገሩት አቶ ይርሳው "ከሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች ጋር እኩል ተጠቃሚነት፣ ባህልንና እሴትን ለማሳደግ እንዲሁም የራስን አካባቢ ህዝቡ ራሱ በሚመርጣቸው ሰዎች እንዲያስተዳደርና በዚህም ከፍተኛ ልማት ለማምጣት ነው" ይላሉ።

የቅማንት የራስ አስተዳደር ጥያቄና የክልሉ ውዝግብ መፍትሔ ሳያገኝ በዚህ ከቀጠለ በኋላ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን በመጡ ማግስት፤ ኮሚቴውንና የክልሉን መንግሥት ተወካዮች ባካተተ መልኩ ውይይት ተደርጎ ጉዳዩ በሰላማዊ ሁኔታ እንዲፈታ ምክረ ሃሳብ አቅርበዋል።

እንደ አቶ ይርሳው ገለጻ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ምክረ ሃሳብ በኋላ ኮሚቴው ነሐሴ ወር 2010 ዓ.ም ጎንደር ለስብሰባ ተቀምጧል።

"ስብሰባ ላይ እያለን በክልሉ የፀጥታ ኃይል የእገታ ሙከራ ተካሂዶብናል፤ ከዚያም በኋላ ከክልሉ መንግሥት ጋር ያለን ግንኙነት ተቋረጠ" ይላሉ።

ውዝግቡ እንዳይቋጭ ምክንያቱ ይህ መሆኑንም ያነሳሉ።

አቶ መርሃ ጽድቅ ግን በዚህ አይስማሙም፤ እሳቸው እንደሚሉት በተለይ የጸጥታው መደፍረስና ነገሮች መበላሽት የጀመሩት ክልሉ በ2005 ባጠናው መሰረት የመጀመሪያውና ትክክለኛው ውሳኔ በመቀልበሱ እንደሆነ አፅንኦት በመስጠት ይናገራሉ።

"ክልሉ ሰለባ ሆኗል፤ በተለይ ከ2005 ዓ.ም ውሳኔ በኋላ ክልሉ ከሚገባው በላይ ባልተገባ መንገድ ተጠልፏል። በማንም አይደለም የተጠለፈው፤ በራሱ ሰዎች ነው። በተለይ በፌደራል ደረጃ ላይ በነበሩት ትልልቅ የብአዴን ሰዎች የክልሉን ምክር ቤት ወደዚህ ችግር አስገብተውት አካባቢው እንዳይረጋጋ ተደርጓል" የሚል ሃሳብ ያነሳሉ።

ግጭትና መፈናቀል በማዕከላዊና ምዕራብ ጎንደር

በአካባቢው በተለያዩ ጊዜያት ችግሮች እየተነሱ የሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም በስፋት ተስተውሏል።

በተለይ ባለፈው ዓመት የተነሳው ግጭት የክልሉን አጠቃላይ ተፈናቃይ አሃዝ ወደ 90 ሺህ ያሳደገና በግጭቱም ቢያንስ 560 ቤቶች መቃጠላቸውን በወቅቱ የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

ለተወሰኑ ወራት አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ ቢቆይም ሰሞኑን በተቀሰቀሰ ግጭት ደግሞ ሰዎች ተገድለዋል፤ ንብረት ወድሟል። ንጹሃን ዜጎችን ከተሽከርካሪ አስወርደው ማንነታቸውን መሰረት በማድረግ ቢያንስ ስድስት ሰዎች እንደተገደሉና ይህም "በጽንፈኛው ኮሚቴ" የሚመራና የሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነት ያለው መሆኑን የክልሉ መንግሥት አስታውቋል።

ለዚህ ክስ ምላሽ የሰጡት አቶ ይርሳው "እኛ የማንም ተላላኪ አይደለንም፤ እንደዚያም ሆነን ከሆነ የክልሉ መንግሥት ምን ይሰራ ነበር?" በማለት ይጠይቃሉ።

ከሰሞኑ የተቀሰቀሰውን ግጭት በተመለከተ ደግሞ "የቅማንት ሕዝብ የትም አልሄደም፤ ሲመጡበት ግን ራሱን ተከላክሏል" ያሉት አቶ ይርሳው "መኪና ላይ ሰዎችን አስወርዶ በማንነታቸው ምክንያት መግደል ነውር ነው፤ ማን እንደፈጸመው ግን መረጃ የለኝም" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።

አሁን የክልሉ መንግሥትና ኮሚቴው አንዱ ሌላውን በመክሰስ ላይ ይገኛሉ። በአካባቢው ግጭቶች እየተፈጠሩ በየጊዜው የሰው ህይወት መጥፋትና የንብረት መውደም የአካባቢው መገለጫ እንደሆነ ብዙዎች አስተያየታቸውን ይሰጣሉ።

መፍትሄው ምን ይሆን?

አቶ መርሃ ጽድቅ ለጉዳዩ ሁለት የመፍትሔ ሃሳቦች መኖራቸውን ይገልጻሉ።

እንደ እርሳቸው ገለጻ "የራስ አስተዳደሩ ሕገ መንግሥታዊ መስፈርቶችን ሳያሟላ የተወሰነ በመሆኑ ህጋዊ መሰረት የለውም በማለት ውሳኔውን ውድቅ ማድረግ ይቻላል" የሚለው አንደኛው አማራጭ ነው፤ ነገር ግን ይህ አማራጭ ተግባራዊ ቢደረግ "ሰላም ሊሰፍን ይችላል ወይ?" የሚለው አጠያያቂ መሆኑን ይገልጻሉ።

"ሕዝቡ በዚህ ደረጃ ከተነሳሳ በኋላና ብዙ ተስፋዎችን ካሳየነው በኋላ የራስ አስተዳደርህን አጥፌብሃለሁ ቢባል ውጤቱ መረጋጋትን የሚያሰፍን አይሆንም" ባይ ናቸው።

ሌላኛው ደግሞ እንደ አማራጭ የሚያቀርቡት የተፈቀደውን የራስ አስተዳደር መመስረትና ይህንን ህጋዊ አካሄድ በሚያስተጓጉሉት አካላት ላይ ደግሞ ህጋዊ ርምጃ መውሰድ እንደሆነ አቶ መርሃ ጽድቅ ይናገራሉ።

"ሂደቱ የራሱ ችግር እንዳለበት ሆኖ 69 ቀበሌዎችን ያቀፈው የራስ አስተዳደር ይደራጃል" ያሉት አቶ መርሃ ጽድቅ ይካተቱልኝ የሚባሉት ሦስት ቀበሌዎች አስፈላጊ ከሆነ ባሉበት በልዩ ቀበሌ ሊደራጁ ይችላሉ ብለዋል።

አቶ ይርሳውም በበኩላቸው ሁለት የመፍትሄ አማራጮችን ያቀርባሉ። አንደኛው የብሔረሰብ አስተዳደሩ እንዲቋቋም ነገር ግን ባለፈው የፌዴሬሽን ሰዎች የሰጡት ውሳኔ ተሽሮ ሌላ አካል በተለይ ከደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች የተውጣጣ አካል የሦስቱን ቀበሌዎች ጉዳይ እንዲያጠና ጠይቀዋል።

ሁለተኛው ደግሞ "ብሔረሰብ አስተዳደሩ ሲመሰረት ምንም አይነት ጣልቃ ገብነት አያስፈልገንም፤ ምክንያቱም አሁን ባለው ሁኔታ ከኮሚቴው ጋር የነበሩ ነገር ግን አሁን አብረውን ያልሆኑ ሰዎች እንዲሳተፉ እየተደረገ ስለሆነ ነው" ይላሉ።