"ታጣቂዎች ሰላማዊ ዜጎች መኪና አስቁመው ተገድለዋል" አቶ አገኘሁ - "ሰላማዊ ሰዎች በአማራ ልዩ ኃይል ጥቃት ደርሶባቸዋል" የአካባቢው ነዋሪ

የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media Agency

በቅማንት አካባቢ ግጭቱ እንደገና ያገረሸው ባለፈው ዓመት ጳጉሜ 3/2011 ዓ.ም እንደሆነ በአካባቢው ነዋሪ የሆኑት መምህር መካሻው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የነዋሪውን ሀሳብ የሚያጠናክሩት የቅማንት የማንነትና የራስ አስተዳደር ይከበርልኝ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ከፍአለ ማሞ በበኩላቸው ከጳጉሜ 3 ጀምሮ በአካባቢው ጦር መዝመቱን የይናገራሉ።

የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበኩላቸው የክልሉ ልዩ ኃይል ሕግ ለማስከበር ወደ ስፍራው መንቀሳቀሱን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ከጳጉሜ 3 ጀምሮ የክልሉ የፀጥታ ኃይል ወደ አካባቢው አንቀሳቅሶ ወደ ቀበሌዎች በመግባት፣ ሰላማዊ መንደርን ከብቦ ጥቃት ማድረሱን የተናገሩት መምህር መካሻው የፀጥታ ኃይሉ ለተኩሱ ምክንያት የሰጠው በአካባቢው ሽፍታ አለ የሚል መሆኑን ያስረዳሉ።

መምህር መካሻው በስፍራው ሽፍታ እንደሌለና፣ ሰላማዊ ሰዎች የሚኖሩበት አካባቢ በልዩ ኃይሉ ጥቃት እንደተፈጸመ ይናገራሉ።

"በሕዝብ ይሁንታ የቅማንት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄን ለማስተባበር የተቋቋመው ኮሚቴ አባላትን ለመያዝ ሆን ብሎ የተደረገ ነው" የሚሉት መምህር መካሻው ሕዝቡ ኮሚቴዎቻችንን አትንኩ እያለ ስለሆነ "ሽፍታ ልንይዝ ነው" በሚል ሰበብ መጥተዋል ሲሉም ያስረዳሉ።

አቶ ከፍአለ ማሞ በበኩላቸው በ2012 ዓ.ም ከመስከረም 10 ጀምሮ በአካባቢው የልዩ ኃይል ጥቃት እያደረሰ ነው ሲሉም ይከስሳሉ። መስከረም 11 ወደ መንደር ገብተው ወጣቶች ላይ ተኩስ መክፈታቸውን ከዚያም ገበሬውም ላይ መተኮስ መጀመሩን ያስረዳሉ።

በአሁኑ ሰዓት ወደ ስፍራው ከፍተኛ ጦር እየተንቀሳቀሰ መሆኑንም ይናገራሉ።

መምህር መካሻው መስከረም 11 የልዩ ኃይል አባላት በድጋሚ መጥተው መንደሩን ማሰሳቸውን፣ የደረሰውን ሰብልም ሲያጠፉ ውለዋል ሲሉ ምሬታቸውን ይገልፃሉ።

"የፀጥታ ኃይሉ በእግሩ የደረሰውን ሰብል ሲረመርም ገበሬዎች ተኩስ መጀመራቸውን" የሚናገሩት መምህር መካሻው "በጥቃቱ ምክንያት ንብረት ወድሟል፣ ሰዎች ከቀያቸውና ከአካባቢያቸው ተፈናቅለዋል" ሲሉም ያለውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ከዚህ በኋላም ከመስከረም 16 ጀምሮ ባሉ ተከታታይ ቀናት ጥቃት እየደረሰባቸው እንዳለ የተናገሩት ግለሰቡ በዚህም የተነሳ አንድ ሰው ጨንቾ አካባቢ መሞቱን ተናግረዋል።

አይከል ከተማ አካባቢም የሞቱ ሰዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ግለሰቡ በወና ከተማ ሰው መገደሉን በመግለፅ በቁጥር በርከት ያሉ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውንና መቁሰላቸውን ያብራራሉ።

አቶ አገኘሁ ተሻገር፣ የአማራ ክልል የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ የቅማንት የማንነትና የአስተዳደር ጥያቄ በአግባቡ እንዲፈታ ክልሉ ውሳኔዎችን ማሳለፉን በማስታወስ "የአማራ ክልል ውስጥ የተረጋጋ ሁኔታ እንዳይፈጠር የሚፈልጉ ኃይሎች" ያሏቸውን ለተፈጠረው ግጭት ተጠያቂ ያደርጋሉ።

እነዚህን ኃይሎችን በስም ባይጠቅሱም፤ የግጭቱ ዓላማ ነው ያሉትን ሲያስረዱም "በአካባቢው አለመረጋጋት እንዲኖር፣ ወደ መተማ የሚሄደውን መንገድ መዝጋት፣ በዚህም የተነሳ የአማራ አርሶ አደርና ባለ ሀብት ምርቱን እንዳይሰበስብ ሆን ተብሎ፣ ታቅዶ እየተሰራ ያለ ሥራ ነው" ይላሉ።

በአካባቢው በታጣቂዎች ደረሰ ያሉትን ጥቃት ሲዘረዝሩም "ሰላማዊ ዜጎች በመኪና ሲንቀሳቀሱ መኪናውን አስቁመው በማንነታቸው ብቻ ተገድለዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም የሚኒባስ ሾፌር ተገድሏል" የሚሉት ኃላፊው የነዳጅ ቦቴ ሾፌሮች መታገታቸውንና ቦቴውን ማቃጠላቸውንም ጨምረው አስረድተዋል።

የሰሞኑ ግጭት የተቀሰቀሰው የፀጥታ አካላት አንድ በወንጀል የሚጠረጠር ግለሰብ ይዘው ከአንድ ቀበሌ ወደ ሌላ ቀበሌ ሲንቀሳቀሱ ተኩስ በመከፈቱ መሆኑን የሚያስረዱት የክልሉ የሰላምና ሕዝብ ደህንነት ቢሮ ኃላፊ በዚህም የተነሳ አንድ የፖሊስ አባል ሕይወቱን ማጣቱን ይናገራሉ።

ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የመከላከያና የልዩ ኃይል አባላት በጭልጋ ወረዳ ጮንጮቅ ቀበሌ ለሚገኝ የልዩ ኃይል አባላት ቀለብ አድርሰው ሲመጡ ተኩስ እንደተከፈተባቸው ይናገራሉ።

የፀጥታ አካላት ወደ ማደሪያ ካምፓቸው ሲገቡ ከበባ እንደተፈፀመባቸው የሚያስረዱት ኃላፊው በዚህ ወቅት "ከደረሰባቸው ውርጅብኝ" ራሳቸውን መከላከላቸውን ይናገራሉ።

ግጭት ውስጥ ተኩስ ሲከፈት ሰው ሊሞት ይችላል የሚሉት ኃላፊው ይህንን ይዞ "ጭፍጨፋ እየተፈፀመብን ነው ማለት ሐሰት ነው" ይላሉ።

"ከታጣቂ ኃይሎች፣ ከፀጥታ አካላት የሞቱና የቆሰሉ እንዳሉ የተናገሩት ኃላፊው ሕግ ለማስከበር ተንቀሳቅሰናል፤ ሕግ ማስከበርም አለብን" ሲሉ እየወሰዱት ያለውን እርምጃ ሕጋዊነት ያስረዳሉ።

አሁን ጉዳዩ እየተረጋጋ ነው ያሉት ኃላፊው ልዩ ኃይልና መከላከያ አይከል ከተማ ውስጥ መኖሩን በመጥቀስ "አንደኛው ጥያቄ ልዩ ኃይል ከአካባቢው ይውጣ የሚል ነው፤ ደግሜ እናገረዋለሁ ልዩ ኃይል ከአካባቢው አይወጣም። ሕግ ለማስከበር እንንቀሳቀሳል" ብለዋል።

"በአጭር ጊዜ ውስጥ መንገዱን ለማስከፈት እየሰራን ነው" የሚሉት አቶ አገኘሁ የመከላከያ መኮንኖችም በአካባቢው ሰላም ለማስፈን እገዛ እያደረጉ ነው ብለዋል።