በማዕከላዊ ጎንደር ዞን በተፈጠረ ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት ደረሰ የሚሉና ሌሎችም

የፎቶው ባለመብት, Amhara Mass Media Agency
ኢትዮጵያ
የሶማሌ ክልል ምክር ቤት 12 የምክር ቤት አባላቱን ያለመከሰስ መብት ማንሳቱን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘገቡ።
በምክር ቤቱ ያለመከሰስ መብታቸው ከተነሳው የምክር ቤት አባላት መካከል የቀድሞ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር፣ የቀድሞ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ፣የቀድሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ኃላፊና ሌሎችም የክልሉ የቀድሞ ባለስልጣናት እንደሚገኙበት ዘገባው አመልክቷል።
***
በማዕከላዊ ጎንደር በተፈጠረ ግጭት በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን የክልሉ መገናኛ ብዙሃን ዘገበ።
በጉዳዩ ላይ የአማራ ክልል የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ አሰማኸኝ አስረስ መግለጫ የሰጡ ሲሆን ግጭቱ በዞኑ ምስራቅ ደንቢያ ወረዳ በተለያዩ ቀበሌዎች በአማራና ቅማንት ብሔረሰቦች መካከል የተፈጠረ ሲሆን በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን አስታውቀዋል።
በጉዳዩ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን የእስር ማዘዣ የወጣባቸው እንዳሉም በመግለጫው ተገልጿል።
***
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ስም የባህልና ኪነጥበብ ማዕከል ሊገነባ መሆኑን አስታወቀ።
የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር ታደሰ ቀነኢ ለቢቢሲ እንደተናገሩት የባህል ማዕከሉ አዲሱ ትውልድ ከአንጋፋ ምሁራን ልምድ በመውሰድና በመማር በዘርፉ ልቀው እንዲገኙ ለማስቻል ያለመ ነው።
ደቡብ አፍሪካ
በደቡብ አፍሪካ በማዕድን ማውጫ ጉድጓድ የጋዝ ማስተላለፊያ ቱቦ ፈንድቶ 6 ሰዎች መሞታቸውን የአገሪቱ ፖሊስ ቃል አቀባይ አስታወቁ።
ግለሰቦቹ መዳብ ለመስረቅ ሲሉ በማዕድን ማውጫ የገቡ ሲሆን ሌሎች 20 ግለሰቦችም መውጫ አጥተው ጉድጓዱ ውስጥ እንደቀሩ ተገልጿል።
ሕንድ
የ27 ዓመቱ ሕንዳዊው ግለሰብ "ወላጆቼ ፈቃዴን ሳይጠይቁ ወልደውኛል" በሚል ሊከሳቸው ነው።
በሙምባይ በንግድ ላይ ተሰማራው ይህ ግለሰብ ህፃናትን ወደ ዚህ ምድር ማምጣትና ለበርካታ ችግር እንድጋለጡ ማድረግ ተገቢ አይደለም ሲል ለቢቢሲ ተናግሯል።
ኢንዶኔዥያ
በኢንዶኔዥያ አንዲት እንግሊዛዊት በባሊ የሚገኝ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሰራተኛን በጥፊ በመምታቷ በቁጥጥር ስር ዋለች።
ሴትዮዋ ጥፋተኛ የተባለችው በሰራተኛው ላይ ባደረሰችው ጥቃትና ፓስፖርቷን በግድ ነጥቃ በመሄዷ ሲሆን የ6 ወራት እስር ተከናንባለች።
አሜሪካ
አሜሪካ ለካሜሩን ወታደራዊ ድጋፍ በሚል ስትሰጥ የነበረውን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ልታቋርጥ መሆኑ ተሰማ።
አሜሪካ ይህን ያለችው በፀጥታ ኃይሎች እየተፈፀመ ነው ባለችው የሰብዓዊ መብት ጥሰት ምክንያት ሲሆን የካሜሩን መንግስት ምርመራ ማካሄድና ድርጊት ፈፃሚዎቹን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት አሳስባለች።
***
አሜሪካ ከእስራኤል ሚሳየል ማክሸፊያ የመግዛት እቅድ እንዳላት አስታወቀች።
መሳሪያው ከስምንት ዓመት በፊት ስራ ላይ የዋለ ሲሆን ራዳርን ተጠቅሞ ሚሳየሎችን በማጨናገፍ የጠላትን ጥቃት የሚመልስ እንደሆነ ተነግሯል።
***
ዝነኛው ፀሃፊ ዳን ማሎሪ የአእምሮ ህመሙን ለመደበቅ ሲል የጭንቅላት ካንሰር ታምሜያለሁ ብሎ መዋሸቱን አመነ።
ለዚህ የሰጠው ምክንያት በወቅቱ የስሜት መዋዠቅን የሚያስከትል የአዕምሮ ህመሙን (ባይፖላር) ለመቆጣጠር ፈታኝ ስለሆነበት እንደነበር ገልጿል።
በቅርቡም ኒውዮርከር የተሰኘው መፅሄት ስለ ግል ህይወቱ ብዙ ሀሰት ተናግሯል በሚል ወንጅሎታል።
የአየር ንብረት
ካለፉት 150 ዓመታት ጊዜ፤ ባሳለፍናቸው 10 ዓመታት የዓለማችን ከፍተኛ ሙቀት መመዝገቡን ተመራማሪዎች ገለፁ።
በሚቀጥሉት 5 ዓመታትም የዓለማችን አማካይ የሙቀት መጠን በ1.5 ሴልሽየስ ከፍ ሊል እንደሚችል ተመራማሪዎቹ ጠቁመዋል።












