ታዋቂው ፀሀፊ የአዕምሮ ህመሙን ለመደበቅ ካንሰር ታምሜያለሁ ብሎ መዋሸቱን አመነ

ዳን ማሎሪ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ዘ ውመን ኢን ዘ ዊንዶው በሚል መፅሀፉ ዝነኝነትን የተጎናፀፈው ፀሀፊው ዳን ማሎሪ የጭንቅላት ካንሰር ታምሜያለሁ ብሎ መዋሸቱን አመነ።

ለዚህ እንደ ምክንያትነት የሰጠውም በወቅቱ የስሜት መዋዠቅን የሚያስከትል የአዕምሮ ህመሙን (ባይፖላር) ለመቆጣጠር ፈታኝ ስለሆነበት እንደነበር ገልጿል።

በቅርቡም ኒውዮርከር የተሰኘው መፅሄት ስለ ግል ህይወቱ ብዙ ሀሰት ተናግሯል በሚል ወንጅሎታል።

በመፅሄቱ ላይ እንደተጠቀሰው ፀሀፊው በተደጋጋሚ የአዕምሮ ካንሰር እንዳለበት የገለፀ ሲሆን፤ ከዚህም መካከል የዩኒቨርስቲ ማመልከቻ ላይ እንዲሁም በለንደንና ኒውዮርክ ማተሚያ ቤቶች በሚሰራበት ወቅት ደግሞ ለጓደኞቹ ካንሰር እንዳለበት ተናግሯል።

ፅሁፉ ጨምሮ እንደጠቀሰው እናቱና ወንድሙ በካንሰር በሽታ እንደሞቱ ዋሽቷል ብሏል።

ምንም እንኳን ማሎሪ ታዳጊ በነበረበት ወቅት እናቱ የካንሰር ህመምተኛ የነበሩ ቢሆንም እናቱም ሆነ ወንድሙ በህይወት እንዳሉ በዚሁ ፅሁፍ ተጠቅሷል።

ፀሀፊው በምላሹ እናቱ በጡት ካንሰር ይሰቃዩ እንደነበርና ይህም ከፍተኛ የሆነ ህመምና ጭንቀት እንዲሁም የአዕምሮው ጤና መቃወስ እንዳስከተለበት ተናግሯል።

"የአዕምሮ ህመም አለብኝ ብየ ብናገር ጉድለት እንዳለብኝ ይቆጥሩኛል ብየ ስላሰብኩኝ ይህንን መንገድ መረጥኩኝ" ብሏል።

በተደጋጋሚም ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት፣ የማስታወስ እክልና እውነታውን የመለየት ችግር በእጅጉ አጋጥሞት እንደነበር ገልጿል።

"በከፍተኛ ጭንቀት ላይ ስለነበርኩኝ አንዳንድ ጊዜም የምለውን ነገር አላስታውሰውም" ብሏል።

ማንንም ለማሳሳትም ሆነ በጥቅም ለመያዝ እንዳልተነሳሳ ለመፅሄቱ ተናግሯል።

በኒውዮርክ ከፍተኛ ሽያጭ ዝርዝር ውስጥ አንደኛ ደረጃ መቆናጠጥ የቻለውን ውመን ኢን ዘ ዊንዶው ከመፃፉ በፊት በመፅሀፍ አርታኢነት አገልግሏል።

ይህ ሁለተኛ መፅሀፉ ሲሆን ለህትመት የበቃውም ባለፈው አመት ጥር ወር ላይ ነበር።