ደቡብ ጎንደር መካነ እየሱስ ውስጥ ምን ተፈጠረ?

በትናንትናው ዕለት (ዕሁድ) በአማራ ክልል ደቡብ ጎንደር መካነ እየሱስ ከተማ በነዋሪዎች መካከል የተፈጠረ ቅሬታ ሃይማኖታዊ ገጽታን በመያዝ አለመግባባቱ ከቁጥጥር ውጪ ወጥቶ በንብረት ላይ ጉዳት ደርሷል። ችግሩ መነሻ ምን ነበር?
አቶ አደም ጡሃሬ ሴት ልጃቸውን ለመዳር ጥር 26/2011 ዓ.ምን ምርጫቸው አደረጉ። በቀጠሮው መሰረት ሠርግ የሚጠይቀውን ማንኛውንም ነገር ተሰናድቶ ተቆረጠው ዕለት የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ መከናወን ጀምሯል።
ያልተጠበቀው ነገር የሆነው ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ነበር። ቢቢሲ የመካነእየሱስ ከተማ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ተወካይ ሃላፊ ኢንስፔክተር አወቀ ተሸሽጎን ምን ተፈጠረ ብሎ ጠይቋል።
ኢንስፔክተሩ እንደገለጹት የሠርጉን ዳስ ለማስዋብ ከማተሚያ ቤቶች የተቆራረጡ ወረቀቶችን አቶ አደም ከባህርዳር በማስመጣት ድንኳን ዉስጥ ነስንሰዋል።
በሠርጉ ደግሞ ሙስሊሙም ክርስቲያኑም ታዳሚ ነበር። አስር ሰዓት አካባቢ ግን ከተነሰነሰው የወረቀት ቁርጥራጭ መካከል "የድንግል ማርያም ስዕለ አድህኖ" ሲረገጥ አይተናል በማለት ክርስቲያን የሃይማኖት አባቶች ቅሬታ ያሰማሉ።
የከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ሁኔታውን በማረጋጋት የሠርጉ ደጋሽ አቶ አደምን ፖሊስ ጣቢያ እንዲቆዩ በማድረግ ሌሎች ደግሞ ወደየመጡበት ተስማምተዉ እንዲመለሱ ያደርጋል።
ይህ ግን ከተወሰኑ ደቂቃዎች በላይ መቀጠል አልቻለም። ወጣቶቹ በመሰባሰብ ተመልሰው ወደ ሠርጉ ቤት በመሄድ የሠርጉን ድንኳንና ሌሎች ንብረቶችን በማቃጠል ግጭቱን ጀመሩ።
በዚህ ያልተቋጨዉ የወጣቶቹ እንቅስቃሴ በከተማው የሚገኙ ሱቆችንና የሞባይል መጠገኛ ማዕከሎችን ከመዝረፍም በተጨማሪ በከተማዋ የሚገኘውን መስጊድ እስከማቃጠል ደርሷል ብለዋል ኢንስፔክተር አወቀ።
ኢንስፔክተሩ አክለውም "ችግሩን ለመቆጣጠር ጥረት ብናደርግም ካቅማችን በላይ በመሆኑ ከዞን ልዩ ኃይል እስኪመጣ ድረስ ችግሩ ከቁጥጥር ውጭ ሆኖ ቆይቷል" ብለዋል።
በንብረት ላይ የደረሰውን ጉዳት እያጣራን ነው ያሉት ተወካይ ሃላፊው ሁለት ግለሰቦች እና አንድ የመስጊዱ ጥበቃ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል።
"የሙስሊሙ ማህበረሰብ ምንም አይነት የአጸፋ እርምጃ ለመውሰድ አልሞከረም። እንዲያውም ቤቱንና ንብረቱን በመተው ወደ ክርስቲያን ወገኑ በመጠለል ችግሩ እንዳይባባስ ያሳየው መልካም ተግባር የሚያስመሰግን ነው" ብለዋል።
"ችግሩን ሆን ብሎ ያነሳሳው አካል አለ" ያሉት ኢንስፔክተር አወቀ እስካሁን ስለተወሰደው እርምጃና የምርመራ ውጤት ለጊዜው መናገር እንደማይፈልጉ ገልጸው ወደፊት አጥፊዎቹን በህግ ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ኢንስፔክተሩ ጨምረው ዛሬ በአካባቢው መረጋጋት መስፈኑንና ችግሩ በቁጥጥር ስር መዋሉን ገለጸዋል።












