ኡጋንዳ የዋትስአፕ ተጠቃሚዎችን ቀረጥ ልታስከፍል ነው

የኡጋንዳ ፓርላማ አጨቃጫቂውን አዲስ ህግ ትናንት ካፀደቀ በኋላ የበይነ-መረብ የመልዕክት መለዋወጫ የሆነውን የዋትስአፕ አገልግሎትን የሚጠቀሙ ዜጎች 200 ሽልንግ ዕለታዊ ቀረጥ እንዲከፍሉ ተወስኗል።
በዚህም ከእያንዳንዱ ተጠቃሚ በቀን 0.05 ዶላር ያህል የሚሰበሰብ ሲሆን አዲሱ ህግ ተግባራዊ የሚሆነው ከፈረንጆቹ ሐምሌ ወር ጀምሮ እንደሆነም ታውቋል።
በተጨማሪም ሃገሪቱ በሞባይል ስልክ አማካይነት የሚተላለፍ ገንዘብም ላይ ቀረጥ ጥላለች። በዚህም መሰረት በእያንዳንዱ የገንዘብ ዝውውር ላይ ከአጠቃላዩ ገንዘብ አንድ በመቶ ቀረጥ እንዲከፈል ተወስኗል።
የግል ጋዜጣ የሆነው ዴይሊ ሞኒተር እንደዘገበው ይህ ውሳኔ "ተደራራቢ ቀረጥ ነው" ሲሉ ቢያንስ ሦስት የፓርላማ አባላት አዲሱን ደንብ ተችተውታል።
የፓርላማ አባላቱ እንዳሉት ዜጎች ዋትስአፕን የሚገለገሉት ቀድመው በሚገዙት የበይነ-መረብ አየር ሰዓት በመሆኑ ድጋሚ ቀረጥ እንዲከፍሉ ማድረግ የተጠቃሚዎችን መብት የሚጋፋ ነው።
ሌላው ሥልጣን ላይ ያለው ፓርቲ አባል ደግሞ "አንድ በመቶ ቀረጥ ለፓርላማ አባላት ትንሽ ገንዘብ ነው። ነገር ግን በቀን ከአንድ ዶላር በታች ለሚያገኙ ሰዎች ግን ከባድ ነው" ሲሉ ተቃውመውታል።








