እንግዳ ሰዎችን በመርዳት ላይቤሪያ ከአፍሪካ ቀዳሚ ሆነች

ለድጋፍ የተዘረጉ እጆች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ላይቤሪያ እንግዳ የሆኑ ሰዎችን በመርዳት በዓለማችን ካሉ አገራት ግንባር ቀደም መሆኗን 'ወርልድ ጊቪንግ ኢንዴክስ' አመለከተ።

ተቀማጭነቱን በእንግሊዝ ያደረገው ግብረ ሰናይ ድርጅት ለጋሽ ሰዎችን አስመልክቶ ላካሄደው ጥናት ከተጠቀማቸው መስፈርቶች መካከል እንግዳ የሆኑ ሰዎችን መርዳት የሚለው ይገኝበታል።

በተጨማሪም ሰዎች ምን ያህል ገንዘብ ለግብረ ሰናይ ድርጅት ይለግሳሉ፤ ምን ያህል ጊዜስ በበጎፈቃደኝነት ሥራ ላይ ያውላሉ የሚለውንም ተመልክቷል።

ጥናቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ 1.3 ሚሊየን ሰዎችን ያሳተፈና ከ10 ዓመታት በፊት የተሠራ ጥናትን መሰረት አድርጓል።

በአጠቃላይ ዝርዝሩ ውስጥ ኬንያ በአፍሪካ ካሉ ለጋሽ አገራት ቀዳሚ፤ በዓለም ደግሞ በ11ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች። ላይቤሪያ በ17ኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ፤ ሴራሊዮን በ20ኛ እንዲሁም ናይጄሪያ በ22 ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ተገልጿል።

ላይቤሪያን ጨምሮ፤ ሰባት የአፍሪካ አገራት እስከ አስር ባሉት ደረጃዎች ላይ ተቀምጠዋል። ሴራሊዮን ሁለተኛ፣ ኬንያ አራተኛ፣ ዛምቢያ አምስተኛ፣ ኡጋንዳ ስድስተኛ ፣ ናይጄሪያ ሰባተኛ እና ማላዊ አስረኛ ደረጃን ይዘዋል።

ደረጃው እንግዳ የሆኑ ሰዎችን በመርዳት የተዘረዘረ ነው።