የሙሴቬኒ ተፎካካሪ ቦቢ ዋይን የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ይቅርብኝ አለ

ሮበርት ኪያጉላኒ (ቦቢ ዋይን)

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሮበርት ኪያጉላኒ (ቦቢ ዋይን)

የኡጋንዳ ፕሬዝዳንትዊ ምርጫ ተፎካካሪ የሆነውና በጥበብ ስሙ ቦቢ ዋይን ተብሎ የሚጠራው ሮበርት ኪያጉላኒ የምረጡኝ ዘመቻን ለማቆም እንደተገደደ ተናገረ።

ለዚህ ውሳኔ ያበቃው ደግሞ የቅስቀሳ ቡድን አባላቱ ላይ ጥቃት በመበራከቱ ነው።

ቦቢ እንደሚለው መኪናው ተሳብሮበታል፣ የቅርብ ረዳቶቹም ላይ ጥቃት ደርሶባቸዋል።

ፖሊስ ደጋፊዎቹን በመደብደብና በማሰቃየት ላይ ይገኛል።

ጥይቶች መኪናው ላይ እንደተርከፈከፉበትና ለቅስቀሳ ከመኪናው ሲወርድ ጎማዎቹን እንደሚያተነፍሱበት፣ በሌሎች የእሱ አባላት ላይ የከፋ አደጋ እንደተጋረጠባቸው ተናግሯል።

በቅስቀሳ ቡድኑ አባላት የተሰራጨ አንድ ቪዲዮ ቦቢ ዋይን ቅስቀሳ ላይ ሳለ በቅርብ ርቀት አንድ ፈንጂ ሲፈነዳ ያሳያል።

በምሥራቅ ካምፓላ ካዩንጋ የቦቢ ደጋፊዎች አደባባይ በመውጣታቸው ፖሊስ በቆመጥና በአስለቃሽ ጭስ በትኗቸዋል።

አራት የቅስቀሳ ቡድን አባላቱም ክፉኛ ቆስለዋል ተብሏል።

ከአራቱ አንዱ የሙዚቃ ፕሮዲዩሰር የሆነው ዳን ማጂክ ሲሆን ፊቱ ላይ ጉዳት ደርሶበታል።

ቦቢ ዋይን ዛሬ ረቡዕ ወደ ምርጫ ኮሚሽን በመሄድ የምርጫ ቅስቀሳ ማድረግ ፈተና እንደሆነበት እንደሚያብራራ ለጋዜጠኞች ተናግሯል።

ከሁለት ሳምንት በፊት ቦቢ ዋይን በፖሊስ መታሰሩን በመቃወም ደጋፊዎቹ አደባባይ በመውጣታቸው 54 ሰዎች መሞታቸው ይታወሳል።

ፖሊስ ቦቢ ዋይንን አስሮት የነበረው ምርጫ ቅስቀሳ በሚያካሄድበት ወቅት ነበር።

ፖሊስ በቁጥጥር ሥር እንዲውል ካደረገው በኋላ ኮሮናቫይረስ በተዛመተበት ወቅት ቅስቀሳ አድርገሀል በሚል ክስ መስርቶበት ነበር።

ለጊዜው በዋስ እንዲለቀቅ ሆኗል።

በምርጫ ሰሞን የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ የጸጥታ ኃይሎች ተፎካካሪዎችን በማስቆምና በማንገላታት ይጠመዳሉ።

አሁንም ቢሆን ተፎካካሪዎች ቅስቀሳ እንዳያደርጉ ክልከላ ይደረግባቸዋል ይላሉ ታዛቢዎች።

ለረዥም ዓመታት ኡጋንዳን የመሩት ዩዌሪ ሙሴቬኒ እሑድ ዕለት በቴሌቪዥን ቀርበው ባደረጉት ንግግር የፖሊስን ተግባር አሞካሽተዋል።

ማንም ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም ሲሉም ተናግረዋል።

በጥር ወር ለሚደረገው ምርጫ የምረጡኝ ቅስቀሳው በመላው ዩጋንዳ ከተሞች እየተሟሟቀ ይገኛል።