ኡጋንዳዊው እንደራሴ እና የጥበብ ሰው ቦቢ ዋይን እንደገና ለእሥር ተዳርጓል

ኡጋንዳዊው እንደራሴ ቦቢ ዋይን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ኡጋንዳዊው እንደራሴ እና የጥበብ ሰው ቦቢ ዋይን

ከመንግሥት ጋር ዓይና እና ናጫ የሆነው ኡጋንዳዊው እንደራሴ እና የጥበብ ሰው ቦቢ ዋይን ከተፈታ ከቀናት በኋላ እንደገና ለእሥር ተዳርጓል።

ቦቢ ዋይን ዕለተ ሰኞ ነበር በሃገር መክዳት ክስ ተከሶ ለፍርድ ከቀረበ በኋላ ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶት በዋስ የተለቀቀው።

ነገር ግን የግለሰቡ ጠበቃ ቦቢ ዋይን ሐሙስ ምሽት ለዳግም እሥር መዳረጉን ለመገናኛ ብዙሃን አስታውቀዋል።

ጠበቃ ሮበርት አምስተርዳም ለቢቢሲ እንደተናገሩት «ምንም አንኳ ዳኛው ቦቢ ዋይን ፓስፖርቱን በእጁ እንዲይዝና ከሃገር ቢወጣም ምንም ጉዳት እንደሌለው ቢያሳውቁም ለሕክምና ለመሄድ ሲሞክር ነው አየር መንገድ ውስጥ የተያዘው።»

አክለውም «እየገፈታተሩ ወደ ፖሊስ መኪና አስገቡት፤ የት እንደወሰዱትም አናውቅም፤ ስጋት ላይ አንገኛለን» ሲሉ ቃላቸውን ሰጥተዋል።

በመዝገብ ስሙ ሮበርት ኪያጉላኒ በመባል የሚታወቀው ቦቢ ዋይን ሰኞ ዕለት ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ በክራንች ድጋፍ ሆኖ ታይቷል።

አጋሮቹ እንደሚሉት ፖሊስ ጣቢያ በነበረበት ወቅት ለፕሬዝደንቱ ቅርብ በሆኑ የጥበቃ ሰዎች ስቃይ ደርሶበታል።

የሃገሪቱ የጦር ኃይል ግን ውንጀላው መሠረተ ቢስ ነው ሲል አጣጥሎታል።

ለመሆኑ ቦቢ ዋይን ማን ነው?

አፍሮቢት በተሰኘው የሙዚቃ ስልት ጨዋታ የሚታወቀው ቦቢ ዋይን በኡጋንዳውያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይንት ያለው ሲሆን ከሙሴቬኒ መንግሥት ጋር ዓይን እና ናጫ ከሆነ ዓመታት ተቆጥረዋል።

የሙዚቃ ሕይወቱን ትቶ ወደ ሕዝብ ፖለቲካ ዓለም ከመጣ ወዲህም የሕዝብ እንደራሴ ሆኖ በመመረጥ ምክር ቤቱን ሲያስጨንቅ ቆይቷል።

ከ75 ዓመት በላይ የሆነው ግለሰብ ለፕሬዝዳንትነት መመረጥ የለበትም በሚልም ሕገ-መንግሥቱ እንዳይነካ ቢታገልም አልተሳካላትም።

የኡጋንዳ መንግሥት ፌስቡክና እና ዋትስአፕን የመሳሰሉ ማሕበራዊ ድር አማባዎች ሊቀረጡ ይገባል ብሎ ያወጣውን ሕግም በፅኑ ሲቃወም ቆይቷል።