አሜሪካ ፡ ዶናልድ ትራምፕ ከሥልጣን እንዲባረሩ ዲሞክራቶች ምክትላቸው ላይ ጫና እያሳደሩ ነው

አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲ

የአሜሪካ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ናንሲ ፔሎሲና ዲሞክራቶች ባለፈው ሳምንት ኮንግረስ ሲወረር ዶናልድ ትራምፕ የነበራቸውን ሚና ተከትሎ ከስልጣን እንዲያነሷቸው በምክትል ፕሬዝዳንት ማይክ ፔንስ ላይ ጫናቸውን አበርትተዋል።

የሕግ አውጪዎቹ ፔንስ ፕሬዝዳንቱን ለቢሮው ብቁ አለመሆናቸውን በማሳወቅ 25ኛ የሚባለውን የሕግ ማሻሻያ [አሜንድመንት] ተግባራዊ እንዲሆን እንዲጠይቁ ሃሳብ እንደሚያቀርቡ ይጠበቃል።

ምክትል ፕሬዝዳንት ፔንስ ግን ሀሳቡን ይቃወማሉ ተብሏል።

ፕሬዝዳንት ፔንስ ፈቃደኛ ካልሆኑ፣ ደጋፊዎቻቸውን ወደ ካፒቶል እንዲወጡ ጥሪ ያቀረቡት ትራምፕ እንዲከሰሱ ምክር ቤቱ ድምጽ ይሰጣል።

ሪፐብሊካኑ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ድምጽ ተጭበርብሯል የሚሉ ያልተረጋገጡ ክሶችን በመደጋገም የተካሄደውን የተቃውሞ ሰልፍ ተከትሎ በዴሞክራቶችና ቁጥራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሄደ ሪፐብሊካኖች ዘንድ አመጽ አነሳስተዋል በሚል ክስ እየቀረበባቸው ነው።

በጥቃቱ የካፒቶል ሂል ፖሊስ መኮንንን ጨምሮ አምስት ሰዎች ሞተዋል።

ትራምፕ ትዊተርን ጨምሮ ከበርካታ የማኅበራዊ ሚዲያ መድረኮች ታግደው ከነበሩበት ጊዜ ጀምሮ ምንም ዓይነት ይፋዊ መግለጫ አልሰጡም።

ዲሞክራቱ ጆ ባይደን ፕሬዝዳንት ሆነው ስልጣኑን ለመረከብና ትራምፕ ዋይት ሐውስ ለመልቀቅ ቀናት ብቻ ቀርቷቸዋል። ትራምፕ ቀናት በኋላ በሚደረገው የባይደን በዓለ ሲመት ላይ እንደማይገኙም ተናግረዋል።

ፔሎሲ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በላኩት ደብዳቤ እንዳሉት ፔንስ በሕገ-መንግሥቱ 25ኛ ማሻሻያ መሠረት ትራምፕን ከዋይት ሐውስ አስወግደው ተጠባባቂ ፕሬዝዳንት እንዲሆኑ ይጠይቃሉ።

ምክር ቤቱ ማክሰኞ ዕለት በውሳኔው ላይ ድምጽ ሊሰጥ ይችላል። ከዚያ በኋላ ፔንስና ካቢኔው ምክር ቤቱ ወደ ክስ ከመግባቱ በፊት እርምጃ እንዲወስዱ 24 ሰዓታት ይሰጣቸዋል።

"በፍጥነትነት እርምጃ እንወስዳለን ምክንያቱም ፕሬዝደንቱ ለሁሉም ስጋት ናቸው። በፕሬዝዳንቱ በዲሞክራሲያችን ላይ እየተፈፀመ ያለው ጥቃት በዘግናኝ ሁኔታ ተጠናክሮ በመቀጠሉ እርምጃው አስቸኳይ ሊሆን ይገባል" ብለዋል።

ምንም እንኳን ፔንስ እሁድ ዕለት የባይደን በዓለ ሲመት ላይ ለመሳተፍ ማቀዳቸውን በመግለጽ ራሳቸውን ከፕሬዚዳንቱ ያራቁ ቢመስሉም ከስልጣን እንዲነሱ ለማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው የሚያሳይ ምልክት ግን የለም።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሁለተኛው የሪፐብሊካኑ ሴናተር ፓት ቶሜይ ፕሬዚዳንቱ "ስልጣናቸውን መልቀቅና በተቻለ ፍጥነት መሄድ አለባቸው" በማለት የአላስካውን ሊዛ ሙርኮቭስኪን ተቀላቅለዋል።

ፔንስ በሃሳቡ ካልተስማሙስ?

የምክር ቤቱ ዴሞክራቶች በክሱ ለመግፋት ቃል ገብተዋል። ዲሞክራቶች በትራምፕ ላይ "አመፅን የማስነሳትን" ክስ ሊመሠርቱ ይችላሉ ብለዋል ፔሎሲ።

የአሜሪካ ከፍተኛ የሕግ አውጪዎች ትራምፕን በምክር ቤቱ ለመክሰስ የሚሰጠው ድምጽ እስከ ሳምንቱ አጋማሽ ድረስ ሊከናወን እንደሚችል ይናገራሉ። በዚህም ትራምፕ በአሜሪካ ታሪክ ሁለት ጊዜ ክስ የተመሠረተባቸው ብቸኛው ፕሬዝዳንት ሊሆኑ ይችላሉ።

ከዚያ ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲወገዱ ጉዳዩ የሁለት ሦስተኛ ድምጽ አስፈላጊ ወደ ሚሆንበት ሴኔት ይመራል። ጥፋተኛ ሆነው ከተገኙም ሴኔቱ ትራምፕ እንደገና የመንግሥት ስልጣን እንዳይዙ ለማድረግ ድምጽ ሊሰጥ ይችላል።

እስካሁን የትኛውም የሪፐብሊካን ሴናተር ትራምፕን በፈጸሙት ጥፋት ለመወንጀል ድምጽ እንሰጣለን አላለም። ዋይት ሐውስ እና ከፍተኛ ሪፐብሊካኖች ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን እንዲነሱ መፈለጉ "ፖለቲካዊ እርምጃ ነው" ያሉ ሲሆን "ታላቋን አገራችንን የበለጠ ለመለያየት ብቻ የሚያገለግል ነው" ሲሉም አጣጥለውታል።

ባይደን "ለረጅም ጊዜ ፕሬዝዳንት ትራምፕ ለሥራውን ብቁ አይደሉም" ብለው እንደሚያስቡ ቢገልጹም ከሥልጣን መነሳታቸው ጉዳይ ግን የኮንግረሱ ውሳኔ ነው ብለዋል።