'ትንሹ ሼፍ' በ14 ዓመቱ ሞተ

ቤን ዋትኪንስ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ "ማስተር ሼፍ ጁኒየር" የቴሌቪዥን ትእይንት እጅግ ተወዳጅ የነበረው ትንሹ ምግብ አብሳይ ቤን ዎኪንስ መሞቱ ተሰማ።

ቤን ገና በልጅነቱ ለሞት የበቃው በካንሰር ህመም ምክንያት ነው።

ትንሹን ቤን ለሞት ያበቃው ካንሰር በዓለም ላይ በጣም በጥቂት ሰዎች ላይ ብቻ የሚከሰት ነው። እንዲያውም ቤንን ጨምሮ 6 ሰዎች ብቻ ነበሩ በዚህ የካንሰር ዓይነት የተያዙት የሚሉ ዜናዎች ወጥተዋል።

ትንሹ ሼፍ ቤን ከዚህ ዓለም በሞት የተለየው ሰኞ ዕለት ነው ተብሏል። የሞቱ ዜና መሰማቱን ተከትሎ የእሱ አድናቂ የሆኑ መቶ ሺዎች ሐዘናቸውን ገልጸውለታል።

በዓለም ላይ ሚሊዮኖች የሚከታተሉት "ማስተርሼፍ" የቲቪ ትዕይንት ነበር ትንሹን ቤን እጅግ ገናና እንዲሆን ያስቻለው።

በፈረንጆች አቆጣጠር በ2018 በዚህ ተወዳጅ የምግብ አብሳዮች የአዳጊዎች ምድብ ውድድር ላይ የተመልካቾችን ቀልብ በእጅጉ የሳበው ቤን በዚያ ውድድር ገኖ ከወጣ በኃላ እሱ ራሱ ገናናና ጋዜጠኞች የሚከታተሉት ትንሹ ዝነኛ ሰው ሆኖ ቆይቷል።

ቤን የቺካጎ ከተማ አካባቢ ልጅ ሲሆኑ አባቱ ምግብ ቤት ነው የምግብ ማብሰል ጥበብን የተማረው።

ቤን ገና ልጅ ሳለ በአባቱ ሬስቶራንት ውስጥ ሒሳብ ተቀባይና አስተናጋጅ ሆኖ ማገዝ ከጀመረ በኋላ ወደ ማድቤት ጎራ እያለም የምግብ ማብሰል ጥበብን ከአባቱ ቀስሟል።

በአባቱ ምግብ ቤት ውስጥም የድኀረ ገበታ ጣፋጮችን (ዲዘርት) ያዘጋጅ ነበር። በተለይም የራሱን ዓይነት ኩኪስ፣ ብራውኒ፣ ሲናመን ሮልስ፣ ባናና ብሬድ ኬኮችን እየሰራ ያቀርብ ነበር። በዚህም የሬስቶራንት አዘውታሪዎችን ቀልብ ስቧል።

ትንሹ ሼፍ ቤን በቴሌቪዥን ተወዳድሮ ታዋቂ ከሆነ በኋላ በእኩዯቹም ሆነ በወላጆች ዘንድ በመላው ዓለም በስስት የሚታይ ልጅ መሆን ችሎ ነበር።

ኬክ የመጋገር ጥበቡን ከእናቱ እንደኮረጀ ይናገራል ቤን። " እሷ የምታውቀውን ምስጢር ሁሉ ነግራኛለች ወይም እኔ ስትሰራ ቀስ ብዬ ተመልክቻት ይሆናል" ሲል ተናግሮ ነበር።

ይሁን እንጂ ትንሹ ቤን እናትና አባቱን ያጣው በሚያሳዝን ሁኔታ ነው።

በ2017 አባቱ የቤንን እናትና ባለቤታቸውን ለይላ ኤድዋርድን ከገደሉ በኋላ ራሳቸውን አጥፍተዋል።

በአንድ ጊዜ ወላጆቹን በአስደንጋጭ ሁኔታ ያጣው ቤን ከዚህ በኋላ ያደገው ከአያቱና ከአጎቱ ጋር ነበር።

ይህን አሳዛኝ አደጋ ተከትሎ ነበር በፎክስ ቲቪ በሚቀርበው ማስተርሼፍ ጁኒየር ትዕይንት ላይ መቅረብ የጀመረው።

ወላጆቹን ያጣበት መንገድ ይታወቅ ስለነበር ተመልካቾች ቤንን በልዩ ፍቅር እንዲመለከቱት ሆነዋል።

ቤን የተወዳደረበት ማስተር ሼፍ ጁንየር አሸናፊ የሚሸለመው 100ሺ ዶላር ነበር።

ተወዳዳሪዎቹም ከ9 እስከ 13 ዓመት ብቻ የሆኑ አዳጊዎች ናቸው። ቤን ያን ውድድር ባያሸንፍም ያሳይ የነበረው መልካምነትና ቀናነት በሚሊዮን ተመልካቾች ልብ ውስጥ እንዲቀር አድርጎታል።

ቤን ካንሰር መታመሙ ከተሰማ ጀምሮ በርካታ ሰዎች ጤናው እንዲመለስ ጸልየውለታል። በየቀኑ እጅግ የበዙ የመልካም ምⶉት መግለጫዎች ከእኩዮቹና ከአድናቂዎቹ ይደርሱት ነበር።