ኢትዮጵያ፡ የዩኒቨርሲቲዎች መከፈት እና የተማሪዎች ስጋት

ደብረ ብርሃን ዩኒቨርሲቲ

የፎቶው ባለመብት, VW Pics

በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት ለበርካታ ወራት ተቋርጦ የነበረው የዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማሩ ሂደት በቅርቡ ይጀመራል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ከጥቅምት 23 እስከ 30/2013 ዓ.ም. ድረስ የመጀመሪያ ዙር የተማሪዎች ቅበለ እንዲጀምሩ መወሰኑ ይታወሳል።

ይህን ተከትሎ በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም ተስተውሎ የነበረው የጸጥታ ስጋት ከግምት በማስገባት የተማሪዎች ደህንነት ሁኔታ ስጋት ውስጥ የከተታቸው በርካቶች ናቸው።

ተማሪዎች ምን ይላሉ?

የአርባምንጭ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ለሆነችው ቃልኪዳን አባይነህ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ መወሰኑ ደስታን ፈጥሮላታል።

ላለፉት ስምንት ወራት በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምከንያት ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅላ ስትኖር የተለየ ጥንቃቄ ባለማየቷ ጊዜዋ እንደባከነ ተሰምቷታል።

እርሷ በምትማርበት ዩኒቨርስቲ ባለፉት ዓመታት ይህ ነው የሚባል የፀጥታ ችግር ተፈጥሮ ስላልነበረ የደህንነት ስጋት ባይገባትም፤ የሌሎች ዩኒቨርስቲዎች ሁኔታ ግን "አሁን ካለው የፖለቲካ ሁኔታ አንጻር ከዚህ በፊት ችግር ይፈጠርባቸው የነበሩ ዩኒቨርስቲዎች ላይ ስጋት አለኝ" ትላለች።

ሊቀሠራዊቱ ይመር ደግሞ የአምቦ ዩኒቨርስቲ ተማሪ ነው። ወደ ዩኒቨርሲቲ የመመለሱ ነገር ስጋት አሳድሮበታል።

ስጋት የሆነበት ነገር ደግሞ ባለፉት ዓመታት በተማሪዎች መካከል ችግር የፈጠሩ ጉዳዮች ምላሽ ሳያገኙ ወደ ዩኒቨርሲቲ መመለሱ ነው።

በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚከሰቱ ችግሮችን የሚቀሰቅሱና የሚዘውሩት በአገሪቱ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ ተዋናይ በሆኑ አካላት መሆኑን የሚናገረው ሊቀሠራዊቱ፤ እነዚህ ባለድርሻ አካላት ቁጭ ብለው ሳይወያዩና ልዩነቶቻቸውን ሳይፈቱ ወደ ዩኒቨርስቲ መመለሱ ስጋት ሆኖበታል።

የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ ፓርቲም በተመሳሳይ ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ ከማቅናታቸው በፊት የተማሪዎች ደህንነትን ለማረጋገጥ እና ግጭት እንዳይከሰት የሚመለከታቸው አካላት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቋል።

ፓርቲው የተቋረጠውን ትምህርት መልሶ ለማስጀመር በሚደረገው ዝግጅት የመማር ማስተማሩ ሥራ አመቺ የሆነ እና በአንጻራዊነትም ከግጭት ነጻ የሆነ ሁኔታን ለመፍጠር እንዲሰራ ጠይቋል።

የኦፌኮ ፓርቲ ሊቀመንበር እና ለበርካታ ዓመታት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና መንግሥት ከዚህ ቀደም በዩኒቨርሲቲዎች የጸጥታ ችግር አደረሱ የተባሉ ሰዎች ላይ የተወሰዱ እርምጃዎች ምን እንደሆኑ ማሳወቅ አለበት ይላሉ።

ፕሮፌሰር መረራ "አምና ከአማራ ክልል የመጡ ተማሪዎች ደምቢ ዶሎ ታግተዋል ተብሎ ሲወራ ነበር። እስከ አሁን ምንም የተባለ ነገር የለም። አሁንም ከዚያ ክልል የሚመጡ ተማሪዎች ወደዚያ መሄድ ይሰጋሉ። ከዚህም ወደዚያ ለመሄድ እንደዚያው" ይላሉ።

እንደ ፕሮፌሰር መረራ ከሆነ ዘንድሮ መንግሥት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የጸጥታ ችግር እንዳይከሰት ምን አይነት ዝግጅት እንዳደረገ ማሳወቅ አለበት።

ፕሮፌሰር መረራ አክለውም ዘንድሮ ምርጫ ስለሚካሄድ የፖለቲካ ትኩሳቱን እንደሚባባስ ገልጸው መንግሥት ከአሁኑ ቢያስብበት መልካም ነው ብለዋል።

መንግሥት በበኩሉ የዩኒቨርሲቲ ደህንነቶችን ለማረጋገጥ ከፌደራል ፖሊስ ጋር እንደሚሰራ አስታውቋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ደቻሳ ጉርሙ በዩኒቨርስቲዎች አካባቢ የሚፈጠሩ የፀጥታ መደፍረሶች በተቋማቱ የፀጥታ ኃይል ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ከፌደራል ፖሊስ ጋር እየሰሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በያዝነው ወር መጨረሻ ላይ ተማሪዎች ተቀብለው ሥራቸውን የሚጀምሩትን የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሰላምና ደህንነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስልጠና መሰጠት እንደተጀመረም አቶ ደቻሳ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን አመራሮች እና የፖሊስ አባላትን ያካተተው ስልጠናው የመማር ማስተማር ሂደት ሊያውኩ ይችላሉ የተባሉ ስጋቶች ላይ ውይይት መደረጉን ተናግረዋል።

ለበርካታ ወራት ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ያለምንም መስተጓጎልና ችግር እንዲቀጥል ከወዲሁ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት አቶ ደቻሳ፤ በጥበቃ እንዲጠናከሩና በቴክኖሎጂ እንዲታገዙ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲ ጊቢዎች ውስጥ የጥበቃ ስራውንም ለማጠናከር የደህንነት ካሜራ ለመጠቀምም ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን ጨምረው ተናግረዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ ደቻሳ የፌደራል ፖሊስ ለዩኒቨርሲቲዎች ጥበቃ ሳይሆን የሚያደርገው የዩኒቨርስቲዎችን ጥበቃ ያጠናክራል ብለዋል።

ዩኒቨርስቲዎች በቁጥር ብዙ መሆናቸው እና አንድ ዩኒቨርስቲም በርከት ያሉ ካምፓሶች እንደሚኖሩት አስታውሰው የፌደራል ፖሊስ የእነዚህን ዩኒቨርስቲዎች ጥበቃ ሁኔታ እንደሚያጠናክር ይናገራሉ።

"አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ እገዛ ያደርጋሉ አላስፈላጊ ሲሆን ወደ መደበኛ ስራቸው ይመለሳሉ" ሲሉም የፌደራል ፖሊስ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፀጥታ ሁኔታ ውስጥ የሚኖረውን ተሳትፎ ተናግረዋል።