ኢሬቻ ፡ በበዓል ላይ ጥብቅ የደኅንነት ቁጥጥር እንደሚደረግ ተጠቆመ

ኢሬቻ በዓል አከባበር

ነገ እና ከነገ ወዲያ በአዲስ አበባ እና ቢሾፍቱ ከተሞች በሚከበረው ዓመታዊው የኢሬቻ በዓል ላይ ጥብቅ የደኅነነት ቁጥጥር እንደሚደረግ ተጠቆመ።

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ በዓሉ ወደ ብጥብጥ ለመቀየር አቅደው እና ተዘጋጅተው በአራቱም አቅጣጫ የሚንቀሳቀሱ አካላት ስላሉ በዚህም ምክንያት አስፈላጊው ቅድመ ጥንቃቄ እየተደረገ መሆኑን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ትናንት በቢሾፍቱና በአዲስ አበባ ከተሞች በርካታ ሕዝብ ታድሞበት ከሚከበረው የኢሬቻ በዓል ጋር በተያያዘ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጥቃቶች ለመፈጸም፣ ግጭትና ትርምስ ለመፍጠር ሲያቅድ የነበረ ቡድን በቁጥጥር ሥር እንዲውል አድርጊያለሁ ማለቱ ይታወሳል።

የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ባልቻ ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ስላለ ወደ አዲስ አበባ ከተማ የሚያስገቡ መንገዶች ላይ ጥብቅ ፍተሻ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ባለፉት ሁለት ቀናት ወደ አዲስ አበባ ከተማ የተጓዙ ሰዎች በመንገድ ላይ በርካታ ጊዜ ለፍተሻ መቆማቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ለምሳሌ ከአምቦ ወደ አዲስ አበባ በሚወስደው 120 ኪሎ ሜትር በሚረዝመው መንገድ ላይ 8 ጊዜ መፈታሻቸውን ተጓዦች ገልጸዋል።

የኢሬቻ በዓልን ለማክበር ከምሥራቅ ሐረርጌ ተነስቶ ወደ አዲስ አበባ የተጓዘ አንድ ወጣት ደግሞ መንገድ ላይ ለበርካታ ጊዜ በተደጋጋሚ መንገድ ላይ እንዲቆሙ እተደረጉ መፈተሻቸውን ተናግሯል። ይህ ወጣት የክልሉ ጸጥታ አስከባሪዎች አንዳንድ ሰዎች በቁጥጥር ሥር ሲያውሉ መመልከቱንም ጨምሮ ተናግሯል።

አቶ ጌታቸው ይህ ፍተሻ የበዓሉን ደኅንነት ለማረጋግጥ ታስቦ የሚደረግ መሆኑን ጠቅሰው፤ "ወደ አዲስ አበባ እንዳይገባ የተከለከለ ሰላማዊ ሰው ግን የለም" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ከዛሬ ጀምሮም ዝግ የሚደረጉ የአዲስ አበባ ጎዳናዎች መኖራቸው ተነግሯል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ ትናንት የኢሬቻ በዓል ላይ ረብሻ ለመፍጠር ሲዘጋጁ ነበር ያሏቸውን ከ500 በላይ ሰዎችን መያዛቸውን አስታውቀዋል።

ከተጠርጣሪዎቹ በተጨማሪ የጦር መሳሪያዎች እና በርካታ የእጅ ቦምቦች መያዛቸውን ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጨምረው ተናግረዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት በዓሉ ላይ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር ከዚህ ቀደም ይታደሙ ከነበሩ ሰዎች ቁጥር አንጻር ሊቀንስ እንደሚችል ተጠቁሟል።

መንግሥት እስካሁን በዚህ በዓል ላይ መታደም ያለበት ሰው ቁጥር ይህን ያክል ነው አለማለቱን የኦሮሚያ ክልል ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።

"መታደም ያለበት ሰው ቁጥር ይህን ያክል ነው ማለቱ የመንግሥት ድርሻ አይደለም። ይህን የሚወስኑት አባ ገዳዎች ናቸው" ብለዋል።

አባ ገዳዎች ከሌሊቱ 11 ሰዓት ጀምሮ ሰዎች ምስጋናቸውን የሚያቀርቡበትን ቦታ ይከፍታሉ ከዚያ በኋላ የፈለገ ወደ ውሃው ዳርቻው ሄዶ ምስጋናውን ማቅረብ ይችላል ብለዋል።

አባ ገዳ ጎበና ሆላ "የጸጥታውን ጉዳይ የጸጥታ ሰዎች፤ የጤናውን ጉዳይ ደግሞ የጤና ሰዎች እንዲያስፈጽሙ ተስማምተናል" ብለው ነበር።

የአርቲስት ሃጫሉን ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በርካታ ሰዎች በበርካታ ቁትር ተጠጋግተው አደባባይ የወጡባቸው ብዙ አጋጣሚዎች መከሰታቸውን ተከትሎ በኦሮሚያ ክልል የቫይረሱ ስርጭት በ500 በመቶ መጨመሩን አቶ ጌታቸው ያስታውሳሉ።

በዚህም ምክንያት የበዓሉ ተሳታፊዎች እራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ለመጠበቅ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስዱ መልዕክት አስተላልፈዋል።