የአውሮፓ ሕብረት ቱርክ ላይ ማዕቀብ እጥላለሁ ሲል አስጠነቀቀ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ ሕብረት ቱርክ በምስራቅ ሜደትራኒያን ከግሪክ ጋር እየፈጠረችው ባለችው “ጠብ አጫሪ እንቅስቃሴ እና ጫና” ምክንያት ማዕቀብ ልጥልባት እችላለሁ ሲል አስጠነቀቀ።
ቱርክ እና ግሪክ በምስራቅ ሜደትራኒያን በባህር ድንበር እና የኃይል ምንጭ ጋር በተያያዘ አለመግባባት ውስጥ ከገቡ ሰነባብተዋል። የአውሮፓ ሕብረት ኮሚሽን ፕሬዝደነት ኡራሱላ ቮን ደር ላየን ቱርክ በምስራቅ ሜደትራኒያን እየወሰደች ካለችው የአንድ ወገን እርምጃ መቆጠብ አለባት ሲሉ አሳስበዋል።
ቱርክ በፈረንጆቹ 2020 መጀመሪያ ላይ የነዳጅ ክምችት ለማሰስ የይገባኛል ጭቅጭቅ ወደሚያስተናግደው ምስራቅ ሜደትራኒያን መርከብ መላኳን ተከትሎ በቱርክ እና በግሪክ መካከል ውጥረት ኃይሏል።
ግሪክ እና ቱርክ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን- ኔቶ አባላት ቢሆኑም በድንበር እና የውሃ ክፍል ይገባኛል በሚሉ ምክንያቶች በተደጋጋሚ ግጭት ውስጥ ይገባሉ። የአውሮፓ ሕብረት የአባል አገር ለሆነችው ግሪክ ድጋፉን ሲግልጽ ቆይቷል።
የአውሮፓ ሕብረት ፕሬዝደንቷ በብራሰልስ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የአውሮፓ ሕብረት ከቱርክ ጋር መልካም እና ገንቢ የሆነ ግንኙነት እንዲኖረው ይሻል፤ በዚህ ደግሞ ትልቁ ተጠቃሚ የቱርክ መንግሥት ነው ብለዋል።
ቱርክ በቀጠናው እየፈጠረች ያለችውን ጫና እና ከጠብ አጫሪ እንቅስቃሴዋ የማትቆጠብ ከሆነ፤ የአውሮፓ ሕብረት ያሉትን ሌሎች አማራጮች ይመለከታልም ብለዋል።
የሕብረቱ አባል አገራት መሪዎች ውይይት ካደረጉ በኋላ ቱርክ ከዚህ እንቅስቃሴዋ የማትቆጠብ ከሆነ ማዕቀብ እንዲጣልባት መስማማታቸው ተጠቁሟል። የኦስትሪያው ቻንስለር ሴባስቲያን ኩርዝ በትዊተር ገጻቸው ቱርክ ዓለም አቀፍ ሕጎችን መተላለፍ የምትቀጥል ከሆነ ሕብረቱ ማዕቀብ ይጥላል ብለዋል።
ቱርክ እና የአውሮፓ ሕብረት ከዚህ ቀደምም መልካም የሚባል ግነኙነት የላቸውም። ቱርክ የሕብረቱ አባል ለመሆን ለዓመታት ጥረት ስታደርግ የቆየች ቢሆንም ጥረቷ ግን ፍሬ ሳያፈራ ዓመታት አልፈዋል።
ሕብረቱ ቱርክ የሰብዓዊ መብት ጥስት ተፈጽማለች ይላል። በተለይ እአአ 2016 የረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን መንግሥትን ለመፈንቀል ሞክረዋል ተብለው በተወነጀሉ ሰዎች ላይ ቱርክ የወሰደችው እርምጃ ከሕብረቱ ጋር ቅራኔ ውስጥ ከትቷታል።
ቱርክ ምንም እንኳ ከሕብረቱ ጋር ጥሩ የሚባል ግንኙነት ባይኖራትም ለአውሮፓ ሕብረት አገራት ወሳኝ አገር ሆና ቆይታለች። ቱርክ መዳረሻቸውን አውሮፓ ማድረግ የሚሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ስደተኞች ይዛ ትገኛለች።
ሰደተኞች ወደ ግሪክ እንዳይሻገሩ ይዛ ለመቆየትም ቱርክ ከአውሮፓ ሕብረት ጋር ከስምምነት ደርሳለች።














