ጥቁር አሜሪካዊቷ ላይ 32 ጥይት የተኮሱት ፖሊሶች አይጠየቁም መባሉ ተቃውሞ አስነሳ

የአሜሪካ ፖሊሶች

የፎቶው ባለመብት, Reuters

መጋቢት ወር ላይ በቤቷ ውስጥ እያለች የተገደለችው ጥቁር አሜሪካዊቷ የጤና ባለሙያ ብሪዮና ቴይለርን ተኩሰው ገድለዋታል የተባሉት ፖሊሶች በግድያ ወንጀል አይጠየቁም በማለት ፍርድ ቤት መወሰኑን ተከትሎ በአሜሪካ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

ሶስት ፖሊሶችም 32 ጥይትም ተኩሰዋል ተብሏል።

በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰልፈኞች ውሳኔውን ለመቃወም በወጡባት በአሜሪካ ሉዚቪል ከተማም ሁለት ፖሊሶች ተተኩሶባቸዋል ተብሏል።

ከወራት በፊት ነበር የሉዚቪል ከተማ ሦስት ፖሊሶች ሌሊት ላይ የ26 ዓመቷ ብሪዮና ቴይለር ቤት ያመሩት፤ በወቅቱ ከወንድ ጓደኛዋ ጋር ተኝታ ነበር።

ዕፅ በማዘዋወር የጠረጠሩት የቀድሞ ጓደኛዋ የእሷን አድራሻ ሊጠቀም ይችላል በሚልም ነበር በሌሊት ቤቷን ሊፈትሹ ፖሊሶች የመጡት።

በሌሊትም ምንም ሳያሰሙ በሩን ገንጥለው የገቡትን ፖሊሶች ማንነት ያላወቀው የወንድ ጓደኛዋ ሌቦች መስለውት መተኮሱ ተነግሯል።

የያዘውም ሽጉጥ ፈቃድ ያለው ነበር። በወቅቱ የተተኮሰው ጥይትም ከፖሊሶቹ መካከል አንደኛውን እግሩ ላይ መትቶ ማቁሰሉ ተነግሯል።

ሆኖም በምላሹ ፖሊሶች በተኮሱት 32 ጥይቶች የጥቁር አሜሪካዊቷ ወጣት የጤና ባለሙያ ህይወት አልፏል።

በግርግሩ ወቅት በድንገት ከእንቅልፏ የተነሳችው ብሪዮና በቤቷ ውስጥ ኮሪደር ላይ እያለች በተተኮሰባት ተደጋጋሚ ጥይት ለሞት ተዳርጋለች።

ፖሊሶቹ የያዙት የእስር ማዘዣ ሳያንኳኩ እንዲገቡ የሚፈቅድ ነው ቢባልም በትናንትናው ዕለት እንዲህ አይነት የፍርድ ቤት ወረቀት እንዳልያያዙ ተገልጿል።

ጎረቤቶችም ቢሆኑ ፖሊሶቹ ማንነታቸውን ሳያሳውቁ በውድቅት ሌሊት በር ሰብረው እንደገቡ ለአገሪቱ ሚዲያ ተናግረዋል።

በቤቷ ምንም አይነት አደንዛዥ ዕፅ ያልተገኘ ሲሆን፤ የጀፈርሰን ግዛት ዐቃቤ ሕግ ቶማስ ዋይን በበኩላቸው ከተኩሱ በኋላ ፍተሻው እንዲቀር ተወስኖ ነበር ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ፖሊሶቹ ብሪዮና ከተገደለች በኋላ ክስተቱን አስመልክቶ ባቀረቡት ሪፖርት ምንም ጉዳት እንዳልደረሰ፤ በሩን ገንጥለው ቢገቡም ኃይል አልተጠቀምንም ብለዋል።

የብሪዮና ጓደኛ ዋከር በፖሊስ ላይ የግድያ ሙከራ በማድረግ ተከሶ የነበረ ቢሆንም በኋላ በነበረው ውዝግብ የተነሳ ክሱ ውድቅ ሆኗል።

በትንትናው ዕለት ብሬት ሃንኪሰን የተባለው ፖሊስ በአካባቢው መኖሪያ ቤቶች ላይ ጥይት በመተኮሱ ነዋሪውን አደጋ ውስጥ ከቷል በሚል ቢከሰስም በብሪዮና ግድያ ማንም ተጠያቂ አይሆንም ተብሏል።

ሁለቱ ፖሊሶች ደግሞ ምንም ክስ አይመሰረትባቸውም መባሉ በርካቶችን አስቆጥቷል።

ብሪዮና

የፎቶው ባለመብት, Facebook

የሉዚቪል ከተማ ፖሊስ ኃላፊ ሮበርት ሽሮደር በተቃውሞው የተተኮሰባቸው ፖሊሶች አደጋ ከባድ እንዳልሆነና ህይወትንም አደጋ ውስጥ የሚከት እንዳልሆነ ተናግረዋል። ተጠርጣሪውም በቁጥጥር ስር ውሏል ብለዋል።

በከተማዋ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የተጣለ ሲሆን የአገሪቱ መከላከያ ኃይልም ተሰማርቷል።

የከተማዋ ከንቲባ ግሬግ ፊሸር ከምሽቱ ሦስት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ አይቻልም በሚል ለሦስት ቀናት የሚቆይ የሰዓት እላፊ አዋጅን አሳውቀዋል።

ሆኖም በርካታ ተቃዋሚዎች ይህንን በመተላለፍ ለብሪዮና ፍትህ እየጠየቁ ነው።