ጥቁር አሜሪካዊ ታዳጊን የገደለው ፖሊስ እንዳይከሰስ ተወሰነ

የፎቶው ባለመብት, FACEBOOK
በአሜሪካ ሴንት ልዊስ ከተማ አቃቢ ሕግ ጥቁሩን ወጣት የገደለው ፖሊስ ላይ ክስ አልመሰርትም አለ።
ማይክል ብራውን የተባለው ወጣት በፈርጉሰን የተገደለው የዛሬ 6 ዓመት በፈረንጆቹ 2014 ላይ ነበር።
ፖሊስ ይህን ታዳጊ ተኩሶ ከገደለው በኋላ በአሜሪካ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሶ ነበር።
"የጥቁር ነፍስ ዋጋ አለው" የሚል ቁጭትን የያዘው "ብላክ ላይቭስ ማተር" የተሰኘው ሕዝባዊ እንቅስቃሴ የተጀመረውን የዚህ ወጣት በፖሊስ በግፍ መገደልን ተከትሎ ነበር።
አቃቢ ሕግ እንደሚለው አምስት ወራትን የፈጀው ድጋሚ ምርመራ ዳረን ዋልሰን የተባለው የፖሊስ መኮንን ወጣቱን በእንዝህላልነት ስለመግደሉ በቂ መረጃን አላስገኘም።
በ2015 በእነርሱ አቆጣጠር የፍትሕ መስሪያ ቤቱ በሰጠው የመጀመሪያ ውሳኔ ፖሊሱ በዚህ ወጣት ላይ የተኮሰው ራሱን ለመከላከል እንጂ ልጁን ለመግደል አልነበረም ሲል ደምድሟል።
በአደጋው ላይ ያን ቀን በትክክል ምን እንደደረሰ ፖሊስ፣ የአይን እማኞችና የሟች ቤተሰቦች የሚሰጡት ምስክርነት የተጣረሰ ነው።
በትክክል የሚታወቀው ነገር ቢኖር በነሐሴ 9/2014 የፖሊስ መኮንኑ ዊልሰን የፖሊስ መኪናውን እያሽከረከረ ይህንን ልጅና ጓደኛውን በመንገድ ሲሄዱ እንዳገኛቸው ነው።
ከደቂቃዎች በኋላ የ18 ዓመቱ ብራውን ሞተ። ፖሊሱ ሰባት ጥይት አርከፍክፎበት ነበር። ሬሳው ለአራት ሰዓታት ከዚያው መንገድ አልተነሳም።
ይህ ዊልሰን የተባለው ፖሊስ 12 ጥይቶችን ተኩሷል። ከእነዚህ ውስጥ 8ቱ ወጣቱ ብራውንን ሳይገኙት አልቀሩም።
አንድ ምስክር እንደሚለው ደግሞ ብራውን እጅ ወደ ላይ ሲባል እጁን ወደ ላይ አድርጎ ነበር። ምርመራው ደግሞ ያን እንዳላደረገ ያሳያል።
ማይክልን የገደለው ፖሊስ በአንድ ወቅት ለኤቢሲ ቴሌቪዥን እንደተናገው ወጣቱን እጅ ወደ ላይ ብሎ የፖሊስ መኪና ውስጥ ሊያስገባው ሲሞክር እንደታገለውና ብሎም በቡጢ እንደነረተው፣ በኋላም ሽጉጥ ቢደግንበትም ወጣቱ አሻፈረኝ ብሎ ሽጉጡን ሊቀማው እንደነበረ ተናግሯል።
በልጁ ላይ የተኮሰውም የገዛ ነፍሱን ለማዳን እንደነበረ አብራርቶ፤ በፈጸመው ድርጊትም አንዳች ጸጸት እንደማይሰማውም ተናግሯል በዚያ ቃለ ምልልስ።
ዞሮ ዞሮ እውነቱ ማን ጋር እንዳለው አይታወቅም።
ይህ ክስተት ከፍተኛ ቁጣ ቀስቅሶ ቆይቶ ብላክ ላይቭስ ማተር የተሰኘውን እንቅስቃሴ ወልዷል።
የልጁ መገደል ሳያንስ የፖሊስ መኮንኑ እንዳይከሰስ መወሰኑም ሌላ ቁጣን ቀስቅሶ ቆይቷል። በተቃውሞው ሁለት ፖሊሶች በፈርጉሰን ከተማ በረብሻው መሐል ተተኩሶባቸው ቆስለዋል።
ይህን ከፍተኛ ተቃውሞ ያስነሳውን ግድያ ለመመርመር ድጋሚ ሥራ ከተጀመረ ቆይቷል፤ በዚህ ሁለተኛ ምርመራ ውጤትም አቃቢ ሕግ የፖሊስ መኮንኑን ላለመክሰስ ወስኗል።
ምክንያቱ ደግሞ ያለጥርጥር ፖሊሱ የተኮሰው ልጁን ለመግደል ነው ወይ? የሚለው በማያሻማ ሁኔታ ሊረጋገጥ ባለመቻሉ ነው።
"ያለምንም ጥርጥር ፖሊሱ በእንዝህላልነት የግድያ ወንጀል ስለመፈጸሙ ማረጋገጥ ይቻላል? መልሱ አይቻልም ነው፤ ስለዚህ ፖሊሱን ዊልሰንን ልንከሰው አንችልም" ብለዋል አቃቢ ሕግ ዊስሊ ቤል።
አቃቢ ሕግ ጨምረው እንዳሉት ፖሊሱ ዊልሰን ወጣቱን ማይክል ብራውንን አለመግደል ግን ይችል ነበር። ቢያንስ ሁኔታውን በሌላ መልኩ ሊቆጣጠር ቢሞክር ይህ ወጣት ባልሞተ ነበር።
ይህ የአቃቢ ሕግ ውሳኔ የተሰማው በሜኔሶታ ባለፈው ግንቦት የጆርጅ ፍሎይድ በሌላ ፖሊስ በግፍ መገደል ተከትሎ የተነሳው ተቃውሞ ሙሉ በሙሉ ባላባራበት ጊዜ ነው። ምናልባት በቀጣይ ቀናት ተቃውሞው በድጋሚ ይቀሰቀስ ይሆናል የሚል ስጋት ተፈጥሯል።
ወጣቱ ማይክል ብራውን ከመሞቱ ከሁለት ቀናት በኋላ ኮሌጅ ለመግባት በዝግጅት ላይ ነበር።















