የአሜሪካ ምርጫ፡ ትራምፕ፤ ባይደን "የአሜሪካን ሕልም ይቀጫል" ሲሉ አስጠነቀቁ

Trump accepts nomination

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የዴሞክራት ፓርቲ ዕጩው ጆ ባይድን 'በቀጣዩ ምርጫ የሚያሸንፍ ከሆነ የአሜሪካን ሕልም ይቀጫል' ሲሉ ተናገሩ።

በሪፐብሊካን ፓርቲ ብሔራዊ ስብሰባ ላይ ተገኝተው ንግግር ያሰሙት ፕሬዝደንቱ ተቀናቃኛቸውን 'የአሜሪካን ታላቅነት የሚያወድም' ሲሉ ገልፀዋቸዋል።

የአሜሪካ ሁለቱ አውራ ፓርቲዎች ወደ ምርጫ ከማምራታቸው ጥቂት ወራት አስቀድሞ ሞቅ ደመቅ ያለ ብሔራዊ ስብሰባ ያከናውናሉ።

ጆ ባይደንን ለፕሬዝደንትነት ያጩት ዴሞክራቶች ባለፈው ሳምንት ስብሰባቸውን በኮሮናቫይረስ ምክንያት በቴሌቪዥኝ ሥርጭት ብቻ እንዲሆን አድርገው ነበር።

በዚህ ሳምንት ተራው የሪፐብሊካን ነው። ለሦስት ተከታታይ ምሽቶች የዘለቀው ብሔራዊ ስብሰባ ሐሙስ ምሽት ተገባዷል።

በዚህ ስብሰባ መቋጫ ላይ ንግግር ያሰሙት ፕሬዝደንት ትራምፕ፤ ዴሞክራቶች በአሜሪካ ከተሞች አጥፊዎችን በማሰመራት ውድመት ያመጣሉ ሲሉ ወቅሰዋል።

ሁለቱ ዕጩዎች ከዚህ ቀጥሎ ወደ ክርክሮች ያመራሉ። አንዳቸው ስለአንዳቸው መልካም ማውራት የማይቀናቸው ዕጩዎች በክርክሮቹ ላይ አፍ እላፊ ይነጋገራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ፕሬዝደንቱ ምን አሉ?

ሐሙስ ዕለት ለደጋፊዎቻቸው የምረጡኝ ድምፅ ያሰሙት ፕሬዝደንት ትራምፕ የአገራቸውን ኢኮኖሚ ያደቀቀውን የኮሮናቫይረስ ወረረሽኝ ድምጥማጡን እንደሚያጠፉት ቃል ገብተዋል።

በርካቶች በተገኙበት በፓርቲያቸው በይፋ የታጩት ዶናልድ ቀጣዩ ምርጫ "የአሜሪካን ሕልም የምናድንበት አሊያም ሶሻሊስት አጀንዳ ያላቸው መጥተው እንዲቀጩት የምንፈቅድበት ነው" ሲሉ ተደምጠዋል።

"ድምፃችሁ ሕግ የሚያከብሩ አሜሪካውያንን ሊያድን ይችላል፤ አለበለዚያ ግን በጥባጭ፣ አክራሪ ወንጀለኞች ዜጎቻችን እያስፈራሩ የሚኖሩበት ይሆናል።"

ትራምፕ አመፀኛ ተቃዋሚዎች የሚሏቸው በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብላክ ላይቭስ ማተር [የጥቁሮች ሕይወት ዋጋ አላት] በሚል አደባባይ ለተቃውሞ የወጡ አሜሪካውያንን ነው። ተቃዋሚዎቹ ትራምፕ ንግግር በሚያሰሙበት ወቅት ዋይት ሐውስ በር ላይ ድምፃቸውን ሲያሰሙ ነበር።

ምንም እንኳ ትራምፕ ይህን በመፍራት በዋይት ሐውስ ዙሪያ አዲስ አጥር ቢያስገነቡም የተቃዋሚዎቹ ጩኸትና የመኪና ድምፅ አልፎ አልፎ ይሰማ ነበር።

ባለፈው ሳምንት ስብሰባ ያደረጉት ዴሞክራቶች አሜሪካን የዘር መድልዎ ያለባት፤ ማኅበረሰባዊና ምጣኔ ሃብታዊ እኩልነት ያልሰፈነባት አድርገዋል ስለዋል በማለት የወቀሱት ፕሬዝደንቱ "አገራችንን እያወደሙ ያሉት ዴሞክራቶች አገር እንምራ ሲሉ አያፍሩም?" ሲሉ ጠይቀዋል።

የዋሽንግተን ከተማ መገናኛ ብዙሃን የትራምፕ ስብሰባ ላይ ከ1500 በላይ እንግዶች ተገኝተዋል፤ የተቀመጡትም በጣም ተጠጋግተው ነው ሲሉ ዘግበዋል።

አልፎም እንግዶቹ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ አለማድረጋቸውንም ፅፈዋል።

በስብባው ላይ የፕሬዝደንቱ ልጅና የዋይት ሐውስ አማካሪ ኢቫንካ ትራምፕ ንግግር አድርገዋል። ሌሎችም ነባር የትራምፕ አስተዳደር ሰዎች ዲስኩር አሰምተዋል።

አንድ ሰዓት ገደማ የፈጀ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝደንቱን እስካሁን ያስመዘገቧቸውን ድሎች እያነሱ ራሳቸውን ሲያደናንቁ ተስተውለዋል። በየመሃሉ ደግሞ ተቀናቃኛቸው ጆ ባይደንን ሲያብጠለጥሉ አምሽተዋል።

የፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ ምክትል የነበሩት ጆ ባይደን በትዊተር ገፃቸው ላይ "ዶናልድ በእኔ ዘመን ደህንነት አይሰማችሁም ይላል። እስቲ እንደው እስቲ አሁን ምን ዓይነት ደህንነት ይሰማችኋል?" ሲሉ ተፎካካሪያቸውን በነገር ወጋ አድርገዋል።