ካናዳ ፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ በተደጋጋሚ የግድያ ዛቻ የሚደርሳቸው ለምንድነው?

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የካናዳ ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ቱሩዶ በየቀኑ የሚደርሳቸው የሞት ዛቻ ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩ ተነገረ።
እንደ ካናዳ ፖሊስ መረጃ ከሆነ ከጥር እስከ ሐምሌ ድረስ ብቻ 130 የግድያ ዛቻዎች ደርሷቸዋል።
ባለፈው ዓመት በእነዚሁ የወራት ልዩነት ጊዜ ይህ የዛቻ ቁጥር ከመቶ አላለፈም ነበር።
ባሳለፍነው ሐምሌ ወር አንድ መሣሪያ የታጠቀ ጎልማሳ ጠቅላይ ሚኒስትር ቱሩዶ የሚኖሩበትን ቤት ዋና መግቢያ ጥሶ መኪናውን አቁሞ ሲንጎማለል በቁጥጥር ሥር ውሏል።
ጠቅላይ ሚኒስሩ ቱሩዶና ባለቤታቸው ይፋዊ መኖርያ ቤታቸው እየታደሰ ስለሆነ አሁንም እየኖሩ ያሉት በጊዜያዊነት በዝነኛው ሪዶ ሆል (Rideau Hall) ሪልስቴት ቅጥር ግቢ ውስጥ ነው። ይህ ሥፍራ የካናዳ ጠቅላይ ገዥ የጁሊ ፓየት ይፋዊ መኖርያ ነው።
ጁሊ የእንግሊዟ ንግሥት ዳግማዊት ኤልሳቤት የካናዳ ወኪል ሆና ታገለግላለች።
ኢንስቲትዩት ፎር ስትራቴጂክ ዳያሎግ የተሰኘ ተቋም ባወጣው ሌላ መረጃ ደግሞ በጠቅላይ ሚኒስትር ቱሩዶ ላይ ቀኝ አክራሪዎች በማኅበራዊ ሚዲያ ውይይቶቻቸው መካከል ከሙስሊም ጠልነትና ከአይሁድ ጠልነት አጀንዳዎች ቀጥሎ የሚወያዩት ጀስቲን ቱሩዶን ነፍስ ማጥፋት ላይ ነው።
ጀስቲን ትሩዱ በቀኝ አክራሪዎች የማኅበራዊ ድር አምባ ላይ 11.4 ከመቶ ርዕሰ ጉዳይ ሆነው የሚነሱ ሰው ሲሆኑ በየትዩብ ላይ ደግሞ ይህ አሐዝ 28 በመቶ ከፍ ይላል። ይህም አሐዝ የሚያሳየው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቀኝ አክራሪዎች ጥቃት ኢላማ መሆናቸውን ነው።
ለምን ባልተለመደ ሁኔታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀኝ አክራሪዎች ዒላማ ተደረጉ፣ ለምንስ ተደጋግሞ የግድያ ዛቻ ይደርሳቸዋል ለሚለው የጥናት ቡደኑ የሚከተለውን ብሏል።
የቀኝ አክራሪዎች የሚያስተሳስሯቸው ሁለቱ ትልልቅ አጀንዳዎች ፀረ እስልምናና ፀረ መጤነት በተለይም ጸረጥቁር መሆናቸው ነው። ሙስሊሞችና ጥቁሮች በካናዳ በሰላም መኖራቸው ቀኝ አክራሪዎችን የሚያንገበግቧቸው ጉዳዮች ናቸው።
እነዚህ እንዲሆኑ ያስቻሉት ደግሞ ቱሩዶ ናቸው ብለው ያምናሉ። ግራ ዘመም ፖለቲከኞች በተለይ የቱሩዶ ሊበራል ፓርቲ ለኢስላምና ለጥቁር መጤዎች የሚያሳየው ቀናኢ ስሜት ቀኝ አክራሪዎችን እንቅልፍ ነስቷቸዋል ይላል ሪፖርቱ።
ከዚህ በተጨማሪ ቀይ አክራሪዎች ከሙስሊምና አይሁድ ጠልነትም ባሻገር "ቢሊየነሩ ጆርጅ ሶሮስ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር በድብቅ ብዙ ጥቁሮችን ወደ ካናዳ በስደተኛ መልክ አስርጎ በማስገባት ካናዳን የጥቁሮች አገር ለማድረግና ነጩን ከምድረ ገጽ ለማጥፋት እየሰሩ ነው" ብለው ጭብጥ የሌለው የሴራ አዳብረዋል።















