ኮሮናቫይረስ ፡ 'በጦርነት አድጌ በወረርሽኝ አልሞትም"

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
"በጦርነት ነው ያደግኩት፤ በወረርሸኙ አልሞትም።"
ማርጋሬት አልኮክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ጊዜ ጀርመን በእንግሊዝ ላይ ያደረሰችው "ዘ ብሊትዝ" ተብሎ የሚጠራው የቦምብ ጥቃት በመጠለያ ውስጥ ሆነው ያን ፈታኝ ጊዜ አልፈውታል ።
ከዚያም ባሕር፣ ውቅያኖስ ተሻግረው ወደ አውስትራሊያ ተወሰዱ።
ላኪ ማርቲን እባላለሁ፤ የ89 ዓመቷ ማርጋሬት አያቴ (ናና) ናት ያንን የጦርነት ጊዜ በጨለምተኝነት አታወሳውም፤ በተቻለ መጠን ሳቅና ቀልድ በተሞላበት መልኩ ነው ጦርነትን የመሰለ አስከፊ ነገር የምታወራው።
ስለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝም እንዲሁ በቀልድ ነው የምታወራው።
"አንዳንዴ በምን ተአምር ነው እንዲያው እዚህ ወረርሽኝ ላይ የጣለኝ፤ እንዴት በህይወት እያለሁ ይሄን አየሁ" ትለኛለች ስደውልላት።
ከዚያም ትቀጥልና "የከፋ ነገር ስላየሁ ወረርሽኙ ብዙም አያስጨንቀኝም" ትለኛለች።
በጥር ወር ላይ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በአውስትራሊያ ሲያጋጥም አያቶቼ የአረጋውያን መንከባከቢያ ማዕከል በመሆናቸው ወላጆቼም ሆነ እኔ ከበሽታው እንደሚጠበቁና ምንም እንደማይነካቸው እርግጠኛ ነበርን።
ነገር ግን ግምታችን የተሳሳተ ነበር በአምስት ወራት ውስጥ በአውስትራሊያ ከተከሰተው 247 ሞቶች መካከል 156ቱ በአረጋውያን እንክብካቤ ማዕከል ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በርካታ አረጋውያንም ሊያልቁ የቻሉበት ምክንያትም የጤና ሥርዓቱ እነዚህን ተጋላጭ የኅብረተሰቡ ክፍሎችን ችላ በማለቱ ነው ተብሎ እየተተቸ ነው።
በተለያየ የስልጣን እርከን ደረጃ ላይ የሚገኙ ኃላፊዎችም ለዚህ ክፍተት መፈጠር ጥያቄዎች እየቀረቡላቸው ነው።

የፎቶው ባለመብት, LUCY MARTIN
በአውስትራሊያ ውስጥ 180 ሺህ ያህል አረጋውያን በእንክብካቤ ማዕከል ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ ማዕከላት በእርዳታ ድርጅቶች፣ በግል ኩባንያዎችና በመንግሥት መስሪያ ቤቶች የሚተዳደሩ ናቸው።
የወረርሽኙን መከሰት ተከትሎ እነዚህም ማዕከላት በፍጥነት ነው ለይቶ ማቆያ ውስጥ ያስገቧቸው።
አንዳንዶቹም መንግሥት ካስተላለፈው መመሪያም በማፈንገጥ እንግዶች እንዳይጎበኙ አረጋውያኑም በክፍላቸው ብቻ እንዲቆዩና ሌሎች እንቅስቃሴዎችንም እንዳያደርጉ ሲከለክሉ ቆይተዋል።
ማርጋሬት ያሉበት ማዕከል ለተወሰነ ጊዜ ጎብኚዎችን ቢከለክሉም በግቢው ውስጥ እንደፈለጉ እንዲንቀሳቀሱና መውጣትም ስለፈቀዱላቸው እድለኛ ናቸው።
ሌላኛዋ የ87 ዓመቷ አያቴ፤ የእሷም ስም በሚገርም ሁኔታ ማርጋሬት ነው፤ ከመጋቢት ጀምሮ በክፍሏ ውስጥ ናት። ማዕከሉ በሜልቦርን የሚገኝ ሲሆን፤ ይህች ከተማም የወረርሽኙ ማዕከል ሆናለች።
አያቴ በክፍሏ ተወስና ነው ያለችው፤ የሚፈቀድላት በኮሪደሩ ላይ እንድትራመድ ብቻ ነው። ለወራትም ያለ ጎብኚ ብቻዋን ትበላለች፤ ወንበሯ ላይ ቁጭ ብላ ነው የምታሳልፈው።
እንዲያም ሆኖ በዚህ አስጨናቂ ሰዓት በማዕከሉ እያገለገሉ ላሉ ሠራተኞች ምስጋናዋ ከፍ ያለ ነው።
"እንዲህ ተዘግቶ መቀመጥ ከባድ ቢሆንም ተቀብየዋለሁ፤ ከሁሉ በላይ ለእኔ ደኅንነትም ነው" ትለናለች።
"ብዙም አልጨነቅም። ቤተሰቦቼን አለማየቴ ከባድ ቢሆንም እዚህ አይደሉም ማለት ግን አይወዱኝም ማለት አይደለምም" በማለት ስሜታችንን ትነካዋለች።

የፎቶው ባለመብት, LUCY MARTIN
እሷ ያለችበትን ማዕከል የሚያስተዳድረው ኩባንያ በሁሉም ነገር ዝግጁ እንደሆነ አሳውቆናል። ጥብቅ የሆነ የጽዳት ቁጥጥርን ጨምሮ፣ ወረርሽኙን ለመከላከል የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን በከፍተኛ መጠን አከማችቷል።
ነገር ግን በተለያዩ ሁለት ግዛቶች የሚገኙ ማዕከላት የቫይረሱን መዛመት መቆጣጠር አቅቷቸው በርካታ አረጋውያን ረግፈዋል፤ ይህም ሁኔታ ለቤተሰቦቻቸው ልብ ሰባሪ ሆኗል።
እነዚህ አረጋውያን በቫይረሱ በቀላሉ እንደሚጠቁና፣ ተጋላጭም እንደሆኑ ማወቅ የሮኬት ሳይንስ አይደለም።
በርካታዎቹ አረጋውያን ሌላ ተደራራቢ ህመሞች ያሉባቸው ሲሆኑ በማዕከላቱም ውስጥ ያለው የህክምና አገልግሎት የተወሰነ ነው።
ከዚህም በተጨማሪ የማዕከሉ ሠራተኞችም በተለያዩ ቦታዎች ከመስራታቸውም አንፃር ቫይረሱን በቀላሉ ያዛምታሉ።
በየካቲት ወር ላይ በአውሮፓ በሚገኙ ማዕከላት ውስጥ ያሉ አረጋውያን በሚያሰቅቅ ሁኔታ እንደ ቅጠል እየረገፉ እንደሆነ ታሪኮች መውጣት ጀመሩ።
ይህም ሁኔታ በአውስትራሊያ ሊያጋጥም እንደሚችል አገሪቷ ማወቅ ነበረባት የሚሉት በሞናሽ ዩኒቨርስቲ የጤና ሕግ ክፍል ኃላፊ ጆ ኢብራሂም ናቸው።
"የአውስትራሊያ ምላሽ በቂ አልነበረም። ለሚመጣው ነገር በሙሉ ዝግጁ አልነበረችም እናም አሁን የተፈጠረው ክስተት ሊያስደንቀን አይገባም" ይላሉ ።

"ብዙ ሰዎች ይህ መሆኑ አይቀሬ ነበር ሲሉ ይሰማል። ይሄ ግን ትክክለኛ አይደለም፤ ምክንያቱም ምንም ማድረግ አንችልም ነበር የሚለውን ትርጉም ስለሚሰጥ ነው። የኮሮናቫይረስ በአረጋውያን ላይ ምን ያህል አደጋ እንደደቀነ ከግምት ውስጥም አላስገባነውም። በሌሎች አገሮች ላይ እያለቁ የነበሩትንም አረጋውያን መረጃዎች አላጤንነውም" ይላሉ።
በመጋቢት ወር ላይ በሲድኒ የሚገኝ ዶሮቲ ሄንደርሰን ሎጅ የተባለ የአረጋውያን ማዕከል ሠራተኛ በኮሮናቫይረስ መያዟ ተረጋገጠ፤ በግንቦት ወርም 21 በማዕከሉ የሚኖሩ አረጋውያንና ሠራተኞችም ተያዙ። ከእነዚህም ውስጥ ስድስቱ ሞቱ።
ሌላ እንዲሁ በሲድኒ ውስጥ የሚገኝ ኒውማርች የተባለ ማዕከልም በኮሮናቫይረስ የተያዙ ህሙማንን ወደ ጤና ማዕከል ከመላክ ይልቅ ክፍላቸው ውስጥ እንዲዘጉ አደረገ። ማዕከሉ የሠራተኞች ዕጥረት እንዲሁም የኮሮናቫይረስ መከላከያ ቁሳቁሶችም በበቂ ሁኔታ አልነበሩትም። ይህንንም ተከትሎ 19 አረጋውያን ሲሞቱ በርካቶችም በቫይረሱ ተያዙ።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአረጋውያኑ መሞት በርካታ ጥያቄዎችን ቢያጭርም ይህ ለምን እንደተከሰተ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጥ አካል አልተገኘም።
አሁንም ከክስተቱ ያልተማረችው አውስትራሊያ አረጋውያኗን በኮሮናቫይረስ እያጣች ነው።
የቪክቶሪያ ግዛት እንደ አዲስ ወረርሽኙ እያገረሸባት ሲሆን ከማህበረሰቡ ስርጭት በተጨማሪ የአረጋውያኑ የእንክብካቤ ማዕከላት በከፍተኛ ሁኔታ እየተጠቁ ነው።
በአሁኑ ወቅትም 1 ሺህ 200 የሚሆኑ አረጋውያን በ97 ማዕከላት ውስጥ መያዛቸው ተረጋግጧል።
ፕሮፌሰር ኢብራሂም እንደሚሉት የእንቅስቃሴ ገደቦች ብቻቸውን ቫይረሱን መግታት አይችሉም።
"በሽታው ቢያጋጥም ምን ማድረግ አለብን የሚለው ላይ የተቀመጠ ግልጽ ያለ ፖሊሲም ሆነ ይህንንም መቆጣጠር የሚችል መዋቅር አልተዘረጋም" ይላሉ።
የአረጋውያኑን የእንክብካቤ ማዕከላት በቀጥታ የሚመለከተው የፌደራል መንግሥቱን ቢሆንም ወረርሽኙን ደግሞ በየግዛቱ ያሉ የኅብረተሰብ ጤና ኃላፊዎች በበላይነት ይቆጣጠሩታል።
"በዚህም ምክንያቱ ኃላፊነቱ የማን ነው በሚል መወዛገብ ተፈጠረ። ይሄ ብቻ አይደለም የኮሮናቫይረስ ህሙማን ህክምናው መሰጠት ያለበት ሆስፒታል ወይስ ቤታቸው ውስጥ የሚለውም ላይ ውሳኔ ሳያገኝ እንዲሁ እያወዛገበ ነበርም" በማለት ያስረዳሉ።
የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ አንቶኒ አልባኔዝ በዚህ ሳምንት ሰፋ ያለ ምርመራና ኃላፊነት ሊወስዱ የሚባቸውም አካላት እንዲጠየቁ ተናግረዋል።
"በኒውማርች እንክብካቤ ማዕከል ካጋጠመን ክስተት ለምን አልተማርንም? ይህ የተከሰተው ከወራት በፊት ነበር" በማለትም ይጠይቃሉ።
በሜልቦርን የግዛቲቷና የፌደራል ኤጀንሲዎች ተጣምረውም በቪክቶሪያ የተከሰተውን የወረርሽኝ ቀውስ ለመቆጣጠር ጥረት እያደረጉ ነው።
ለፕሮፌሰር ኢብራሂም ግን ዋናው ነገር ብሔራዊ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ በአውስትራሊያ የሚገኙ የእንክብካቤ ማዕከላት ሁኔታ ሊገመገም እንዲሁም ቁጥጥር ሊደረግበት ይገባል ይላሉ።
"በዚህም መንገድ ነው የትኞቹ ማዕከላት አደጋ ውስጥ እንዳሉ የምንረዳው" የሚሉት ፕሮፌሰሩ አክለውም "ከዚያ በመቀጠልም ያለምንም ማንገራገር ፈጣንና የማያዳግም እርምጃ ሊወሰድ ይገባል" በማለትም ምክራቸውን ለግሰዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በእንክብካቤ ማዕከላቱ የተፈጠረውንም ሁኔታ የሚያጣራ የመንግሥት ቡድንም ተቋቁሟል።
ከተለያዩ ቦታዎች የተገኙ መረጃዎች እንደሚያስረዱትም ለእነዚህ አረጋውያን መሞት ዋነኛ ምክንያቶች በማዕከላቱ የሚገኙ ሠራተኞች እጥረት እና በቂ ስልጠና አለማግኘት የሚጠቀሱ ናቸው።
ከዚህም በተጨማሪ የኮሮናቫይረስ የመከላከያ ቁሳቁሶች እጥረትና የጤና ኃላፊዎች ምላሽ መዘግየት ይገኙበታል።
የአውስትራሊያ ህክምና ማኅበር በበኩሉ መንግሥትን ተጠያቂ አድርጓል፤ ጥብቅ ምርመራም ያስፈልጋል እያለ ነው።
በቪክቶሪያ የሚገኘው ቅርንጫፉ ፕሬዚዳንት ጁሊያን ራይት ለናይን ጋዜጣ እንደተናገሩት ቀውሱ "የተገመተውን አሳዛኝ ክስተት ጥሎ አልፏል" እንዳሉ አስነብቧል።
በቪክቶሪያ የሚገኙ በርካታ አረጋውያን በኮሮናቫይረስ መሞታቸው አይቀሬ እንደሆነ የአውስትራሊያ ጤና ቢሮ ፀሐፊ ብሬንዳን መርፊ ከሰሞኑ ተናግረዋል።
ውድ አያቶቼ በእነዚህ ማዕከላት አለመገኘታቸው እድለኛ ነኝ። አሁንም የሚገኙባቸው የእንክብካቤ ማዕከላት ከኮሮናቫይረስ ነፃ ናቸው።
አንደኛዋ አያቴ ማርጋሬት ጎብኚም አያያትም፤ ሌላኛዋ አያቴ ማርጋሬትን ግን በሳምንት አንዴ እንድናያት ተፈቅዶልናል፤ እናቴም ቅዳሜ እለት ሄዳ ነበር።
ለረዥም ጊዜያት ሳቁ፣ ተቃቀፉ፣ ቀልድም ጣል እያደረጉ ኮሮናቫይረስ እንዳለ ዘነጉት።
አያቴ ናና ቫይረሱ ከያዛት መሞቻዬ ነው ብትልም እንዲህ በቀላሉ እጅ አልሰጥም ትላለች።
"ህፃን እያለሁ ዳክዬዎች አባረሩኝ ግን አልደረሱብኝም፤ አሁንም ኮሮናቫይረስ ይይዘኛል የሚል ግምት የለኝም" ብላ አስቃናለች።














