መርዛማ ሊድን አጋልጣ 423 ሚሊዮን ብር ያገኘችው ፊሊስ ኦሚዶ

የፎቶው ባለመብት, CJGEA
ፊሊስ ኦሚዶ ኬንያዊት የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ናት። እንደ ጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር 2009 ላይ ለምትሠራበት ድርጅት ስጋቷን ስትገልጽ፤ ይህን ጉዳይ ዳግመኛ እንዳታነሺ ተብላ ነበር።
ፊሊስ ትሠራበት የነበረው ድርጅት የሚያካሂደው የባትሪ መልሶ ጥቅም ላይ (ሪሳይክሊንግ) ሂደት የሰዎችን ሕይወት ሊቀጥፍ እንደሚችል ነበር ለአሠሪዎቿ የተናገረችው። ነገር ግን ሰሚ ጆሮ አላገኘችም።
በአሠሪዎቿ “ዝም በይ” ብትባልም ፊሊስ አልሰማቻቸውም።
ያኔ 31 ዓመቷ ነበር። ገና ከዩኒቨርስቲ እንደተመረቀች ሞምባሳ የሚገኝ ‘ኬንያ ሜታል ሪፈረንስስ’ የሚባል ድርጅት ውስጥ ተቀጠረች።
ድርጅቱ የመኪና ባትሪን መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ሊድ የተሰኘውን ንጥረ ነገር ያመርታል።
መርዛማ ጭስ
ፊሊስ የድርጅቱ ክንውኖች አካባቢ ላይ ሊያደርሱ የሚችሉትን ተጽዕኖ እንድታጠና ተጠይቃ ነበር። ሆኖም ግን ግኝቷን ለድርጅቱ ስታሳውቅ እርምጃ ከመውሰድ ይቆጠባሉ።
ባትሪ የማቅለጥ ሂደቱ አየር ከመበከሉም በላይ ተረፈ ምርቱ የሚጣለው በድርጅቱ አቅራቢያ የሚገኘው የኦዊኖ ማኅበረሰብ መኖሪያ አካባቢ ነው።
ድርጅቱ የአካባቢውን አየርም ውሀም እየበከለ ነበር። ሠራተኞቹ ላይም ጉዳት ደርሷል።
ከልጅነቷ ጀምሮ ተፈጥሮን የምትወደው ፊሊስ፤ 2009 ላይ ችግሩ ምን ያህል ስር የሰደደ እንደሆነ አልተረዳችም ነበር።
ፊሊስ የ15 ዓመት ወጣት ሳለች እናቷ ከሞቱ በኋላ ወደ ሞምበሳ አቀናች።
ዩኒቨርስቲ ስትገባ መማር የምትፈልገው የአካባቢ ጥናት ነበር። ሆኖም የቢሮ ሠራተኛ የሚያደርጋት ዘርፍን ማጥናት ግድ ሆነባት።
ምንነቱ ያልታወቀው ህመም
በቢሮ ሠራተኛነት የተቀጠረችበት ድርጅት እሷ ለምትወደው ነገር ደንታ አልነበረውም። ፊሊስም ቅሬታዋን ይዛ በድርጅቱ መሥራት ቀጠለች።
2010 ላይ የሁለት ኣመት ልጇ ታመመ። የተለያዩ ሕክምናዎች ቢሰጡትም፤ ህመሙ ሊታወቅለች፣ ሊያገግምም አልቻለም።
የልጇ ህመም ተባብሶ ሆስፒታል አልጋ ያዘ። ያኔ አንድ ጓደኛዋ ልጇ በሊድ ተመርዞ ከሆነ እንድታስመረምረው መከረቻት።
ምርመራ ሲደረግለት ደሙ ውስጥ ከፍተኛ የሊድ መጠን ተገኘ። ልጇ ጡት ሲጠባ ለንጥረ ነገሩ ተጋልጦ እንደሆነ ስትረዳ እጅግ ተደናገጠች።
ተበሳጭታ ሥራዋን ለቀቀች። ከዛም ድርጅቱ የልጇን የሕክምና ወጪ እንዲሸፍን መጎትጎት ጀመረች።
ማኅበረሰቡ ውስጥ ከሚኖሩ ልጆች ሦስቱ ምርመራ እንዲደረግላቸው ገፋፍታ ያገኘችው ውጤት ፍርሀቷን እውን ያደረገ ነበር።
“ውሸትሽን ነው”
ፊሊስ የምርመራ ውጤቶቹን ይዛ የመንግሥት ተቋሞች ጣልቃ እንዲገቡ ደብዳቤ መጻፍ ጀመረች።
ቢሆንም ምላሽ እንዳልሰጧት ትናገራለች።
“ብሔራዊ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም የማወራው ነገር ውሸት እንደሆነና ፍርድ ቤት ብሄድም ራሳቸውን ለመከላከል ዝግጁ እንደሆኑ ጻፉልኝ” ስትል ትገልጻለች።
ለድርጅቱ ፍቃድ እንዲሰጥ ያደረገው ይህ የአካባቢ ጥበቃ ተቋም ነው።

የፎቶው ባለመብት, GOLDMAN ENVIRONMENTAL PRIZE
ፊሊስ ያላት እውነተኛ መረጃ እንደሆነ ለማሳየት ከአካባቢ ጥበቃ ተሟጋች ድርጅት ጋር በመጣመር ተጨማሪ ምርመራዎች እንዲካሄዱ አደረገች።
ማስረጃ ቢኖራትም የመንግሥት ባለሥልጣኖች ጫና ሊያሳድሩባት ሞክረዋል።
“ቀስ በቀስ ነበር የምንቀሳቀሰው። ሥራችን በበጎ ፍቃድ ላይ የተመሠረተ ነበር። በኢ-ፍትሐዊ መንገድ ስታሰር ለዋስ የምከፍለው ገንዘብ እንኳን አልነበረኝም። 17 ሰዎች በዋስ እንድወጣ አደረጉ።”
2012 ላይ ሞምባሳ ውስጥ የተቃውሞ ሰልፍ ካስተባበች በኋላ፤ ግጭት ለመቀስቀስ ሞክረሻል ተብላ ለአንድ ምሽት ታስራ ነበር።
‘ፍሮንት ላይን ዲፌንደርስ’ እና ‘ኢስት አፍሪካን ሎው ሶሳይቲ’ የተባሉ የሕግ ጉዳዮች የተራድኦ ድርጅቶች ፊሊስ ክሱን እንድትከላከል የገንዘብ ድጋፍ ሰጥተዋል።
ኋላ ላይ የሰልፉ አስተባባሪዎች ላይ ማስረጃ ባለመገኘቱ ክሱ ተቋረጠ።
ድብደባ
ፊሊስ ከ204 በፊት የነበረውን ጊዜ “በጣም ከባድ” ስትል ትገልጸዋለች። ትግሏን ለማቀረጥ የተቃበረችበት ወቅት እንደነበረም ታስታውሳለች።
ከመንግሥት ባለሥለጣኖች የሚደርሳት ማስፈራሪያ ያስጨንቃት ነበር። ቤቷ በር ላይ ማንነታቸው ባልታወቁ ወንዶች ድብደባ ደርሶባት ለአንድ ወር ተደብቃም ነበር።
“ሲደበድቡኝ ጎረቤቴ ስለደረሰ ነው የተረፍኩት። ተደብድቤ የተጣልኩበት ቦታ የመኪናው መብራት ሲበራ ልጄ እየጮኸ ነበር።”
የፊሊስ ቤተሰቦች ልጇ ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድር ነገር ውስጥ እንደገባች በማሰብ፤ በተፈጠረው ነገር ደስተኛ አልነበሩም።
እሷ ግን የሚተማመኑባትን የማኅበረሰቡ አባላት ችላ ማለት አልፈለገችም።
በተለይ 2011 ላይ ማኅበረሰቡ ውይይት አድርጎ ሲጨርስ ፖሊሶች አስለቃሽ ጭስ የተኮሱባቸውን ጊዜ አትዘነጋም።
“አደገኛ እፅ እየፈለግን ነው በሚል ሰበብ የሰዎች ቤት ላይ ጉዳት አደረሱ። ትንሽ ገቢ ያላቸው ድሆች አሉ። የነሱን ቤት ከሚጎዱ እኔን ቢያስሩኝ ይሻለኝ ነበር።”
ካሳ
ፊሊስን መሰናክሎቹ አላስቋሟትም። ማኅበረሰቡን ለመታደግ ለዓሥር ዓመታት ያለመታከት ፍድድ ቤት ቆማ ታግላለች።
በስተመጨረሻም ድል ቀንቶት፤ ፍርድ ቤቱ 12 ሚሊዮን ዶላር (423 ሚሊዮን ዶላር ገደማ) ካሳ አግኝታለች። ካሳውን የሚከፍሉት አካባቢ ያለ እየደረሰ የነበረውን ጉዳት ችላ ያሉ የመንግሥት ተቋሞች እና የመኪና ባትሪ መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውለው ድርጅት ነው።
ፍርድ ቤቱ አካባቢው በአራት ወር ውስጥ እንዲጸዳም ውሳኔ አስተላልፏል። ውሳኔው ካልተተገበተ ሌላ ቅጣት ይጠብቃቸዋል።
“ገንዘቡ 3000 የሚሆኑት የማኅበረሰቡ አባለት ያዩትን ስቃይ አይተካም። ሆኖም ግን ገንዘቡ ለሕምናና መድኃኒት መግዣ ይውላል” ብላለች።
ከዚህ ቀደም በፍርድ ቤት የተበየኑ የካሳ ክፍያዎች በአፋጣኝ ተጎጂዎች እጅ እንዳልገቡ ስለምታውቅ፤ ፊልሰን ትግሉ እንዳልተቋጨ ትናገራለች።
እስከ መስከረም አጋማሽ የካሳ ገንዘቡ እጃቸው ካልገባ ዝም እንደማትልም ታስረግጣለች።












