የቁማሩ ጌታ በ98 ዓመታቸው አረፉ

ስታንሊ ሆ

የፎቶው ባለመብት, AFP/GETTY

ስታንሊ ሆ ይባላሉ። ቢሊየነር ነበሩ። ማካዎ ከተማን የዓለም የቁማር ማዕከል ያደረጓት እርሳቸው ናቸው። ዛሬ በ98 ዓመታቸው መሞታቸው ተሰምቷል።

መካዎ በደቡብ ቻይና ጠረፍ የምትገኝ ራስ ገዝ ከተማ ናት። ከሆንግ ኮንግ 60 ኪሎ ሜትር ትርቃለች። ይቺ ከተማ ለ440 ዓመታት የፖርቹጋል ቅኝ ነበረች። ሕዝቧም 600 መቶ ሺህ ብቻ ነው።

ከፍተኛ ገቢዋ ሕጋዊ ቁማር ማጫወት ሲሆን በዓመት 3 ቢሊዮን ዶላር ታገኝበታለች። መካዎ በይበልጥ "የእሲያዋ ላስቬጋስ" በሚል ትታወቃለች።

ስታንሊ ሆ ታዲያ ይቺን ከተማ የፈጠሩ ሰው ተብለው ይሞካሻሉ። ኋላ በእሲያ አህጉር ከእውቅ ሀብታሞች ተርታ ሊመደቡ ያስቻላቸውን ሀብት ያጋበሱትም ከዚሁ ነው።

ኤስ ኤም ጂ ሆልዲንግስ የተባለውን ትልቁን አቋማሪ ድርጅት የመሰረቱትም አርሳቸው ናቸው።

የዚህ ኩባንያ ዋጋ አሁን 6 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል።

እጅግ ቀበጥ፣ ዳንስና ዝነጣን ወዳጅ የነበሩት ስታንሊ ሆ ለቤተሰባቸው ቁማር መጥፎ እንደሆነ ዘወትር መካሪ ነበሩ።

የስትንሊ ሆ ሴት ልጅ ፓንሲ ሆ "አባቴ ዛሬ በሆንግ ኮንግ ከተማ በሰላም አርፏል" ስትል መርዶውን ለዓለም ሚዲያ አርድታለች።

ሆ የካዚኖ ቁማር ንግድን በቀድሞው የፖርቱጋል ቅኝ ግዛት በነበረችው መካዎ ውስጥ የጀመሩት ከመንግሥት ድርጅቱን በመግዛት ነበር።

የቁማር ቢዝነሱ ከፍተኛ አዱኛ ይዞ ሲያመጣ ንግዱን ወደ ፖርቱጋልና ሰሜን ኮሪያ አስፋፍተውታል። ሰውየው በሆንግ ኮንግ ሰማይ ጠቀስ ህንጻዎችንም አስገንብተዋል።

በፈረንጆቹ በ2018 ጡረታ ሲወጡ የስታንሊ ሆ ሀብት 6.4 ቢሊየን ዶላር አልፎ ነበር። ሰውየው ጡረታ የወጡት ታዲያ በ97 ዓመታቸው ነው።

ስታንሊ ሆ በዚያች 'የሃጥያት' ከተማ ብቻ 20 የካዚኖ ማስቆመርያ ድርጅቶች አሏቸው። ድርጅታቸው በቻይና ውስጥም በሌሎች ቢዝነሶች ከፍተኛ ትርፍ ያጋብሳል።

ቢሊየነሩ ስታንሊ ሆ የእኔ ብለው የተቀበሏቸው 17 ልጆች አሏቸው። በይፋ 4 ሚስቶችንም አግብተዋል።

የቻይና መገናኛ ብዙሃን የሆን ሞት "የጀግናው ቢዝነስ ሰው ሞት" ሲሉ ነው የዘገቡት።

ማካዎ ከስታንሊ ሆ በፊት አሳ የሚጠመድባት ትንሽዬ የገጠር ከተማ እንደነበረች ይነገራል።

ስታንሊ ሆ ቆማሪዎቻቸውን ከሆንግ ኮንግ የሚያመላልሱበት አነስተኛ ጀልባዎችና ሄሊኮፕተሮችም ነበሯቸው።