ኮሮናቫይረስ፡የአሜሪካ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጉባኤ የህፃናትን ወሲባዊ ጥቃት በሚያሳይ ቪዲዮ ተጠለፈ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
በካሊፎርኒያ የሚገኝ አንድ ቤተክርስቲያን ዙም የሚባለውን የቪዲዮና የድምፅ መነጋገሪያ መተግበሪያን ከሰሞኑ እንደሚከስ አስታውቋል።
ለክሱ ምክንያት የሆነውም መተግበሪያውን በመጠቀም ሲደረግ የነበረውን የቪዲዮ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ጠላፊዎች የህፃናትን ወሲባዊ ብዝበዛ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በመለጠፋቸው ነው።
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናቱ ተሳታፊ የሆኑትን ሰዎች ኮምፒውተሮች በመጥለፍ "የሚረብሹና የሚዘገንኑ ቪዲዮዎችን" መለጠፋቸውንም በቅዱስ ጳውሎስ ሉተራን የክስ ወረቀት ያስረዳል።
የሳንፍራንሲስኮ ቤተ ክርስቲያን ኃላፊ አባላትም በወቅቱ የዙምን ኩባንያ እርዳታ ለመጠየቅ ቢሞክሩም ድርጅቱ ግን ለማስቆምም ምንም አለማድረጉን ክሱ ጠቁሟል።
የዙም ኩባንያ ቃለ አቀባይ ባወጡት መግለጫ "ይህ አሰቃቂ ተግባር ነው" በማለት አውግዘውታል።
"በዚህ አፀያፊ ተግባር ተፅእኖ ለደረሳባቸው ሁሉ ሃዘኔታችን ይድረሳቸው" ያለው ኩባንያው "ጠለፋው ደረሰ በተባለበት ቀን ወንጀለኞች በመከታተል ያገኘናቸው ሲሆን፤ መተግበሪያው እንዳይጠቀሙ ሙሉ በሙሉ ከማገድ በተጨማሪ መረጃቸውንም ለሚመለከታቸው ባለስልጣናት አስተላልፈናል" ብሏል።
ኩባንያው ከሰሞኑ የመተግበሪያው ደህንነት ለመጠበቅ የተለያዩ ማሻሻያዎች ማድረጉን ጠቅሶ፤ በተጨማሪም የዙም ተጠቃሚዎች ለስብሰባውም ሆነ ጉባኤውን ለመሳተፍ የሚያስፈልጉ የይለፍ ቃሎችን (ፓስወርድ) በሚስጥራዊነት ሊጠብቁ ይገባል ሲል መክሯል። የተለያዩ የቤተክርስቲያን ቡድኖች የይለፍ ቃሎችን ለሁሉም ሰው ዝም ብለው እንደሚያጋሩም ኩባንያው ገልጿል።
በኮሮናቫይረስ ምክንያት እንቅስቃሴዎችም ሆነ ስብሰባዎች ላይ ገደብ መጣሉን ተከትሎ በርካታ ሰዎችን በስብሰባም ሆነ በጉባኤ ለማሳተፍ ለሚፈልጉ የተለያዩ ተቋማትም ሆነ ቡድኖች ዙም ተመራጭ መተግበሪያ ሆኗል።
ሆኖም ተፈላጊነቱ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምርም ከደህንነትና የግል መረጃን ከመጠበቅ አንፃር በርካታ ጥያቄዎች እየተነሱበት ነው። 'ዙምቦምቢንግ' በሚልም መጠሪያ በርካታ ጠላፊዎች ስብሰባዎችን በመጥለፍ ዘረኛ ስድቦችን፣ እንዲሁም ወሲባዊ ይዘት ያላቸው ቪዲዮዎችን እያጋሩም ይገኛሉ።
በሳንፍራንሲስኮ የሚገኘው ጥንታዊው የቅዱስ ጳውሎስ ቤተክርስቲያን ባቀረበው ክስ ላይ አንደኛው ጠላፊው ከዚህ ቀደም የሚታወቅና "ወሲባዊ ጥቃቶችን" ያደረሰ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተደጋጋሚም ባለስልጣናቶችን አሳውቀው እንደነበር ጠቅሰዋል።
ስምንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ተሳታፊዎቹ አብዛኛዎቹ ጡረተኞች ሲሆኑ ኮምፒውተራቸውን በመጥለፍ ልቅ ወሲብ የሚያሳዩ ቪዲየዎች ተለቀውባቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, Zoom
"ቪዲዮዎቹ አሰቃቂና አፀያፊ ናቸው። ህፃናትና ጨቅላዎች ላይ በትልልቅ ሰዎች አማካኝነት የወሲብ ተግባር ሲፈፀምባቸው፤ ወሲባዊ ጥቃትና ብዝበዛም ሲያስተናግዱም ይታያል" ብሏል ክሱ።
ተሳታፊዎቹ ቪዲዮውን ለማስቆም ቢሞክርም እንደገና ይጀምራል፤ እናም ጠላፊው በተደጋጋሚ ጥቃት አድርሷል።
ቤተ ክርስቲያኗ ለደረሰባት ጉዳት፣ ውል በመጣስ እንዲሁም ያልተገባ የንግድ አሰራር በሚልም ዙም ካሳ እንዲከፍል ጠይቃለች።














