ኮሮናቫይረስን እየተከላከልን በጥንቃቄ ምርጫ እናደርጋለን፡ ዶ/ር ደብረፅዮን

የፎቶው ባለመብት, TPLF/FB
የትግራይ ክልል አስፈላጊውን ሁሉ በማድረግ የራሱን ምርጫ ማካሄድ እንደሚችል የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካል ተናገሩ።
የትግራይ ክልል ገዢ ፓርቲ ሊቀ መንበር የሆኑት ዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካል ይህንን የተናገሩት በምርጫና በኮሮናቫይረስ ዙሪያ ትናንት መቀለ ውስጥ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ነው።
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ እንዳሉት "የፌዴራል መንግሥት ምርጫ ሊያካሂድ እንደማይችል በማስታወቁ በክልል ደረጃ ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን እየተከላከልን በጥንቃቄ ምርጫውን ማካሄድ እንችላለን" ብለዋል።
ጨምረውም "በክልላችን ምርጫው በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ በክልሉ ካሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከማህበራትና ከሕዝብ ጋር በመመካከር የምርጫ ቦርድንም ባሳተፈ ሁኔታ ሕጋዊ አፈፃፀም እንዲኖረው ይደረጋል" ብለዋል።
የትግራይ መንግሥት በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ሲወስን ለኮሮናቫይረስ ትኩረት ባለመስጠት ሳይሆን ለሕዝብ ውሳኔና ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ በመሆናቸው እንደሆነም ተናግረዋል።
ከመስከረም በኋላ በየትኛውም ደረጃ ሥልጣን ላይ ያለው የመንግሥት መዋቅር ሕጋዊነት ስለማይኖረው ምርጫ ሳይካሄድ ከቀረ አደገኛ ሁኔታ ሊከሰት እንደሚችል ያስጠነቀቁት ዶ/ር ደብረፅዮን "ከመስከረም በኋላ የፌዴራልም ሆነ የክልል መንግሥታት ቅቡልነትም ሆነ ሕጋዊነት ስለማይኖራቸው በአገር ደረጃ ምርጫ አለመካሄዱ አደገኛ ነው" በማለት አስጠንቅቀዋል።
ከመስከረም ወዲያ ሥልጣን ላይ መቆየት "ከሕዝብ ውሳኔና ፍላጎት መውጣት ነው፤ ከሕገ መንግሥትም ውጪ ነው" ብለዋል።
"ወደ ውድድሩ እንገባለን፣ ልንመረጥም ላንመረጥም እንችላለን"
የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን፤ "ወደ ውድድሩ እንገባለን፣ ልንመረጥም ላንመረጥም እንችላለን" ሲሉ ምርጫ ማካሄድ የግድ መሆኑን አስምረውበታል።
አያይዘውም ምርጫ ማካሄድ አይቻልም ቢባል እንኳን፤ ቀጣይ እርምጃ ምን መሆን አለበት የሚለውን መወሰን የሚችው ሕዝብ እንዲሁም የፖለቲካ ፓርቲዎች መሆኑን ጠቁመው፤ "አገር አቀፍ ምክክር ያስፈልጋል" ብለዋል።
ምርጫን ማካሄድ የሚያስፈልገው የዜጎችን የመምረጥና የመመረጥ መብትን እንዳይጣስ ለማድረግ ነው ያሉት ዶ/ር ደብረፅዮን "አሁን ያለው ሁኔታ ምርጫን የማራዘምና ያለማራዘም ብቻ ሳይሆን የሕዝብን ውሳኔ አለመተግበር፣ ሕገ መንግሥቱ ያለማክበር ነው" ብለዋል።
"ምርጫ አይካሄድም እየተባለ ያለው በኮሮናቫይረስ ምክንያት አይደለም" ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ "ቀደም ሲል ፍላጎትና ዝግጅት ቢኖር ኖሮ በግንቦት ወር ላይ ማድረግ ይቻል ነበር" በማለት ቀድሞውኑም ምርጫ ለማድረግ ፍላጎት እንዳልነበረ አመልክተዋል።
ለተፈጠረው ችግር በመንግሥት በኩል ቀርቦ የተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀውን ውሳኔንም በሚመለከት "ከምርጫ ጋር ተያይዞ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የሚተረጎም ነገር የለም፤ አምስት ዓመት ማለት አምስት ዓመት ነው" ሲሉ የትርጉም ጥያቄ የቀረበበትን ሁኔታ አጣጥለውታል።
ከዚህ ይልቅም ሕገ መንግሥቱን በጣሰ መንገድ ስልጣንን ለማራዘም የተለያየ ሰበብ ከማቅረብ፣ ከሕዝብና ከፖለቲካ ፓርቲዎች እንደዚሁም ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት መፍትሄ መሻት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።
ዶክተር ደብረ ፅዮን በሕገ መንግሥቱ በየአምስት ዓመቱ ምርጫ መካሄድ እንዳለበትና ከሕዝብ ምርጫ ውጪ ወደ ኃላፊነት መምጣት እንደሌለ በግልፅ የተቀመጠ መሆኑን አመልክተው "ከመስከረም በኋላ በፌዴራል ደረጃም ሆነ በክልሎች አሁን ያሉት መንግሥታት የስልጣን ጊዚያቸው ስለሚያበቃ። ህጋዊነት ስለማይኖራቸው ምርጫውን ማድረግ ወሳኝ ነው" ብለዋል።
"ኮሮናቫይረስ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ምክንያት መሆን የለበትም"
ሕወሓት በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምርጫ ይካሄድ፣ አፈጻጸሙ ላይ ደግሞ ምክክር ይደረግ የሚል አቋም እንዳለውም አክለዋል። ምርጫ ቦርድና ምርጫውን የሚታዘብ ነፃ አካል ተሳትፎ፣ በሥርዓት ምርጫው እንዲካሄድ ፍላጎት እንዳላቸውም አያይዘው ጠቅሰዋል።
"ምክንያት ደርድረን ወይም ለሕገ መንግሥት ትርጉም ሰጥተን ልንቀጥል አንችልም" ብለዋል ርዕሰ መስተዳድሩ።
ዶ/ር ደብረፅዮን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ደብረፅዮን፤ ኮሮናቫይረስ ሥልጣን ላይ ለመቆየት ምክንያት መሆን የለበትም" ሲሉ በመግለጫው ተናግረዋል።
ኮሮናቫይረስ መቼ እንደሚወገድ ስለማይታወቅ፣ ጥንቃቄ እያደረጉ ምርጫ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። ምርጫ እንደቀደሙት ጊዜያት ሳይሆን የቅስቀሳ ሂደት እና ድምፅ አሰጣጥ ጥንቃቄ የተሞላ ሆኖ ምርጫውን ማካሄድ ይቻላል ብለዋል።
"ኮሮናቫይረስን ለመከላከል ራሱ ሕዝቡ የሚፈልገው መንግሥት መሆን አለበት" ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ "ያልተመረጠ መንግሥትን ማስቀጠል ተቀባይነት የለውም። ወደ አምባገነንነት እየተቀየረ ነው ማለት ነው" ሲሉ በዛሬው መግለጫ ተናግረዋል።
አያይዘውም "ምርጫ ይካሄድ ያለ መወቀጥ አለበት፤ የተባልከውን ስማ፣ ተግብር ካልሆነ ትወቀጣለህ የሚለው ነገር መፍትሔ አይሆንም፤ የባሰ ነገሩን ያቀጣጥለዋል፤ ችግሩን ያባብሰዋል። የኃይል እርምጃ የሚያስወስድ ነገር የለም" ሲሉም አቋማቸውን አስታውቀዋል።
"ሕዝቡ ከፈለገ ይምረጠን ካልፈለገ ይወርውረን" ሲሉም ለምርጫ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።














