የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሃማዱ ቡሃሪ ለሞተ ግለሰብ ሹመት ሰጡ

የፎቶው ባለመብት, PHILL MAGAKOE
የናይጄሪያው ፕሬዚዳንት ሙሐማዱ ቡሃሪ ለሞተ ሰው ሹመት መስጠታቸው አነጋጋሪ ሆኗል።
ቶቢያስ ቹክዌሜካ ኦክውሩ ከሞቱ ሁለት ወራት ቢያልፋቸውም በቅርቡ የአንድ የመንግሥት መስሪያ ቤት የቦርድ አባል ተደርገው በፕሬዚዳንቱ ተሹመዋል።
ፕሬዚዳንት ቡሃሪ ለአገሪቱ ምክር ቤት ከሰሞኑ የ37 እጩ ተሿሚዎችን ዝርዝር የያዘ ደብዳቤ የላኩ ሲሆን፤ የሞቱትም ግለሰብ ስም በዝርዝሩ ውስጥ ተካቷል።
የፕሬዚዳንቱ ሚዲያ አማካሪ ላውሬታ ኦኖቺ በበኩሏ ፕሬዚዳንቱ በቦርድ አባልነት ሲሾሟቸው ግለሰቡ በህይወት እንደነበሩ ገልፀው "የትምህርትና የሥራ ማስረጃቸውን አቅርበዋል። ለሹመታቸውም ዝግጁ ሆነው በደስታ ነበር የተቀበሉት" ብላለች ላውሬታ።
"በሚያሳዝን ሁኔታ ህይወታቸው ሲያልፍ የምክር ቤቱን የማጣራት ሂደት እየጠበቁ ነበር። የማለፋቸውም ዜና ለፌደራል መንግሥቱ አልተነገረም" ብላለች።
ምንም እንኳን አማካሪዋ ይህንን ትበል እንጂ ፕሬዚዳንቱ እንዲህ አይነት ከባድ ስህተት ሲፈፅሙ የመጀመሪያቸው አይደለም። ከዚህ ቀደምም፣ ከሦስት ዓመታት በፊት ከሞቱ ረዥም ጊዜ ያለፋቸውን አምስት ሰዎች ለመንግሥት መስሪያ ቤቶች በቦርድ አባልነት ሾመዋል።








