ኬንያ ከለይቶ ማቆያ ያመለጡ ሰዎችን እያደነች ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኬንያው ፕሬዝደንት ኡሁሩ ኬንያታ ለኮሮናቫይረስ ለይቶ ማቆያ ከተዘጋጁ ሥፍራዎች ሲያመልጡ በካሜራ ዕይታ ሥር የገቡ ሰዎችን አሳደን እንይዛለን ብለዋል።
'እናውቃችኋለን፤ አሳደንም እንይዛችኋለን' ሲሉ ነው ፕሬዝደንቱ ማስጠንቀቂያ አዘል መልዕክታቸውን ያሰሙት። ፕሬዝደንቱ ያመለጡት ሰዎች የሌሎችን ሕይወት አደጋ ላይ ጥለዋል ይላሉ።
በኬንያ መዲና ናይሮቢ ከሚገኝ አንድ የኮሮናቫይረስ ለይቶ ማቆያ የተወሰኑ ግለሰቦች በአጥር ተንጠላጥለው ሲያመልጡ የሚያሳይ ምስል በማሕበራዊ ድር አምባዎች መሠራጨቱን ተከትሎ ነው ፕሬዝደንቱ 'የትም አታመልጡም' ሲሉ የተሰሙት።
ይህ ጽሑፍ በX. የቀረበ ይዘት ይዟል። ገጹ ቴክኖሎጂዎች ወይም ኩኪዎች ሊኖረው ስለሚችል ገጹ ከመከፈቱ በፊት የእርስዎን ፍቃድ እንጠይቃለን። ፍቃድዎን ከመስጠትዎ በፊት የX ኩኪ ፖሊሲ እና የ ማንበብ ይፈልጉ ይሆናል። ይዘቱን ለማንበብ ‘እቀበላለሁ ቀጥል’ የሚለውን ይምረጡ።
የ X ይዘት መጨረሻ
በለይቶ ማቆያው ውስጥ የሰነበቱ ሰዎች ሥፋራው ምቾት የሌለው እንደሆነ ሲያማርሩ ተደምጠዋል።
ማዕከሉ ከእሥር ቤት ምንም የሚተናነስ አይደለም የሚሉት እኒህ ሰዎች ቦታው ንፅህና እንደሚጎድለውና እጅግ በጣም ብዙ ሰዎች ስላሉ ማሕበራዊ መራራቅ የሚታሰብ አይደለም ሲሉ ምሬታቸውን ያሰማሉ።
ሌሎች ደግሞ ለቆዩባቸው ቀናት ከ60-100 ዶላር ድረስ ክፍያ መፈፀማችን አግባብ አይደለም ይላሉ።
ሆቴሎች፣ ትምህርት ቤቶች ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ እንዲከርሙ የተደረጉ ሰዎችን ሲያስተናግዱ ሰንብተዋል።
ከ400 በላይ ሰዎች አሁን ላይ በለይቶ ማቆያዎች እንዳሉ ይነገራል።
ምን ያክል ሰዎች ከለይቶ ማቆያዎች እንዳመለጡ የታወቀ ነገር የለም። ነገር ግን 50 ሰዎች ሳያመልጡ አልቀረም የሚሉ ዘገባዎች እየወጡ ነው።
ሲትዝን የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣብያ እንደዘገበው ሰዎች ምግብ እየቀረበ ሳለ ነው ያመለጡት ሲል ዘግቧል። አክሎም ዝናብ ሲዘንብ ጠባቂዎች ወደ መጠለያቸው መግባታቸውን አይተው ነው ያመለጡት ብሏል።
ዴይሊ ኔሽን የተሰኘው ጣብያ ደግሞ የተወሰኑ ሰዎች አጥር ዘለው ሲያመልጡ የሚታዩበትን ተንቀሳቃሽ ምስል አጋርቷል።
ኬንያ ከምሸቱ 1፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ንጋት 11፡00 የሚቆይ ሰዓት እላፊ ጥላለች። አልፎም ወደ ዋና ከተማዋ ናይሮቢ መግባትም ሆነ መውጣት ክልክል ነው።
የረመዳን ፆም መግባትን ተከትሎ መልዕክት ያስተላለፉት ፕሬዝደንት ኡሁሩ ዜጎች በሕግ እንዲመሩ ተማፅነዋል።












