ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከግጭት ጋር በተያያዘ በ74 የዩኒቨርሲቲው ማሕበረሰብ ላይ እርምጃ ወሰደ

የፎቶው ባለመብት, Gonder University FB
በተለያዩ የአገሪቷ ክፍሎች በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች በሚከሰቱ ግጭቶች የሰዎች ሕይወት አልፏል፣ የአካል ጉዳት አጋጥሟል፣ በንብረት ላይም ጉዳት ደርሷል። ከእነዚህም ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነበር።
ዩኒቨርሲቲው ችግሮቹን ለመፍታት "አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ" የሚለውን ጨምሮ የተለያዩ መፍትሄ ይሆናሉ ያላቸውን ተግባራዊ እያደረገ ይገኛል።
በዚህም ታህሳስ 22/2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ፤ በግጭቶቹ በተለያየ ደረጃ ተሳትፈዋል ባላቸው ተማሪዎች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሠራተኞችና የጤና ባለሙያ ላይ እርምጃ መወሰዱን የዩኒቨርሲቲው ኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር ይዳኝ ማንደፍሮ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
እርምጃው የተወሰደው ከኅዳር 4 ጀምሮ በዩኒቨርሲቲው ከተፈጠሩ ግጭቶች ጋር በተያያዘ ነው።
ኃላፊዋ እንዳሉት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ እጃቸው አለበት ተብለው የተጠረጠሩት ግለሰቦች በተለያዩ ማስረጃዎች፣ የዐይን ምስክሮች እና እጅ ከፍንጅ የተያዙ ሲሆኑ እንደየ ተሳትፏቸው ቅጣቱ ተላልፏል።
ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሂደት እንዳይቀጥል ለማደናቀፍ በተቀናጀ መልኩ በውጭም ካሉ ኃይሎች ግፊት በድርጊቱ ላይ የተሳተፉም ይገኙበታል ብለዋል።
በዚህም መሠረት 2 ተማሪዎች ለአንድ ዓመት፣ 39 ተማሪዎች ደግሞ ለሁለት ዓመት ከትምህርታቸው እንዲታገዱ፣ እንዲሁም 11 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርታቸው እንዲሰናበቱ ተወስኗል።
ከዚህም በተጨማሪ ለ7 መምህራን የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ተሰጥቷል።
3 መምህራን እና 8 የአስተዳደር ሠራተኞች እንዲሁም የጤና ባለሙያም ሙሉ ለሙሉ ከሥራ እንዲሰናበቱ ውሳኔ ተላልፏል።
"የአምቡላንስ አሽከርካሪ ግጭት ሲከሰት በሥራ ገበታው ላይ ባለመገኘቱ፤ ለአንድ ተማሪ ሞት ምክንያት ሆኗል" በሚልም ሙሉ ለሙሉ ከሥራው ተሰናብቷል። የጦር መሳሪያ አስቀምጠው የተገኙ ፕሮክተሮችም እርምጃው ከተወሰደባቸው የአስተዳደር ሠራተኞች መካከል እንደሚገኙበት አክለዋል።
በወቅቱ ከነበረው የተማሪው ግድያ ጋር በተያያዘ የተያዙ ሰዎች ምርመራ እየተካሄደባቸው እንደሆነ ያስታወሱት ኃላፊዋ፤ አሁን ላይ እርምጃ የተወሰደባቸው "ሁከት የፈጠሩ፣ ያባባሱ፣ ተማሪዎችን የሚስፈራሩ መልዕክቶችን ሲለጥፉ የተያዙ" ናቸው ብለዋል።
ዩኒቨርሲቲው ከከተማው አስተዳደር፣ የፌደራል ፖሊስ፣ የክልል ልዩ ኃይል እና ኮማንድ ፖስት ግብረ ኃይል ጋር በመቀናጀት በተደረገ ማጣራት የተገኙ ማስረጃዎች ላይ ተመስርተው የተጠረጠሩት ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን ኃላፊዋ አስረድተዋል።
ውሳኔውን የፌደራል ሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ባለሙያዎች ቡድን አባላት ከዩኒቨርሲቲው ሴናተሮች ጋር በመሆን ታህሳስ 22/2012 ዓ.ም ባካሄዱት ስብሰባ ነው ውሳኔውን ያሳለፉት።
ከዚህም በኋላ የዩኒቨርሲቲውንም ሆነ የከተማውን ማህበረሰብ ሰላም ለማስከበር በመሰል ድርጊቶች ላይ በሚሳተፉ ማንኛውም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ሴኔቱ አስጠንቅቋል።
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከፌደራል መንግሥትም ጋር በመሆን በግቢው ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የተለያዩ አማራጭ መፍትሔዎችን እያከናወነ እንደሆነ የሚገልፁት ኃላፊዋ "አንድ ተማሪ ለአንድ ቤተሰብ " የሚለውን ፕሮጀክት በምሳሌነት ይጠቅሳሉ።
በዚህ ፕሮጀክት በዩኒቨርሲቲ ያሉ ተማሪዎች በችግራቸው ጊዜ የሚያማክሩት፣ የሚከታተላቸው፣ የሚጠይቃቸው ቤተሰብ የሚፈጥሩበት ነው።
እነዚህ ወላጆች በዩኒቨርሲቲው የታመነባቸውና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ እንደሚወጡም የታመነባቸው ናቸው።
"እኔም ለአራት ተማሪዎች ቤተሰብ ሆኛለሁ፤ እንደዋወላለን፤ እንጠያየቃለን" ብለዋል።
ይህም ችግሮችን ለመፍታት እና ተማሪዎችን ለማረጋጋት በጎ አስተዋፅኦ እያደረገ እንደሆነ አክለዋል።

በተያያዘ ዜና ታህሳስ 21/2012 ዓ.ም በወሎ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ ተከስቶ በነበረው ግጭት ጉዳት ከደረሰባቸው 3 ተማሪዎች መካከል የአንድ ተማሪ ሕይወት ማለፉ ይታወቃል።
በተማሪው ግድያ የተጠረጠረ አንድ ተማሪ ከነተባባሪዎቹ ታህሳስ 22 ከምሽቱ 4፡00 አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገፁ አስታውቋል።
ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ሥር ማዋል የተቻለው በተማሪዎች ጥቆማ በተማሪዎች ማደሪያ [ዶርም] በተደረገ ፍተሻ እንደሆነ አስታውቋል።













